24/08/2026
ሲኖሩ ለመብል፥ ለ'ኔ ለ'ኔ ቅሚያ ፤
ሲያልፍም ጊዜ ሄዶ፥ የታሪክም ሽሚያ ።
ሰሜን ወደ ደቡብ፥ ሥልጣኔ አንድምታ፤
ምሥራቅ ወደ ምዕራብ፥ፀሐይ ወጥታ ገብታ።
ምሽቱ ወደ ቀን ፥ ሌሊቱም ሲነጋ ፤
መፀው ወደ ፀደይ ፥ ክረምቱም ሲበጋ ፤
መስቀልና አደይ ፥ ፈክተውና በርተው ፤
ወቅቶች ተፈራርቀው፥ መጥተውና ሄደው፤
ካለፈም በኋላ ፥ ያ ሁሉ መከራ ፤
ያኔ ነው የሚመጣው፥ ያስመሣይ ፉከራ ።
በድል አጥቢያ ኮከብ ፤
ያም ይኼም መዋከብ ፤
"ብለን ነበር ..." ማለት ፤
ነግቶ ለውጡን ሲያዩት ።
መሃል ሰፋሪዎች ፣
ማልያ ቀያሪዎች ፣
ብልጣብልጥ ሰዎች ፤
. . . አጥር ላይ ነበሩ ፤
ሲነጋ ጠብቀው ፥ ወዲያው የዘለሉ ።
ደክመናል ፣ ወርደናል ፤
ቆስለናል ፣ ሞተናል ፤
ለትግሉ የሚሉ ፥ ብዙ ሰዎች አሉ ።
በዚያ ቀውጢ ጊዜ፥ የገዳይ አጃቢ ቀድሞ የነበሩ።
ታች እና ላይ ሲወረድ ሲወጣ ፤
እኔም ብዬ ነበር፥ ይኽ እንደሚመጣ ።
ዥዋዥዌ ሆነ ፥ የሀገሬ ክፉ ዕጣ ፤
ተጽፎ ይቀመጥ ፥ ቀን እስከሚወጣ ።
ሚሊዮን በለጠ አሰፋ ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፲፰ ዓ/ም