06/09/2026
ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ለርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል እንደፈጠረ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ
***********
(አሶሳ፣ ጳጉሜ 1/2018 ዓ.ም) በክልሉ በአሶሳ ከተማ የተካሄደው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል እንደፈጠረ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።
ከነሐሴ 27 እስከ ጳጉሜ 1/2018 ዓ.ም በአሶሳ ከተማ ሲካሄድ የነበረው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ተጠናቋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ እንደገለጹት፣ ከለውጡ ወዲህ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያጋጥሙ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዋና እሳቤው የአምራች እንዱስትሪውን ማስተዋወቅና የክልሉን እምቅ አቅም ማስተዋወቅ እንደሆነም አቶ አመንቴ ተናግረዋል።
ተጨባጭ ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚቻለው ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት በማስገባት ለሀገር እድገት አስተዋጽኦ እንድያበረክቱ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ክልሉ ለኢንቨስትመንትና ለኢንዱስትሪ ምቹ አቅም ያለው መሆኑን የተናገሩት አቶ አመንቴ፣ ይህንን ለመጠቀም የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ያሉንን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋዎቻችንን በአግባቡ በማልማትና ወደ ውጤት በመቀየር የህብረተሰቡን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቶ አመንቴ ጠቁመዋል።
ቢሮው ለኤክስፖ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱት ተቋማት፣ ድርጅቶች እና የሚዲያ አካላት የእውቅናና ምስጋና መርሃ-ግብር አካሂዷል።