05/06/2026
ኮርፖሬሽኑ (EEC) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 85 ፕሮጀክቶችን በብቃት ማጠናቁቁን ገለጸ
ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፤
ኮርፖሬሽኑ፣ በሥራ ላይ ከነበሩት 385 ፕሮጀክቶች መካከል በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 85 ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ ከዕቅድ አኳያም ቀሪ የአንድ ወር ጊዜ ኖሮም በጥሩ አፈጻጸም ላይ መሆኑ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
ይህ የተገለጸው አዲሱንና ኮርፖሬሽኑ ተግባራዊ ያደረገውን የመዋቅር አደረጃጀትና የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተ ከሠራተኞች ጋር ባደረገው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡
ውይይቱ በኮርፖሬሽኑ ሁሉም ቢዝነስ ዩኒቶች እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በትናንትናዉ ዕለት የዲዛይንና ማማከር ቢዝነስ ዩኒት በቁጥር 800 ገደማ ከሚሆኑ የቢዝነስ ዩኒቱ አጠቃላይ ሠራተኞችና በየደረጃው ካሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የዲዛይንና ማማከር ቢዝነስ ዩኒት ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቢይ ፀጋዬ (ኢንጅነር) በፓወር ፖይንት የተደገፈ ገለጻ አቅርበዋል፡፡
የቀረበውን ገለጻ ተመስርቶም ተሳታፊ ሠራተኞች ይህን መሰሉ ውይይት ኮርፖሬሽኑ ሊያሳካ ላቀዳቸው የላቁ ግቦች ውጤታማነት ጅምር በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሠራተኞቹ አያይዘውም፤ በመዋቅሩ አሰራርና በሠራተኞች ምደባ ዙሪያ፣ በውሎ አበል፣ በስልጠና፣ በሕክምናና በቢሮ ውስጥ የህጻናት ማቆያ ስፍራን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
ለተነሱት ጥያቄዎችም የሚመለከታቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በምላሹም ከስትራክቸሩ ጎን ለጎን የተለያዩ የአሰራር ማኑዋሎች ተግባራዊ በመሆን ላይ ሲሆኑ በአሁን ሰዓት እየተዘጋጁ ያሉት የአሰራር ሥርዓቶች ተከትሎ ከቤቱ የቀረቡት ልዩ ልዩ ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ የሚያገኙበት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በመጨረሻም የኮርፖሬሽኑ (EEC) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽመልስ እሸቱ (ኢንጅነር) በሰጡት ማጠቃለያ፣ ኢንዱስትሪው አሁን ባለበት ሁኔታ ተቋሙ በውጤታማነት ቀጥሎ መዋቅር መስራቱና ተግባራዊ ማድረጉ፤ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር መሆኑን አስምረውበታል፡፡
አክለውም፤ ኮርፖሬሽኑ እያከናወናቸው ያሉትን ትላልቅ አገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች በመጥቀስ፤ ከነዚህ መካከል የጂኦ ፖለቲካውና የነዳጅ ችግሮች ያስከተሉትን መስተጓጎል ተቋቁሞ፤ 85 ያህሉን በላቀ ብቃት ማጠናቀቅ የተቻለው፣ አመራሩና አጠቃላዩ ሠራተኛ ባደረገው ያላሰለሰ ትጋት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ይኸው ተጠናክሮም ተቋሙን ወደፊት ማሻገር ይገባል ብለዋል፡፡
“የኮርፖሬሽኑ ትልቁ ሀብቱ ሰው ነው” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በቀጣዩ አንድ ወር ቀሪ ተግባራትን ያለማንጠባጠብ መተግበር እንደሚገባና የሠራተኛውም አፈጻጸም በአግባቡ ሊመዘን እንደሚገባው፤ በተያያዘም በተመሳሳይ ከሠራተኞች የሚነሱ ጥያቄዎች እታች ባለው መዋቅር መፈታት የሚችሉትን አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡