25/06/2026
#ችሎት
የበረከት ወርቁ (በረከት ገበሬዋ) የክስ ሂደት በሌለችበት እንዲታይ ተወሰነ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት "በገበያ ላይ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት አድርገዋል" የተባሉ የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር(ዲባራ ፉፋ) እና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር (አቶ ሹምአለም ብርሃኔ) ጨምሮ የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች ጉዳይ እየተመለከተ መሆኑ ይታወቃል።
ተጠርጣሪዎቹ ከመመሪያ ውጪ የነዳጅ ግዥና አከፋፋይነት ፈቃድ በመስጠት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሊትር ናፍጣ በኮንትሮባንድ እንዲሸጥ በማመቻቸት እና ከጅቡቲ የሚመጣ ድጎማ የተደረገበትን ነዳጅ ከቁጥጥር ውጪ በማድረግ ወንጀል የተከሰሱ 13 ተከሳሾች ውስጥ የ 4 ተከሳሾች እና የአንድ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ክስ እንዲቋረጥ በመደረጉ ክሳቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተከሳሾች ቁጥር 9 ሆኗል።
ከእዚህ ቀደም በነበረው የችሎት ውሎ ከ1ኛ እስከ 10 ኛ ተከሳሾቹ የተከሰሱበት የክስ መዝገበ ከ 10 ኛ እስከ 13ኛ ተከሳሾች ከተከሰሱበት ክስ ተሻሽሎና ተለይቶ እንዲቀርብ እና ለበረከት ወርቁ(በረከት ገበሬዋ) የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግ ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
በረከት ወርቁ ሰኔ 8/2018 በታተመው የአዲስ ዘመን እና Jun 18/2026 በታተመው Ethiopian Herald ጋዜጣ ጥሪ ቢደረግላትም በችሎቱ አልተገኘችም።
በመሆኑም ከእዚህ ቀደም በነበረው የክስ መዝገብ በሰባተኛ ተከሳሽነት በተሻሻለው የክስ መዝገብ ደግሞ በ 5 ኛ ተከሳሽነት የተቀመጠችው በረከት ወርቁ የክስ ሂደት በሌለችበት እንዲካሄድ ተወስኗል።
አቃቢ ህግ ክሱን ለይቶ እና አሻሽሎ በሁለት መዝገብ ያደራጀው ሲሆን በተሻሻለው ክስ መሰረት በመጀመሪያው የክስ መዝገብ እነ ዲባራ ፉፋን ጨምሮ 6 ተከሳሾች በሁለተኛው የክስ መዝገብ እስምአለም ምህረቱን ጨምሮ ሦስት ተከሳሾች ይገኛሉ።
በገበያ ላይ ነዳጅ እጥረት እንዲከሰት በማድረግና ሥልጣንን ያለአግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል በድምሩ ከ 30 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በመንግስት ላይ በማድረስ በሚል ክስ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት ተከሳሾች የክስ ሂደት በተለዋጭ ቀጠሮ በሌላ ችሎት እንዲታይ ተወስኗል።
መዝገቡ በሌላ ችሎት እንዲታይ ተመርቶ የነበረ ቢሆንም ሳይታይ በመቅረቱ ተለዋጭ ቀጠሮው ቀን በዛሬው የችሎት ውሎ ሳይወሰን ቀርቷል።
መንግሥት ድጎማ ያደረገበትን ነዳጅ ከጅቡቲ በመጫን 17.8 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ጉዳት በማድረስና በዋና ወንጀል አድራጊነት የመንግሥትን ሥራ በማይመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ከ 11 እስከ 13 ኛ ያሉ ተከሳሾችን በሚመለከት ደግሞ ምስክሮችን የመስማት ሂደት በቀጠሮው መሰረት የሚቀጥል ይሆናል።
ፌዴራል ፖሊስ ይፈለጋሉ ካወጣባቸው እና እስካሁን በቁጥጥር ስር ያልዋሉትን ተከሳሾች ጌታቸው አሞኘ እና አቡሽ አየለን በሚመለከት ፖሊስ በአድራሻቸው ፈልጎ እንዳላገኛቸው ለችሎቱ የተገለጸ ሲሆን የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ታዟል።
የጌታቸው አሞኘ እና አቡሽ አየለ የጋዜጣ ጥሪ ለመጠባበቅ እና አቃቢ ህግ የሚያቀርባቸውን 24 ምስክሮችን የመስማት ሂደት ለማከናወን ከሐምሌ 21 እስከ 23/2018 ዓም ቀጠሮ ተሰጥቷል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ/ም