17/08/2024
በትብብር የመቆምና በጋራ የመልማት ትሩፋት፦ አረንጓዴ አሻራ!
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት መዛባት የሚያስከትላቸው የአፈር መሸርሸር፣ የወንዞች መመናመን፣ የዱር እንስሳት ሽሽት፣ ድርቅ እና በመሳሰሉ ችግሮች ተጠቂ ከሆኑ ሀገራት ተጠቃሽ ናት፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የሚደቅነውን ከባድ ፈተና መቋቋሚ የሚችል ልማት እንዲሁም የሚያስከትለውን ችግር ማቃለል የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ስላልነበረ በድርቅ እና በርሀብ በርካታ ወገኖቻችን ሲጎዱ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡
በጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተራቆተውን የሀገራችንን የደን ሽፋን አረንጓዴ በማልበስ የአየር ንብረት መዛባቱን በማስተካከል ተጨባጭ ስኬቶች የታዩበት ሲሆን ከሶስት በመቶ በታች የነበረውንና ወደ 20 በመቶ እየተጠጋ የሚገኘውን የከተማችንን የአረንጓዴ ሽፋን ለማሳያ መጥቀስ ከበቂ በላይ ነው፡፡
በትብብር መቆምና በጋራ የመልማት ትሩፋት የችግሮቻችን ሁሉ መውጫ መንገድ ነው። አረንጓዴ አሻራችን አንድነትን በማጽናት ሀገራዊ ልዕልናን የምንገነባበት አንዱ የአርበኝነት መገለጫ ነው።
''የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ'' በሚል ዕሳቤ በመላው ኢትዮጵያ የሚደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የወል ሀገርን የምንገነባበት የወል እውነታችን ነው።
አረንጓዴ አሻራችን በግብርና መስክ በበጋና በክረምት ወቅት የጀመርነውን የማምረት አቅም በማሳደግ ከተረጅነት ዕሳቤ የምንላቀቅበትን ዕድልም አስፍቷል፡፡
የአረንጓዴ አሻራችን የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ፀጋዎች በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን የምናጎለብትበትና እድገቷንና ብልፅግናዋን ለመጪዎቹ ትውልድ ማስቀጠል የሚችል አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት የኢትዮጵያን ብልፅግናን እውን የምናደርግበት ተግባር ነው።
የጋራ በሆነችው ምድር የኢትዮጵያ ልምላሜ ብቻውን በቂ ስለማይሆን አረንጓዴ አሻራችን በተለይም በጎረቤት ሀገራት እና በመላው አፍሪካ እንዲስፋፋም ብርቱ ፍላጎት እና ጅምር ጥረት መኖሩን መረዳት ይቻላል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት