08/04/2026
አገልግሎትን ለማሳለጥ የመንግስት ሰራተኛው በከፍተኛ ተነሳሽነት መስራት እንዳለበት ተገለጸ።
የለሚ ኩራ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በወረደው ሰነድ ዙሪያ ከአጠቃላይ የመንግስት ሰራተኛው ጋር ባደረገው ውይይት የመንግስት ሰራተኛው ፈጣን ፍትሀዊና ከእጅ መንሻ የጸዳ አገልግሎትን ለመስጠት በከፍተኛ ተነሳሽነትና የእኔነት ስሜት መስራት እንደሚገባው ገልጿል።
የመወያያ ሰነዱን በማቅረብ መድረኩን የመሩት የክ/ከተማው ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ድርብሳ ተስፋ ዜጎች ማንኛውንም ህጋዊ አገልግሎት መመሪያና አሰራሩ በሚፈቅደው መሰረት የማግኘትና ስለ አገልግሎቱ በቂ መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው ገልጸው አገልግሎት ለመስጠት የተቀመጠው አካል ያለምንም ማጉላላትና እጅ መንሻ ፈጣን፣ ፍትሀዊና ስታንዳርዱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የበኩሉን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል።
አቶ ድርብሳ አክለውም መንግስት አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ለሰራተኛው በርካታ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አንስቶ አገልግሎትን እስከማዘመን ድረስ ሰፋፊ ርምጃዎችን በቆራጥነት መውሰዱን ገልጸው በቀጣይም የተሳለጠ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ተናግረዋል።