05/09/2026
የኢተምድ ሰራተኞችና የስራ መሪዎች በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉብኝት አደረጉ።
ነሐሴ 30/2018 ዓ/ም
አዲስ አበባ (ኢተምድ)
====================
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት (ኢተምድ) የስራ መሪዎችና ሰራተኞች በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመገኘት በፓርኩ ውስጥ በሚካሄዱ የላቁ የአመራረት ሂደቶች፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የጥራት አጠባበቅ ስርዓቶች ላይ ያተኮረ የልምድ ልውውጥ ጉብኝት አድርገዋል።
ጉብኝቱ በሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚታዩ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራሮችን በአካል በመመልከት የአምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፍላጎት መሰረት ያደረገ እና ዘመኑን የዋጀ የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን የስራ ትብብር ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በጉብኝቱ የቴክኖሎጂ እና የአመራረት ስርዓት በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ አለምአቀፍና ሀገር በቀል ኩባንያዎች የሚጠቀሟቸውን ዘመናዊ የምርት ቴክኖሎጂዎች እና አጠቃላይ በጥራት ጉዳይ ላይ ከአምራቾችና የኢንዳስትሪ ፓርኩ የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይትና ጉብኝት ተደርጓል።
የኢተምድ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መዓዛ አበራ በጉብኝቱ ተገኝተው በጥራት ማረጋገጫ አገልግሎቶች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የአለምአቀፍ ደረጃዎችን እና የጥራት ቁጥጥር መስፈርቶችን ያሟሉ መሆናቸውን የሚረጋገጡበት የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት አገልግሎቶችና አሰራሮች ላይ ገለፃ አድርገዋል።
የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሀላፊዎች በበኩላቸው መሰል የልምድ ልውውጦች በተቋማት መካከል ያለውን ትስስር የሚያጠናክሩና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያፋጥኑ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።