03/09/2026
መጪውን የአዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ በየካ ክፍለ ከተማ የንግድ ትርኢት እና ባዛር ተከፈተ።
በየካ ክፍለ ከተማ መጪውን የአዲስ ዓመት በዓል አስመልክቶ "መሠረታዊ የግብርናና የኢንዱስትሪ ፍጆታ ምርቶችን በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰባችን በማቅረብ ገበያን እናረጋጋለን!" በሚል መሪ ሀሳብ የበዓል ባዛር ተከፍቷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኤፍሬም ግዛው ባዛሩ ሻጮችንና ሸማቾችን በቀጥታ ለማገናኘት ያለመ የግብይት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
ውጤታማና አጥጋቢ የግብይት ሥርዓት እንዲሰፍን የሁሉም አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ር ኤፍሬም ባዛሩ በሰላማዊና ሥርዓት በተሞላበት መልኩ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የስራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው አስራት በበኩላቸው፣ ባዛሩ ለነዋሪዎችና ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት የሚያግዝ፣ የግብይት ሥርዓቱን የሚያሻሽልና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል።
የባዛሩ ዓላማ በሸማቾች እና በአምራቾች መካከል ቀጥተኛ የግብይት ሥርዓትን በማጠናከር የምርት አቅርቦትን ማሳደግና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ ማቅረብ መሆኑን ያመለከቱት አቶ እንዳልካቸው፣ ለባዛሩ ስኬታማ አፈጻጸም የተረባረቡ አካላትን በአስተዳደሩ ስም አመስግነዋል።
ባዛሩ በቀጣይም በቅንጅትና በተቀናጀ አሠራር እንዲጠናከር አስፈላጊው ሥራ በየደረጃው መከናወን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የተከፈተው የበዓል ባዛር እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ሲሆን፣ የክፍለ ከተማው ንግድ፣ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ህብረት ሥራ፣ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና እንዲሁም ሥራና ክህሎት ተቋማት በጋራ በመሆን የባዛሩን አገልግሎት እያስተባበሩ ይገኛሉ።
#የካ