13/04/2026
መንገዳችን መደመር፣ ምርጫችን የስንዴ ነዶ፣ መዳረሻችን ሁለንተናዊ ብልጽግና!
የምንከተለው መንገድ፣ የምንመርጠው ምልክት እና የምንመኘው ግብ በአንድነት ተሳስረው የኢትዮጵያን አዲስ ምዕራፍ ይተልማሉ። ይህ ጉዞ የትናንቱን መልካም እሴት ጠብቆ፣ የዛሬውን አቅም አቀናጅቶ ለነገው ትውልድ የምትመች ሀገር የመገንባት ጉዞ ነው።
መደመር እንዲሁ ቁጥርን ማብዛት ሳይሆን ባለን ላይ መጨመር፣ የጎደለውን መሙላት እና የተበተነውን አቅም ማቀናጀት ነው። ያለፉ ስህተቶችን እያረምን፣ መልካም ስራዎችን ደግሞ በማስቀጠል ሀገራዊ አንድነትን እናጠናክራለን። የሁሉንም ኢትዮጵያውያን እውቀት፣ ጉልበትና ሀብት በማቀናጀት የጋራ ቤታችንን እንገነባለን።
የስንዴ ነዶ እንዲሁ ምልክት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነታችን እና የጥንካሬያችን መገለጫ ነው። በላባችንና በወዛችን ለምለሙን መሬታችንን አልምተን፣ እጃችንን ከልመና አውጥተን የምግብ ሉዓላዊነታችንን እናረጋግጣለን። ነዶው የትጋትና የድካም ውጤት ነው። በአንድነት ተሰባስቦ የታሰረ ነዶ ደግሞ የማይበገር አንድነታችንን ያሳያል። ከቤት ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ የሚተርፍ ምርት በማምረት የኢኮኖሚ ጥንካሬያችንን እናበስራለን።
ብልጽግና ለጥቂቶች ሳይሆን ለሁሉም፤ በአንድ ዘርፍ ሳይሆን በሁሉም ዘርፍ የሚረጋገጥ የነፃነትና የክብር ኑሮ ነው።ዘመናዊ መሠረተ ልማት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የተደላደለ የኢኮኖሚ ሕይወት። ሰላም፣ ፍትህ፣ አብሮነትና የማንነት ኩራት የታከለበት ማህበረሰብ መፍጠር። ዛሬ የምንተክለው የብልጽግና ዘር ለልጆቻችን የምትመችና የተከበረች ኢትዮጵያን ያስረክባል።