15/11/2025
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ሰጪነቷን ትቀጥላለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
*******************
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ሰጪነት ከአፍሪካ የመሪነት ሚናዋን መጫወት እንደምትቀጥል አስታወቁ።
ኢትዮጵያ COP 32ን ለማስተናገድ ያቀረበችውን ጥያቄ በሙሉ ድምፅ ለደገፈው ለአፍሪካ የተደራዳሪዎች ቡድን ምስጋና አቅርበዋል።
አፍሪካ በብራዚል ቤሌም ከተማ በተካሄደው የ2025ቱ የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (COP 30) ላይ በአንድ ድምፅ ተናግራለች፤ ዓለምም ሰምቷታል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የሰው ልጅ ከሚያጋጥሙት እጅግ ከባድ ተግዳሮቶች አንዱ የሆነውን ችግር ለመፍታት የሚደረገውን የጋራ ጥረት እንድንመራ ለተሰጠን ዕድልም እናመሰግናለን ነው ያሉት።
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እንዲህ ያለ ወሳኝ ኃላፊነት ስለሰጠንም ክብር ይሰማናል ብለዋል በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት።
ይህ እውቅና ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ባሳየችው የመሪነት ሚና እና ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን የማስተናገድ አቅሟ ላይ ያላችውን እምነት የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ገልጸዋለ።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2027 በአዲስ አበባ የሚካሄደው COP 32 ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ውጤት እንዲያስመዘግብ እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የጋራ እርምጃዎችን ለመውሰድ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደምትሠራም ቃል ገብተዋል።
አፍሪካ የመፍትሔ አህጉር መሆኗን እና በዓለም አቀፍ ጥረቶች ውስጥ ቁርጠኛ አጋር መሆኗን ለማሳየት ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን መጫወት ትቀጥላለችም ብለዋል።