03/07/2023
የደቡብ ክልል ህገ ወጥ ንግድና ፀረ-ኮንትሮባንድ መከላከል ግብረ-ሃይል የምክክር መድረክ አካሄደ
ግብረ-ሃይሉ የ2015 በጀት ዓመት የ11 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል፡፡
ሀዋሳ ፣ሰኔ 26/2015ዓ.ም (ደ.ክ.ን.ገ.ል.ቢ) በመድረኩ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ እንደገለፁት ሀገራችን የተያያዘችውን ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን የብልጽግናና የልማት ጉዞ ቀጣይነት እንዳይኖረው ከሚጠቀሱ አፍራሽ ተግባሮች አንዱ የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ህገ ወጥ ተግባር በጋራና በትብብር በመቀናጀት ሥርዓቱን ወደ ህጋዊ መስመር ለማስገባት የባለድርሻ አካላት ሚናቸው የላቀ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አቶ ማሄ አክለውም በክልሉ በህገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ህጉንና ደንቡን በመጣስ በአቋራጭ ለመክበር የሚያደርጉት ሩጫ የመንግስትን የልማት አቅጣጫ እየተፈታተኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የቢሮው የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉሌሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቸርነት ፈቃዱ የፀረ-ኮንትሮባንድ የፀረ-ኮንትሮባንድ ኮማንድ-ፖስትና የቴክኒክ የግብረ-ሃይል የ11 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋው ውይይት ተደርጓል፡፡
የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የንግድ አሠራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ዘይቱና ኢብራሂም በበኩላቸው ህገ ወጥ ኬላዎች ለኑሮ ውድነት እንዲሁም ለኮንትሮባንድ መባባስ መንስኤዎች ስለሆኑ ይህንን ተግባር በጋራ መከላከል አለብን ብለዋል፡፡
በ11 ወራት ከገቢ፤ከወጪ ኮንትሮ ባንድ ፣ከኤክስፖርት ምርቶች ፤ከመሠረታዊ ሸቀጦች፤ከታክስ ሥወራ፤ ከቅጣት እንዲሁም ከተወረሱ ሸቀጦች አጠቃላይ ከ1 ነጥብ ዘጠኝ ብሊዮን ብር ግምት ዋጋ ያላቸው ለመንግስት ገቢ መሆኑን በቀረበው ሰነድ ላይ ተመላክቷል፡፡
በመድረኩ የሚመለከታቸው የክልል፣ የዞን እና የልዩ ወረዳ የፀረ-ኮንትሮ ባንድ እና ኮማንድ ፖስት ግብር-ሃይል እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡