13/08/2026
የባሕርዳር ከተማ አስተዳድር በ901 ማህበራት የተደራጁ 19ሺ 698 ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የሚያደርግ የብሎክ እጣ መርሀ ግብር ተካሄደ
ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም (ባሕርዳር ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ) የባሕርዳር ከተማ አስተዳድር የመንግስት ሰራተኞችን የመኖሪያ ቤት እጦት ችግር በመፍታት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ፣የማደራጀት ፣እውቅና የመስጠትና የካሳ ግምት ክፍያ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
በመሆኑም ከዚህ በፊት የቤት ማሕበር እውቅና ያገኙ እና የካሳ ክፍያ ያጠናቀቁ የ789 እና 119 ህብረት ስራ ማሕበራት የክልል ፣የከተማ እና ክፍለ ከተማ አመራሮች ፣የማህበራት አመራሮችና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ተካሄዷል።
የባሕርዳር ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው የራዕያችን መዳረሻ የባሕርዳርን ተጨማሪ ውበት ፣ልማትና ተመራጭነት ማጉላት ብቻ ሳይሆን በዘላቂ እድገት በተቃኘ ማስተር ፕላን ታግዞ ጥራትና ተደራሽነቱ የተረጋገጠ መሰረተ ልማት እና የነዋሪዎችን ፍላጎት ያማከለ የመኖሪያ ቤት ማሟላት ነው ብለዋል።
ለዚህም መላ አመራሩ ለመኖሪያ ቤት እጦት አንገብጋቢ ችግር ትኩረት በመስጠት በመንግስትና በግል ድርጅቶች ተቀጥረው ለህዝብና መንግስት አገልግሎት የሚሰጡ ከ26ሺ በላይ ነዋሪዎችን በመመዝገባና በማጣራት በመጀመሪያው ዙር የተለዩ 19ሺ 696 ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የብሎክ እጣ እንዲያወጡ መደረጉን ገልፀዋል።
በዚህም ተነሽ አርሶ አደሮች ማግኘት ያለባቸውን መብትና ጥቅም በማስጠበቅ ተገቢ ካሳ እና ትክ በመስጠት በኩልም በውጤታማነት የተከናወነ ቁልፍ ተግባር እንደነበር ተናግረዋል።
ባሕርዳር በለውጥ ጎዳና ላይ ናት ስንል በሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ትሩፋቶቿ ብቻ ሳይሆን በመኖሪያ ቤት አቅርቦትና መሰል ሰው ተኮር ስራዎች ዙሪያ በሚመዘገቡ ውጤቶች ጭምር ነው ብለዋል።
በቀጣይም በማጣራት ሂደት ላሉ ፣በባሕርዳር ዙሪያ ለተደራጁ እና ሌሎች ነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ሰፋ ያለ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ ባልተገባ መንገድ ቦታ ለመውሰድ የሚሞክሩ አካላትን የመከላከል ጉዳይ በትኩረት የተያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 1ሺ 045 ሄክታር መሬት በማዘጋጀት በመጀመሪያ ዙር ብቻ ከ19ሺ 696 በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ በማድረጉ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
የመኖሪያ ቤት ልማት ጉዳይ ለግለሰብ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ልማትና ብልፅግና እንዲሁም የተረጋጋና ኢኮኖሚያዊ ምህዳሩ የሰፋ አካባቢ ለመፍጠር ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
ለከተሞች መስፋፋትና መዘመን የቤት ልማት ፕሮግራን ጥራትና ተደራሽነት ማረጋገጥ ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነ ገልፀው ለዚህ ተግባር ውጤታማነት ደግሞ የሁሉንም አካል የጋራ ጥረት የሚጠይቅ እንደሆነ አሳስበዋል።
የባሕርዳር ከተማ አስተዳድር መሬት መምሪያ ኀላፊ ወ/ሮ መልካም ስራ ካሳው በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ለመኖሪያ ቤት እጦት ችግር መፈታት በሰጠው ልዩ ትኩረት በ4 ሳይቶች 1ሺ 045 ሄክታር መሬት አዘጋጅቶ ለዚህ አድርሷል ብለዋል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-የባሕርዳር ከተማ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ገጽ ይወዳጁ:-
Facebook
https://www.facebook.com/BahirdarcityGovenmentalCommunicationAffairsoffice
YouTube
https://www.youtube.com/channel/UCNoAcvzPiExah4lyaAb6_BQ
Telegram
https://t.me/Bahirdarcitycommunication
Twitter
https://x.com/BahirdarO8493?s=35
Tiktok
https://www.tiktok.com/