01/09/2026
የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሄደ፤
የ10 አመት የተከለሰ ኮምፕሬሄንሲቭ የቡና ስትራቴጂ ዕቅድም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።
ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣ ከቡና ሻይና ቅመማ ቅመም አብቃይ ክልሎች እና የባለስልጣኑ አመራሮች በታደሙበት መድረክ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ10 አመት የተከለሰ ኮምፕሬሄንሲቭ የቡና ስትራቴጂ ዕቅድ ላይ የግምገማና ውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ልማት ዘርፍ ኃላፊ ክቡር አቶ ታጋይ ኑሩ ንግግር አሰምተዋል። በንግግራቸው ያለባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የታቀደ ከዳር እንደማይደር ስለሚታወቅና የተገኘውም የክንውን ውጤት በመድረኩ በታደሙ አካላት እና በቡና ተዋናዩ ጥረት ስለሆነ በጋራ ለመነጋገር መድረኩ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል።
ከተዘጋጀ ፓኬጅ የተቀዱ በአንገብጋቢነት የሚለዩ የቡና ኢኒሼቲቮች እንዳሉ የተናገሩት ኃላፊው ወደአርሷደሩ እንደወረደ ገልጸዋል፤ በጉዳዩ ላይም ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።
በማስከተልም አቶ ቦንሳ መርጋ የባለስልጣኑ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ ዕቅድ አፈጻጸሙን አቅርበዋል። ሲያቀርቡም 1.6 ሚሊዮን ሄክታር በቡና እንደተሸፈነ ገልጸው ከአምናው አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ14 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
የምርት አፈጻጸሙን ሲያቀርቡም 1.5 ሚሊዮን 80 ሺ ቶን እንደሆነ ተናግረው ምርታማነት 9.4 ኩንታል በሄክታር እንደሆነ ገልጸዋል።
ከላይ የተጠቀሱት ውጤቶች የተመዘገቡበት ምክንያቶችን ሲናገሩ በአዲስ ቡና ተከላ፣ በማሳ እንክብካቤ፣ በጉንደላ እና በነቅሎ ተከላ ላይ ስራዎች በመሰራታቸው ነው ብለዋል። በቀጣይም ጉንደላና ነቅሎ ተከላ ላይ በይበልጥ መሠራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በሻይውና በቅመማቅመም ሰብሎች ላይ ያለውን አፈጻጸም አቅርበዋል።
የኤክስፖርት አፈጻጸሙን ሲያቀርቡም 40 በመቶ የዓለም ዋጋ በቀነሰበት፣ የሆርሙዝ ክስተት በታየበት፣ የነዳጅ ዋጋ በናረበት፣ የብራዚል ቡና በገፍ ወደገበያ በገባበት ሁኔታ የታቀደው 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተሳክቷል ብለዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከታቀደው የቡና መጠን ያነሰ ተልኮ መሳካቱም ስኬቱን ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
በዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ውስጥ ለመጣውም ውጤት ምክንያቶቹን ሲያቀርቡም ከጀረጃ 1 እስከ ደረጃ 3 ያሉ ቡናዎች መጠን እና ዋጋቸው መጨመር መሆኑን ጠቅሰው ይህ ምን ያህል የቡና ጥራት ላይ ውጤታማ ስራ እንደተሰራ ማሳያ ነው ብለዋል።
በማስከተልም ስትራቴጂ ዕቅዱ ቀርቦ በሁለቱም አጀንዳዎች ላይ ሐሳቦች ከታዳሚው ተሰንዝረው የመድረኩ ፍጻሜ ሆኗል።
አሸናፊ ጌታሁን እንደዘገበው