21/08/2026
ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡ ቅሬታ ስለማቅረብ ይሆናል
በጉዳዩ እንደተቀጠቀሰው እኛ ስማችን ቀጥሎ በፊርማችን ያረጋገጥን የሲዳማ ክልል የህብረተሰብ ተወካዩች የሲዳሙ አፎ/ሲዳሚኛ ቋንቋ/ የፌደራል የስራ ቋንቋነት ዝርዝር ከተካተቱ 5 ዋና ዋና ቋንቋዎች ውጪ መደረግ አስመልክቶ ያለንን ቅሬታ ቀጥሎ አቅርበናል።
1ኛ. በቡድን አራት (4) የሀገር ግንባታ አጀንዳ ስር የሲዳሚኛ ቋንቋ በፌደራል የሥራ ቋንቋዎች ምድብ ውስጥ እንዲካተት በአሥር፣ በአምሳ፣ በሁለት መቶ አምሳ እና በአምስት መቶ ቡድኖች ላይ ምክረ-ሀሳብ ቀርቦ ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም፤ አጀንዳዎች ተጣጥመው በአንድ ላይ ተዋቅረው ሲቀርቡ 5 ቋንቋዎች (አፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ አፍ ሶማሌ እና አፋርኛ) ቀጥታ የፌደራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ፤ ሲዳሚኛ ግን አስፈላጊነቱ በቀጣይ ታይቶ እንዲወሰን ተብሎ መቅረቡ ቅሬታ ፈጥሮብናል። ይህም፡-
* 1.1. የፌደራል መንግሥቱን የሥራ ቋንቋ ለመበየን ግልጽ የሆነ የአመራረጥ መስፈርት ባልተቀመጠበት ሁኔታ የሲዳሚኛ ቋንቋ ከቀዳሚዎቹ 5 ተመራጭ ቋንቋዎች ውጪ መደረጉ አግባብ አለመሆኑ፤
* 1.2. ከሁሉም ቡድኖች ተወጣጥተው የተመረጡ 120 አጠናቃሪዎች የውሳኔ ሀሳብ የማቅረብም ሆነ የቀረበውን ምክረ-ሀሳብ የመሻር ወይም የመለወጥ ሥልጣን በምክክር ኮሚሽኑ አሰራር የማይፈቀድ ሆኖ ሳለ፣ ተመካካሪዎች በቋንቋ ዙሪያ ያቀረቡትን ምክረ-ሀሳብ በመለወጥ ደረጃ መድበው ማቅረባቸውን የማንቀበለው መሆኑን፤
2ኛ. በሀገራችን በአሁኑ ወቅት ያሉት 12 ክልሎች እና 2 የከተማ አስተዳደሮች፤ በአጠቃላይ 6 የመንግሥት የሥራ ቋንቋዎችን (አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማሌኛ፣ አፋርኛ እና ሲዳሚኛ) በሕገ-መንግሥቶቻቸው ተቀብለው ተግባራዊ አድርገዋል። ይህም ማለት ከሲዳሚኛ ቋንቋ በስተቀር የሁሉም ክልሎች የመንግሥት የሥራ ቋንቋዎች የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ምክረ-ሀሳብ የቀረበ መሆኑን ያመላክታል። ከዚህ አኳያ የሲዳሚኛ ቋንቋ ብቻ ተነጥሎ ከዝርዝሩ ውጪ መደረጉ ኢ-ፍትሐዊ ከመሆኑም በላይ አግላይ በመሆኑ በድጋሚ እንዲታይልን እንጠይቃለን።
3ኛ. የሲዳማ ክልል የፌደሬሽኑ አባል ክልል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ የሲዳሚኛ ቋንቋ በክልሉ ሕገ-መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። በ1999 ዓ.ም በተደረገው የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሲዳማ ብሔር በቁጥር 2,966,474 የነበረ ሲሆን፣ በ2018 ዓ.ም የክልሉ ተወላጆች ቁጥር ከ5.5 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ግምት ያሳያል። በዚህም ከኦሮሞ፣ ከአማራ፣ ከሶማሌ እና ከትግራይ ቀጥሎ በሕዝብ ቁጥር በአምስተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ አንጋፋ ሕዝብ በመሆኑ፤
4ኛ. በተጨማሪም የመማሪያና የምርምር ቋንቋ በመሆን ከቅድመ-መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ (MA) ደረጃ ድረስ ትምህርት የሚሰጥበት፣ ሙሉ የሥነ-ልሳን ጥናትና ምርምር የተካሄደበት፣ የሕግ፣ የአዋጆች እና የቴክኖሎጂ አገልግሎት ላይ የዋለ አንጋፋ ቋንቋ በመሆኑ ከሌሎች አቻ ቋንቋዎች ተለይቶ ከፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋነት መገለሉ መሠረታዊ ስህተት በመሆኑ፤
5ኛ. የሲዳሚኛ ቋንቋ ከክልሉ በተጨማሪ ከአጎራባች ሕዝቦች (ከኦሮሞ፣ ከጌዲዮ እንዲሁም ከወላይታ) ጋር በአዋሳኝ ወሰኖች ላይ ዋነኛ የመግባቢያ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤ በተጨማሪም በፍልሰት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተናጋሪ ከክልሉ ውጪ በዋናነት በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሰራጭቶ ይገኛል። በዚህ ምክንያት የሲዳሚኛ ቋንቋ የፌደራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ ቢካተት የሕዝቦችን ትስስር የበለጠ ያጠናክራል የሚል እምነት ያለን በመሆኑ፤
6ኛ. የሲዳሚኛ ቋንቋ ከአፋን ኦሮሞ፣ ከአማርኛ፣ ከአፍ ሶማሌ፣ ከትግርኛ እና ከአፋርኛ ቀጥሎ የገዥው ፓርቲ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የምርጫ ቦርድ እና የምክክር ኮሚሽን ከሚጠቀሙባቸው የሥራ ቋንቋዎች ውስጥ አንዱ ነው። ነገር ግን ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል የሲዳሚኛ ቋንቋ ብቻ ተነጥሎ ከዝርዝር ውጪ መደረጉ ኢ-ፍትሐዊ እና አግላይ በመሆኑ በድጋሚ እንዲታይልን እንጠይቃለን።
በእነዚህ እና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሳ ኮሚሽኑ ቅሬታችንን ተቀብሎ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠን በትሕትና እንጠይቃለን።