10/07/2026
በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በ24 ብር ከ07 ሳንቲም ማቅረብ የሚያስችል የኃይል አቅርቦት ስምምነት ተፈረመ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኬንያው የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ (Kenya Power and Lighting Company - KPLC) ጋር አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በ24 ብር ከ07 ሳንቲም ለማቅረብ የሚያስችለው አዲስ ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኤሌክትሪክ ንግድ ለማጠናከር፣ በድንበር አካባቢዎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋት እና የምስራቅ አፍሪካን የኢነርጂ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው።
የኃይል አቅርቦት ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው እና የኬንያው አቻቸው ዶ/ር ኢ/ር ጆሴፍ ሲሮር ጋር በጋራ ሆነው ፈርመዋል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኢንጂነር ጌቱ እንደገለጹት፤ የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሀገራት በአንድነትና በትብብር ሲሠሩ ትልቅና ስኬታማ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ይህ ስምምነት ማሳያ ነው።
ስምምነቱ የጋራ ህልም የሆነችውን ይበልጥ የተገናኘች ምስራቅ አፍሪካን (Connected East Africa) እውን ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን የጠቀሱት ኢንጂነር ጌቱ፣ ኢነርጂ የሀብት ምንጭ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሕዝብ ወደ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያደርስ ድልድይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኬንያው KPLC ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢ/ር ጆሴፍ ሲሮር በበኩላቸው፣ ስምምነቱ ከኃይል አቅርቦት ትስስር ባሻገር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሰላምና የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በተለይም በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ የሚገኙ ማህበረሰቦች ከዚህ ስምምነት ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆናቸው በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው አክለው ገልጸዋል።
ይህ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኃይል ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከማሻሻል ባለፈ፣ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተቀናጀ የኃይል አቅርቦት ስርዓት (Regional Power Pool) ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ የቀጣናውን የኢኮኖሚ እድገት ለማበረታታት እና ለሕዝቦች የተሻለና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ እንደሚያስችል ይጠበቃል።
በስምምነቱ መሰረት የኬንያው የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ በአንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ለኢነርጂ 24 ብር 07 ሳንቲም እንዲሁም ለዲማንድ ቻርጅ 1 ሺህ 10 ብር ከ89 ሳንቲም የሚከፍል ይሆናል፡፡
#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት