04/09/2026
የአማራ ክልል ውኃ ልማት ፈንድ ጽህፈት ቤት በ2018 በጀት ዓመት በ4 ከተሞች ለንፁህ መጠጥ ውኃ ማስፋፊያ የሚውል 59 ሚሊዬን ብር ብድር ሰጥቷል።
-------------------------------------
የጽ/ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አደም ወርቁ እንደገለጹት የአማራ ክልል ውኃ ልማት ፈንድ ጽ/ቤት በከተሞች የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሳደግ የሃገር ውስጥ የፋይናንስ አቅም ለመፍጠር የተቋቋመ ነው።
በመሆንም ለከተሞች የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ማስፋፊያ የሚውል የብድር አገልግሎት በረዥም ጊዜና በአነስተኛ ወለድ በማቅረብ፣ የገቢ አቅማቸውን በማሳደግ፣ የቀረብውን ብድር በማስመለስ ሌሎች ከተሞችንም በተመሳሳይ ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋቋመ ነው ጽህፈት ቤቱ።
ጽ/ቤቱ ሲቋቋም የመነሻ ሃብት ያልነበረው ቢሆንም በተከታታይ አመታት በተሰራው ስራ በየበጀት ዓመቱ እያደገ ያለ የብድር አመላለስና የብድር አቅርቦት እያደረገ እንደሚገኝም የጽ/ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመትም ከሰበሰበው ሃብት 40 ሚሊዬን ብር ለከተሞች ለማበደር አቅዶ የብድር አመላለሱን በማሳደግና ተጨማሪ ፋይናንስ በማፈላለግ 59 ሚሊዬን ብር ለከተሞች በብድር አቅርቧል።
በዚህም የጎንደር፣ የዳንግላ፣ አገው ግምጃ ቤት እና አርጎባ ልዩ ወረዳ መዲና ከተማ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል።
ጽ/ቤቱ በ2019 የበጀት ዓመት ክልሉ ባለው የመልማት አቅም ልክ ሃብት ለመሰብሰብ፣ የተሻለ ብድር ስርጭት ለማድረግና ለማስመለስ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቋል።