Tazeb Tadie

Tazeb Tadie to read book

22/08/2025

ቤተ ክርስቲያን "እንቁዎቼ" ከምትላቸው ሴት ጻድቃን አንዷ ናት፡፡

| ቅድስቷ ወላጆቿ ከእርሷ በቀር ሌላ ልጅ የሌላቸው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብፅ ተወልዳ ያደገች ክርስቲያን ስትሆን ቅድስት እንባ መሪና ትባላለች፡፡ "እንባ መሪና" የወንድ ስም ነው የእርሷ ስም "መሪና" ቢሆንም በተለየ ታሪኳ ምክንያት በወንድ ስም ተጠርታለች፡፡

ቅድስት መሪና ገና ልጅ ሳለች እናቷ ማርያም ስለሞተችባት ያሳጋት ደግ አባቷ ነው፡፡ አሥራ አምስት ዓመት ሲሆናትም "ልጄ! እኔ ወደ ገዳም ስለምሔድ አንቺን መልካም ባል ላጋባሽ" አላት፡፡ ቅድስት መሪናም "የራስህን ነፍስ አድነህ እንዴት የእኔን ትተዋታለህ? እኔም እመንናለሁ" አለችው፡፡ አባቷ የተናገረችው ከልቧ እንደሆነ ሲያውቅ "ልጄ! በአካባቢው ያለው ገዳም ሁሉ የወንድ ብቻ ነውና አይሆንም" አላት፡፡ እርሷ ግን "አባቴ! ግዴለህም፣ ስሜን እንደ ወንድ ቀይረህ፣ አለባበሴንም ለውጥ" አለችው፡፡

አባትና ልጅ ሃብት ንብረታቸውን ሸጠው ለነዳያን አካፈሉ፡፡ በፍጹም ልባቸውም መነኑ፡፡ በደረሱበት ገዳም ቅድስት መሪና በወንድ ስም "እንባ መሪና" በሚል ገባች፡፡ ቀጣዩ ሥራዋ እንደ ወንዶች እኩል መስገድ፣ መጾምና መጸለይ ነበር፡፡ ቅድስት መሪና በገዳም ስትኖር ማንም በእርሷ አይፈተንም፤ አያውቋትምና፡፡ እርሷ ግን ወጣት ሴት ሆና በወንዶች ገዳም ጸንታ መቆየቷ መልአካዊ ኃይልንም ይጠይቃል፡፡ በተጋድሎዋ ወንድሞች መነኮሳት ይደነቁባት ነበር፡፡ ጃንደረባ ናት ብለው ስላሰቡ ጺም ባለማውጣቷና በድምጿ መቅጠን አልተጠራጠሩም፡፡ አባቷ ምስጢሩን ያውቃልና ታሞ ከማረፉ በፊት አበ ምኔቱን ጠርቶ "ልጄን ወደ ከተማ እንዳትይልኩብኝ አደራ!" አላቸው፡፡ ያም ሆኖ አንዳንድ መነኮሳት ቅሬታ በማንሳታቸው ወደ ከተማ ተላከች፡፡

በዚህም ቀን ባደሩበት ቤት አንድ ጐረምሳ ገብቶ የአሳዳሪውን ልጅ ከክብር አሳንሷት፣ ወጣቱ መነኩሴ አባ እንባ መሪና ነው በይ ብሏት ሔደ፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ የዚያች ዘማ ሴት ጽንስ በታወቀ ጊዜ ለአባቷ "አባ እንባ መሪና እንዲህ አደረገኝ፡፡" አለችው:: አባት መጥቶ እየጮኸ መነኮሳትን ተሳደበ:: አበ ምኔቱ ግራ ተጋብቶ ቢጠይቀው "የአንተ ደቀ መዝሙር እንባ መሪና ልጄን ከክብር አሳነሳት" አለው፡፡ አበ ምኔቱ ቅድስቲቱን ጠርቶ ቁጣና እርግማንን አወረደባት፡፡ ሴት ነኝ ብላ ከመከራከር ይልቅም ተንበርክካ "ማሩኝ ወጣትነት ቢያስተኝ ነው?" አለቻቸው፡፡ ተቆጥተው ዕለቱን እየገፉ ከገዳም አስወጧት፡፡ ከባድ ቀኖናም ጫኑባት፡፡ ከስድስት ወራት በኋላም የእርሷ ልጅ ነው የተባለ ሕፃን አምጥተው ሰጧት፡፡ ይህኛው ግን ከባድ ፈተና ሆነባት፡፡ እንዳታጠባው አካሏ በገድል ደርቁአል::

ለሕፃኑ ከእረኞች ወተት እየለመነች አሳድጋው ወደ ገዳሙ ከከባድ ቀኖና ጋር ተመልሳ በትጋት እያገለገለች ሰላሳ ሰባት ዓመታት አለፉ፡፡ ሕፃኑም አድጐ ደግ መናኝ ወጣው፡፡ በመጨረሻ ቅድስት መሪና ታማ ዐረፈች፡፡ ሊገንዟት ሲቀርቡ ሴት ናት፡፡ እጅግ ደንግጠው አበ ምኔቱን ጠሩት፡፡ በዙሪያዋ ከበው እንባቸውን አፈሰሱ፡፡ ሥጋዋን በክብር ገንዘው፣ በአጐበር ጋርደው፣ በራሳቸው ተሸክመው "ስለ ቅድስት መሪና ብለህ ክርስቶስ ሆይ ማረን?" ሲሉ ዋሉ:: ድንገት ግን ከተባረከ ሥጋዋ "ይቅር ይበለን" የሚል ድምጽን ሰምተው ደስ ብሏቸው ቀበሯት፡፡ ገዳማውያን ዓለምን ጥለዋት ቢሔዱም በምናኔ የሚገጥማቸው መከራም የበረታ ነው፡፡ ነገር ግን በጸሎትና በትጋት ያልፉታል፡፡ ገዳማቸውን እየደገፍን በዓታቸውን እያጸናን ከበረከታቸው እንሳተፍ፡፡

ካለን ላይ ለተቸገሩ በማካፈል ለነፍሳችን ስንቅን እንያዝ

Address

Quarit
Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Tazeb Tadie posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share

Category