ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ - ወሎ Freedom & Equality Party - Wollo

  • Home
  • Ethiopia
  • Bistima
  • ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ - ወሎ Freedom & Equality Party - Wollo

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ - ወሎ   Freedom & Equality Party - Wollo “የወሎ ድምፅ ለነፃነት፣ ለፍትህ እና ለእኩልነት።
Voice of Freedom & Equality in Wollo.”

የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ያበርክት!! የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሀምሌ 8፣ 2018 በይፋ መጀመሩ ይታወሳሉ። ሀገራዊ ምክክሩ ቀደም ሲል በተመረጡ እና በስምንት አን...
15/08/2026

የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ያበርክት!!

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሀምሌ 8፣ 2018 በይፋ መጀመሩ ይታወሳሉ። ሀገራዊ ምክክሩ ቀደም ሲል በተመረጡ እና በስምንት አንጓዎች በተደራጁ አጀንዳዎች ዙሪያ ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እና የማህበረሰብ ክፍሎች በተወከሉ በሺህ የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች እየተካሄደ እንደሚገኝ የሂደቱ አስተባባሪ የሆነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

ምክክሩ ቀደም ሲል በተነደፈ የውይይት ስርዓት መሰረት በመካሄድ ላይ እንድሚገኝ እና ባለፉት ጥቂት ቀናት በአጀንዳዎች ላይ ምክክር በማካሄድ የተወሰኑት የስራ ቡድኖች ውይይታቸውን ማገባደድ መጀመራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ላይ ይገኛል።

በሀገራችን ለረዢም ጊዜ የልዩነት እና የግጭት ምንጭ ሆነው በቆዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረግ ምክክር እጅግ አከራካሪ እና አጨቃጫቂ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። በሀገራዊ ምክክሩ ውይይት እየተደረገባቸው የሚገኙ አጀንዳዎች፡ የማንነት ጉዳይ፣ የአስተዳደር ወሰን፣ የእኩል ተሳታፊነት እና እኩል ተጠቃሚነት፣ የታሪክ እና ትርክት ጉዳዮች፣ ሀገራዊ ምልክቶች እና መገለጫዎች፣ የከተሞች አስተዳደር፣ ቋንቋ፣ የህዝብ ውክልና እና የምርጫ ስርዓት እና ሌሎች እጅግ መሰረታዊ ጉዳዮች ሰፊ የሀሳብ ልዩነት እና ፍጭት ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው። በእነዚህ አጀንዳዎች ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን መገመት ይቻላል።

በታሪካዊም ሆነ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያየ እይታ፣ አስተሳሰብ፣ ፍላጎት፣ የታሪክ ግንዛቤ፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወዘተ ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ የፖለቲካ ኃይሎች በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ያላቸውን አስተሳሰብ በማቀራረብ፣ ሁሉንም አሸናፊ ሊያደርጉ በሚችሉ ምክረ ሀሳቦች ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ትእግስት፣ ጥበብ እና ኃላፊነት ይጠይቃል። በተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ሀገራችንን ካለችበት ውስብስብ ችግሮች አላቆ የተሻለ ሰላም እና እድገት የተረጋገጠባት ሀገር ለመፍጠር ከራስ እና ከራስ ቡድን ፍላጎት በላይ ሀገርን እና ህዝብን ያስቀደመ እይታ፣ ዝግጅት እና ቅንነት ያስፈልጋል።

ባለፈት ጥቂት ሳምንታት በሁሉም አጀንዳዎች ዙሪያ እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች ከሞላ ጎደል በመግባባት እና በሰላማዊ ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆናቸው ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ የምክክር ሂደቱን ሊያውኩ የሚችሉ አካሄዶች እና ፍላጎቶች ሲከሰቱ ይስተዋላል። ሀገራዊ ምክክሩ ዓላማውን በትክክል ያሳካ ዘንድ ሂደቱ ሳይንሳዊ በሆነ የምክክር ስነ ዘዴ፣ ገለልተኛ እና አካታች በሆነ መልኩ ሊካሄድ ይገባል።

በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎችም ሆነ ከሂደቱ ውጪ ያሉ ባለድርሻ አካላት ሂደቱን በተመለከተ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ የሚወስዱት አቋም እና የሚሰጡት አስተያየቶች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድሩ እና ሂደቱ የታለመለትን ዓላማ እንዳይመታ ሊያደርጉ ይችላሉ። በአንድ ወይም በጥቂት አጀንዳዎች ዙሪያ በሚፈጠር አለመግባባት አጠቃላይ የምክክር ሂደቱ ቅርቃር (Deadlock) ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ሀገራዊ ምክክሩ ዓላማውን እንዳያሳካ ምክንያት ሊሆኑ ይችላል።

በመሆኑም የተጀመረው ሀገራዊ ምክክሩ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የቆዩ እና ጥልቅ አለመግባባቶችን ለመፍታት በሚያስችል ሁኔታ ይጠናቀቅ ዘንድ፣ የምክክሩ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለሂደቱ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጾ ሊያበረክቱ ይገባል። በምክክሩ የሚሳተፉ አካላት ይህ ታሪካዊ ሂደት በስኬት ይጠናቀቅ ዘንድ፣ ከራስ ፍላጎት ባሻገር የሌሎችን ፍላጎት እና ስጋት በቅጡ ለመረዳት፣ ለመደራደር እና የሌሎችን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ መግባባት ላይ ለመድረስ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

የምክክር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የአንድ ወገን ፍላጎትን በሌሎች ላይ ለመጨን ከሚደረግ ሙከራ መራቅ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በምክክር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ከሚያደርጉ አፍራሽ ተግባራት መቆጠብ ያስፈልጋል።

የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር በሀገራችን ካሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች መካከል የተወሰኑትን ለመፍታት እና ቀሪ የሀሳብ ልዩነቶች በሂደት የሚፈቱበትን ልምድ እና ተግባራዊ ተሞክሮ ሰጥቶን እንደሚያልፍ ይጠበቃል። ነእፓ በሀገራችን አካታች ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ባለፉት ዓመታ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ፣ የተጀመረው የምክክር ሂደት እንዲሳካ የበኩሉን አስተዋጾ እንደሚያደርግ በዚህ አጋጣሚ ያረጋግጣል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ
ነሀሴ 6፣ 2018

በሌቦች ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥል!!ሙስና ነቀርሳ ነው!! ሀገራችንን ከገጠሟት ከፍተኛ ቀውሶች አንዱ እና ዋነኛው በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚፈጸም ሙስና እና ብልሹ አሰ...
10/08/2026

በሌቦች ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥል!!
ሙስና ነቀርሳ ነው!!

ሀገራችንን ከገጠሟት ከፍተኛ ቀውሶች አንዱ እና ዋነኛው በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚፈጸም ሙስና እና ብልሹ አሰራር ነው። በመንግስት መሰሪያ ቤቶች ውስጥ የተሰገሰጉ ባለስልጣናት እና ኃላፊነት የጎደላቸው የመንግስት ሰራተኞች እና ‘ባለሙያዎች’ ዜጎችን እጅግ ለከፋ ችግር ዳርገዋል። የተሰጣቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት ገሸሽ በማድረግ ነጋዴዎች፣ ነዋሪዎች፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የስራ እድል ለማግኘት ከመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚሹ ዜጎች ለከፍተኛ ጉቦ፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮች ተጋልጠዋል።

ጉቦ እና ሌብነት በበርካታ የፌዴራል እና የክልል የመንግስት ተቋማት የተስፋፋ ሲሆን፣ በመሬት አስተዳደር፣ በወጪ እና ገቢ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና መሰል የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል። በእነዚህ ተቋማት ውስጥ በግል ጥቅም የሰከሩ እና ኃላፊነት የማይሰማቸው የመንግስት ሹማምንት እና ባለሙያዎች ለዜጎች መሰረታዊ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጉቦ እንዲከፍሉ ማስገደድ እጅግ መደበኛ አሰራር ሆኗል።

በእነዚህ የሀገር ነቀርሳ በሆኑ ግለሰቦች ምክንያት ሀገር እና ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ። ለሀገር ተስፋ የሆኑ የንግድ እና ኢንቨስትመት ስራዎች ተኮላሽተዋል፣ ከፍተኛ የሀገር ሀብት ወድሟል፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሀገር ሸሽቷል፣ የስራ እድሎች ባክነዋል።

በመንግስት ተቋማት የተንሰራፋው ብልሹ አሰራር ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚፈለጉ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳያገኙ ከማድረግ ባሻገር የሀገራች እድገት እንዲስተጓጎል፣ መንግስት ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዳያገኝ፣ የሀገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲዛነፍ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚፈጸም ሙስና እና ሌብነት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አሻጥር፣ የሸቀጦች እና አገልግሎቶች ዋጋ እንዲንር፣ ስራ አጥነት እንዲስፋፋ፣ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ፣ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲበላሽ እና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር እና እንዲባባስ ያደርጋል። ብልሹ የመንግስት አሰራር ከምጣኔ ሀብታዊ ጉዳቱ ባሻገር፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት መንስኤ እና ለሀገር ሰላም እና ደህንነት አደጋ ደቅኗል።

በሀገራችን በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋውን ብልሹ አሰራር ለመከላከል እና ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ የተጠናከረ እና የተቀናጀ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር መንግስት በቅርቡ በአንዳንድ የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ላይ የወሰደው እርምጃ የሚበረታታ ነው።

የሀገራችን የገቢ እና ወጪ ንግድ ማሳለጫ፣ ለዜጎች የስራ እድል መፍጠሪያ፣ ለሀገር ከፍተኛ ገቢ ማስገኛ በሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ህዝብን የማገልገል ኃላፊነት ተሰጥቷቸው በሀገር እና በዜጎች ላይ ከፍተኛ በደል ሲፈጽሙ እና ከፍተኛ የሀገር ሀብት ሲመዘብሩ በነበሩ ግለሰቦች ላይ የተወሰደው እርምጃ፣ በሀገራችን መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት አንድ አርምጃ ነው። ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የህግ የበላይነትን እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መንግስት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ይደግፋል።

መንግስት በቅርቡ በመንግስት መስሪያ ቤቶች የተደበቁ ሌቦች ላይ የወሰደው እርምጃ ተስፋ ሰጭ ቢሆንም፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ከተንሰራፋው ብልሹ አሰራር አንጻር ኢምንት ነው። በሌቦች ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጨባጭ ውጤት ያስገኝ ዘንድ፣ እርምጃው በሁሉም መስሪያ ቤቶች ተሰግስገው ሀገርን እና ህዝብን ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረጉ ባሉ ከፍተኛ የመንግስት ሹማምንት እና የወንጀል ተባባሪ ባለሙያዎች ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በሙሰኞች ላይ የተወሰደው እርምጃ ፍሬ ያፈራ ዘንድ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የፍርድ ሂደቱን በቅርብ በመከታተል፣ በሀገር እና ህዝብ ላይ ወንጀል በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ አስተማሪ ቅጣት ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሊያደርጉ ይገባል። በህግ ቁጥጥር ያሉ ግለሰቦች በተካኑበት የሙስና ተግባር በጉቦ እና በብልሹ አሰራር ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ የፍትህ አካላት በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ስሜት ስራቸውን ሊሰሩ ይገባል።

በሀገራችን ለሰፈነው አስከፊ ድህነት እና አለመረጋጋት ዋነኛው ምንጭ በመንግስት ተቋማት የተንሰራፋው ሌብነት አንዱ እና ዋነኛው ነው። ከድህነት እና ኃላ ቀርነት ለመላቀቅ በተባበረ ክንድ የህዝብ ተቋማትን ከሌብነት እና ብልሹ አሰራር ልናጸዳ ይገባል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ
ነሀሴ 2፣ 2018

በሀገራዊ ምክክር . . . .   ከጥላች ወደ ፍቅር፣ከግጭት ወደ ሰላም፣ከልዩነት ወደ አንድነት፣ ከመወጋገዝ ወደ መተጋገዝ፣ ከመከፋፋል ወደ መሰብሰብ፣ ከመጠራጠር ወደ መተማመን ለመሸጋገር ለም...
19/07/2026

በሀገራዊ ምክክር . . . .
ከጥላች ወደ ፍቅር፣
ከግጭት ወደ ሰላም፣
ከልዩነት ወደ አንድነት፣
ከመወጋገዝ ወደ መተጋገዝ፣
ከመከፋፋል ወደ መሰብሰብ፣
ከመጠራጠር ወደ መተማመን ለመሸጋገር ለምክክሩ መሳከት የድርሻችንን እናበርክት!!

ምክክር ልዩነቶችን መፍቻ የተሻለው አማራጭ ነው!!

አባሪ፡
ነእፓ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር እንዲጀመር ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ለዓለም ዓቀፍ እና ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያደረገው ጥሪ፣ መጋቢት 2012።

ሀገራዊ ምክክር መጀመርን አስመልክቶ ከነጻነትና እኩልነት ፓርቲ  የተሰጠ መግለጫ!!በሀገራዊ ምክክር ነጻነት፣ እኩልነት እና ፍትህ የሰፈነባት ሀገር እንገንባ!!በሀገራዊ ምክክር አዲስ እና ጠን...
15/07/2026

ሀገራዊ ምክክር መጀመርን አስመልክቶ ከነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!!
በሀገራዊ ምክክር ነጻነት፣ እኩልነት እና ፍትህ የሰፈነባት ሀገር እንገንባ!!
በሀገራዊ ምክክር አዲስ እና ጠንካራ ማህበራዊ ውል እንሰር!!

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ መላ የሀገራችን ህዝቦች ለረዢም ዘመናት ሲመኙ ኖረዋል። መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተን እጅግ የተራራቁ የሀሳብ ልዩነቶቻችን በውይይት እና በድርድር ይፈቱ ዘንድ በርካታ ትውልዶች ሲጠይቁ ኖረዋል። የሀሳብ ልዩነትን በጠመንጃ የመፍታት የፖለቲካ ባህል አስወግደን በመነጋገር፣ በመደማመጥ እና በመከባበር ለሁላችን የምትሆን ሀገር ለመገንባት በርካቶች ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ሲወተውቱ ኖረዋል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ ሀገራዊ ምክክር ይካሄድ ዘንድ ከፓርቲው ምስረታ ጀምሮ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል። ነእፓ በመጋቢት ወር 2012 ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ የሀገራዊ ምክክር ጽንሰ ሀሳብ በመቅረጽ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለመንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አቅርቧል። ነእፓ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በሀገራዊ ምክክር ዙሪያ ዝርዝር ሰነድ በማዘጋጀት በኢትዮጵያ ሊካሄድ የሚገባው ሀገራዊ ምክክር ምን አይነት ይዘት እና ቅርጽ ሊኖረው እንደሚገባ ሀሳብ አበርክቷል። ነእፓ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማህበራት ጋር በመተባበር የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ትኩረት እንዲያገኝ የድርሻውን አስተዋጾ ለማበርከት ታትሯል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ላለፉት አመታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ የቆየው ሀገራዊ ምክክር በዛሬው እለት በይፋ በመጀመሩ መላ የነእፓ አባላት እና አመራሮች ላቅ ደስታ ተሰምቶናል። የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አባላት እና አመራሮች ላለፉት አመታት ተግባራዊ እንዲሆን ስትደክሙለት የቆያችሁት ሀገራዊ ምክክር እውን በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ። መላ የሀገራችን ህዝቦች በተለይም የፖለቲካ ልሂቃን እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በሀገራችን እውን እንዲሆን የታገላችሁለት ሀገራዊ ምክክር በዛሬው እለት ከሀሳብ ወደ ተግባር በመሸጋገሩ ደስተኛ እንደምትሆኑ እናምናለን።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሀገራችን ለረዢም ዘመናት የነበሩ እና አሁንም የቀጠሉ የእርስ በእስር ግጭቶች በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉት በምክክር፣ በድርድር እና በውይይት ነው ብሎ ያምናል። ነእፓ የሀሳብ ልዩነቶች በኃይል ሳይሆን በሀሳብ ሊፈቱ ይገባል የሚል ጽኑ አቋም አለው። ነእፓ ሀገራችን ከጦርነት አዙሪት እንድትላቀቅ እና ኢትዮጵያውያን እጅግ አስከፊ ከሆነ ድህነት እንዲላቀቁ የፖለቲካ ልዩነቶች በምክክር ሊፈቱ ይገባል የሚል የማይናወጥ እምነት አለው።

ይህ የፖለቲካ ፍላጎት ሊሳካ የሚችለው በሀገራዊ ምክክር ብቻ እና ብቻ ነው። ነእፓ ላለፉት አመታት አጥብቆ ሲያቀነቅን እና ሲወተውት የቆየው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በይፋ መጀመር በሀገራችን ሰላም፣ የፖለቲካ መረጋጋት እና ልማት እውን እንዲሆን ትልቅ እድል ይፈጥራል ብሎ እናምናለን።

በዛሬው እለት በይፋ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር በተለይም በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለውን እጅግ የተራራቀ የፖለቲካ ልዩነት በማቀራረብ፣ በጋራ በሚያግባቡን ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት የተሻለ እድል ይፈጥራል ብለን እናምናለን። በዛሬ እለት የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ከሚለያዩን ጥቃቅን ጉዳዮች ይልቅ በሚያስማሙን በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ተቀራርበን፣ ተነጋግረን እና ተግባብተን ለመስራት ታሪካዊ እድል ያስገኛል ብለን እናምናለን።

በመሆኑም ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ በውጤት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት እና ተጠያቂነት ስሜት የድርሻቸውን ይወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የዝግጅት ምእራፍ ተጠናቆ ዋናው የምክክር ጉባኤ እንጂጀመር አስተዋጾኦ ላበረከቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ላበረከቱት አስተዋጾ ምስጋና ያቀርባል።

ዛሬ አንድ ብሎ የጀመረውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬታማ በማድረግ ነጻነት፣ እኩልነት እና ፍትህ የሰፈነባት ሀገር እንገንባ። ዛሬ የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር በውጤት በማጠናቀቅ አዲስ እና ጠንካራ ማህበራዊ ውል እንሰር!!
ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ
ሀምሌ 8፣ 2018

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ሂደት እና ውጤት ግምገማ እና ምክረ ሀሳቦች።  ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ7ኛ ጠቅላላ...
03/07/2026

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
የ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ሂደት እና ውጤት ግምገማ እና ምክረ ሀሳቦች።


ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መገለጽን ተከትሎ በምርጫው ሂደት እና ውጤት ዙሪያ ሰፊ እና ጥልቅ ግምገማ አድርጓል። ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከፓርቲው ብሄራዊ ምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ የቀረበለትን የምርጫ እቅድ ክንውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና ድህረ ምርጫ የተሰሩ ስራዎችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችን፣ የተገኙ ውጤቶችን እና ተሞክሮዎችን በመገምገም ለቀጣይ የፓርቲው የምርጫ ተሳትፎ ውጤታማነት እና ለሀገራችን የምርጫ ስርዓት መሻሻል ይበጃሉ ያላቸውን ምክረ ሀሳቦች አስቀምጧል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ባዘጋጀው “የምርጫ ስትራቴጂ” እየተመራ በቅድመ ምርጫ ወቅት ውጤታማ ስራዎችን አከናውኗል። በዚህ ምዕራፍ ከተሰሩ ስራዎች ውስጥ ልዩ ልዩ የምርጫ ማስፈጸሚያ መመሪያዎች እና የአሰራር ደንቦች ማዘጋጀት፣ የእጩዎች ምልመላ እና ምዝገባ፣ የምርጫ ክርክር፣ የነጻ ሰዓት መልእክቶች ዝግጅት እና ስርጭት፣ የመራጮች ምዝገባ ቅስቀሳ እና ክትትል፣ የፓርቲ ወኪል ታዛቢዎች ምልመላና እና ስምሪት፣ የጎዳና ላይ፣ የቤት ለቤት እና የአዳራሽ ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳዎች ይገኙበታል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ካደረጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ እና ዋነኛው በመረጃ ላይ የተመሰረተ የምርጫ ማንፌስቶ ማዘጋጀት ሲሆን፣ በምርጫ ክርክር መድረኮች፣ በምርጫ ቅስቀሳ እና በሌሎች አጋጣሚዎች ለህዝብ እንዲደርስ አድርገናል። ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት ለመፍጠር አስፈላጊ ዝግጅት እና ከነእፓ ጋር ተቀራራቢ አጀንዳ ሊኖራቸው ይችላል ተብሎ ከታመነባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሰፊ ውይይት ማድረግ በቅድመ ምርጫ ከተሰሩ ስራዎች ውስጥ ይገኛል። ለምርጫ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ሀብት ከአባላት እና ከደጋፊዎች ለማሰባሰብ ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል።

እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ቅድመ ምርጫ ስራዎች ነእፓ በዜጎች ዘንድ በስፋት እንዲታወቅ እና ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርገዋል። የነእፓ አማራጭ የፖሊሲ አማራጮች ከፓርቲው ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ ፖለቲካ መርሆች ጋር ተዋህደው፣ ፓርቲያችን በመላ የሀገራችን አካባቢዎች እጅግ ሰፊ የህዝብ ተቀባይነት እና ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጎታል። በቅድመ ምርጫ ወቅት የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ባደረጉት የተቀናጀ እና መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ነእፓ የዜጎችን ቀልብ መግዛት እንዲችል፣ የፓርቲው የምርጫ ምልክት የሆነው ብዕር በዜጎች ልብ ውስጥ ታትሞ እንዲቀመጥ አድርጓል። በዚህም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነእፓ ታሪካዊ ድል ተጎናጽፏል።

ውድ የነእፓ አባላት፣ ደጋፊዎች እና መላ የሀገራችን ህዝቦች
ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ ዝግጅት እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከፍተኛ የህዝብ ቅቡልነት ማግኘት ቢችልም፣ በምርጫው ሂደት ላይ በተስተዋሉ የምርጫ ህግን እና አሰራርን የሚጥሱ ተግባራት ምክንያት የሚገባውን ውጤት ማግኘት ሳይችል ቀርቷል። ፓርቲው በተለያየ ደረጃ ባዋቀራቸው የምርጫ ክትትል ዴስኮች ከተመዘገቡ ቅድመ ምርጫ እና ምርጫ ችግሮች መካከል፣

📍በተለያየ እርከን ላይ የሚገኙ የመንግስት ሹመኞች እና የገዢ ፓርቲ አመራሮች በመራጩ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጫና ማድረግ፣ ከምርጫ ቀን አስቀድሞ የመንግስት አካላት ቤት ለቤት በመሄድ ዜጎች ገዢውን ፓርቲ እንዲመርጡ ማስፈራራት እና የስነ ልቦና ጫና ማድረግ፣ የፓርቲው እጩዎች ከእጩነት እንዲወጡ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ፣ የመንግስት እና የህዝብ ሀብትን ለምርጫ ስራ በስፋት መጠቀም፣

📍በምርጫው እለት በበርካታ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ድምጽ ለመስጠት የተሰበሰው ህዝብ ገዢውን ፓርቲ እንዲመርጥ መወትወት፣ ከዚህ አልፎ በሚስጥር ድምጽ በሚሰጥበት ቦታ በመግባት መራጩ ህዝብ ማንን መምረጥ እንዳለበት ማስገደድ፣ የድምጽ መስጫ ሰዓት መራዘምን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የምርጫ ህግን እና አሰራርን የሚጥሱ ተግባራት መፈጸም፣

📍የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛ አለመሆን፣ በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ምርጫ አስፈጻሚዎች ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ድምጽ ያልተሰጠባቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ድምጽ የመስጠት ህገ ወጥ ተግባር ላይ መሳተፍ፣

📍በድምጽ ቆጠራ ወቅት ፍጹም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ፓርቲያችን ያገኘውን ድምጽ ለሌሎች ፓርቲዎች በመስጠት ፓርቲያችን ሊያገኝ ይችል የነበረው ውጤት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ማድረግ። በተመሳሳይ በአንዳንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ለፓርቲያችን የተሰጡ ድምጾች እንዲባክኑ በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ተጨማሪ ምልክቶች ማስቀመጥ፣

📍በተለያዩ ክልሎች ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ የተሰጣቸው የነእፓ ወኪል ታዛቢዎች ምርጫውን መታዘብ እንዳይችሉ ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ በማድረግ ምርጫው ያለ ነእፓ ታዛቢዎች እንዲካሄድ ማድረግ። ከድምጽ መስጫ ቀን በኃላ ባሉ ተከታታይ የድምጽ ቆጠራ እና በምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች በተደረጉ የድምጽ ማዳመር ስራዎች የፓርቲያችን ታዛቢዎች እንዳይሳተፉ መከልከል፣

📍በ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የነእፓን ጨምሮ የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውጤት ዝቅተኛ እንዲሆን ካደረጉ በርካታ ምክንያቶች መካከል የፓርቲዎች በትብብር አለመስራት አንዱ ነው። ፓርቲዎች በምርጫው የነበራቸው የተናጠል ተሳትፎ ድምጽ እንዲከፋፈል አድርጓል። ነእፓ ከምርጫው አስቀድሞ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እጩ የማቅረብ ሀሳብ አቅርቦ ለተግባራዊነቱ ሰፊ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ሊሳካ አለመቻል፣

📍በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች በተለይም በተወሰኑ የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው የጸጥታ መደፍረስ በነእፓ የምርጫ እንቅስቃሴ እንዲሁም በምርጫው አጠቃላይ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደር። በዚህም ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች በቂ እጩዎችን ማቅረብ፣ የጎዳናም ሆነ የቤት ለቤት የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ ያልተቻለ ሲሆን ይህም በፓርቲው የምርጫ ውጤት ላይ ተጽእኖ አሳድሯል። ከዚህ ባሻገር በአካባቢዎቹ ያለውን የጸጥታ መደፍረስ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ ኃይሎች በምርጫ ሂደት ህገወጥ ተግባር ውስጥ መሳተፍ።

በጠቅላላው በድምጽ አሰጣጥ፣ በድምጽ ቆጠራ እና ድምጽ ማዳመር ወቅት በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች የምርጫውን ውጤት በጉልህ ሊቀይሩ የሚችሉ የአሰራር ግድፈቶች መፈጸማቸውን መገንዘብ ተችሏል። በምርጫ ሂደት የተፈጸሙ የህግ ጥሰቶችን የሚያሳዩ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ፣ የተፈጸሙት የህግ ጥሰቶች በህግ አግባብ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ አቅርበናል።


በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት የተከሰቱ እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ችግሮችን አልፈን በኢ.ፊ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በተለያዩ የክልል መስተዳድር ምክር ቤቶች የተወሰኑ መቀመጫዎችን ማግኘት ችለናል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የተጠቃለለ የምርጫ ውጤት መሰረት ነእፓ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3 መቀመጫ እንዲሁም በሰባት ክልል መስተዳድር ምክር ቤቶች 35 መቀመጫዎች አግኝቷል። ነእፓ ካገኛቸው እነዚህ ወንበሮች በብዙ እጥፍ የሚበልጡ እና የባከኑ ከፍተኛ የህዝብ ድምጽ ማግኘቱን ልብ ይሏል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት ባከናወናቸው ሰፊ ድርጅታዊ እና የአቅም ግንባታ ስራዎች እንዲሁም በምርጫ ወቅት ባካሄዳቸው የምርጫ እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት አስመዝግቧል ማለት ይቻላል። በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አልፈን፣ በምርጫው ያገኘናቸው ውጤቶች እና ያሳካናቸው ግቦች ነእፓ በቀጣይ በሚኖረው የምርጫ ተሳትፎ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል ትልቅ ግብአት ይሆናሉ ብለን እናምናለን።


የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የፓርቲያችንን የ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ እንቅስቃሴ እና ውጤት በጥልቀት ከገመገመ በኃላ የፓርቲያችንን ቀጣይ የምርጫ ተሳትፎ ውጤታማነት እንዲሁም የሀገራችንን የምርጫ ስርዓት፣ ሂደት እና ውጤታማነት ለማሻሻል ይረዳሉ ያላቸውን የሚከተሉትን ምክረ ሀሳቦች እና የስራ አቅጣጫዎች አስቀምጧል፣

1. ፡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛ አለመሆን እና የብቃት ማነስ በምርጫው ሂደት እና ውጤት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ፣ ምደባን እና ብቃት በተመለከተ ነእፓ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ያገናዘበ ጥናት በማካሄድ ግኝቶቹን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲያቀርብ፣

2. ፡ የምርጫ ታዛቢዎች ገለልተኛነት ለአንድ ምርጫ ነጻ እና ፍትሀዊ መሆን ከፍተኛ ድርሻ አለው። የምርጫ ታዛቢዎች በድምጽ አሰጣጥ እና ድምጽ ቆጠራ ሂደት የዜጎች ድምጽ እንዲከበር ትልቅ ሚና አላቸው። ይሁን እንጂ በሀገራችን “በገለልተኛ ታዛቢ” ስም በምርጫ የሚሳተፉ የምርጫ ታዛቢዎች የገለልተኛ ታዛቢነት መርህን ፍጹም በሚጻረር ሁኔታ የአንድ ወገን ደጋፊ ሆነው ሲያገለግሉ ይስተዋላል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ የታዛቢዎች ምልመላ እና ምደባ በተመለከተ በስራ ላይ ያሉ የህግ ማእቀፎች እና አሰራሮች እንዲሻሻሉ ነእፓ የራሱን ጥናት በማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት ምክረ ሀሳብ እንዲያቀርብ፣

3. ፣ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በመደበኛ ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማድረግ፡ በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እጅግ አዝጋሚ መሆን፣ ዜጎች ድምጻቸውን ለመስጠት ለረዥም ሰዓት ተሰልፈው እንዲጠብቁ አድርጓል። አዝጋሚ የሆነው የድምጽ አሰጣት ሂደት የድምጽ መስጫ ሰዓት እንዲራዘም ያደረገ ሲሆን፣ ይህም በተያያዥ የድምጽ ቆጠራ ስራ በወቅቱ እንዳይጀመር አድርጓል።

ከመደበኛ የድምጽ መስጫ ሰዓት ውጪ የሚካሄድ የድምጽ አሰጣጥ እና የድምጽ ቆጠራ ሂደት ምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የፓርቲ ወኪሎች እና ሌሎች “ገለልተኛ ታዛቢዎች” በድካም ስሜት ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ ያደረገ ሲሆን፣ ለብልሹ አሰራር ምቹ እድል ፈጥሯል። ይህንን ችግር ለመፍታት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በመደበኛ ሰዓት እንዲጠናቀቅ እና የድምጽ ቆጠራው በወቅቱ ተጀምሮ መጠናቀቅ የሚችልበት የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፣

4. ፡ በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ እና ምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች የፓርቲ ወኪሎች (ታዛቢዎች) መገኘት ፓርቲው የሚያገኘውን ድምጽ ለመጠበቅ እና ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጾ አለው። በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በነበረብን ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች በቂ የፓርቲ ወኪሎችን መመደብ አለመቻላችን ፓርቲው ያገኘውን ከፍተኛ የህዝብ ድምጽ ከህገ ወጥ ተግባራት መጠበቅ እንዳይችል ያደረገ ሲሆን፣ ይህም ፓርቲው ባገኘው ውጤት ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል።

በመሆኑም በቀጣይ በሚካሄዱ ምርጫዎች በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ እና ምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች በቂ ተቀማጭ እና ተንቀሳቃሽ የፓርቲ ወኪሎች ለማስቀመጥ በቂ ሀብት እንዲመደብ እና ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ፣

5. ፡ የፓርቲውን የምርጫ እንቅስቃሴ በጉልህ እንዲገደብ ካደረጉ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ እና ዋነኛው የፋይናንስ እጥረት ነው። የፋይናንስ እጥረት የፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ በከፍተኛ ደረጃ እንዲወሰን፣ በቂ እጩዎችን እና ታዛቢዎችን ማቅረብ እንዳይቻል እና ሌሎች ወሳኝ ስራዎች በተያዘላቸው ጥራት እና ብዛት እንዳይሰሩ አድርጓል። በመሆኑም በቀጣይ ፓርቲው በሚሳተፍባቸው ምርጫዎች በቂ ሀብት ለማንቀሳቀስ ልዩ ስራ እንዲሰራ፣

6. ፡ ነእፓ በ6ኛው እና በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫዎች ያገኘው ከፍተኛ የመራጭ ድምጽ እንዲባክን እንዲሁም የሀገራችን ጠቅላላ የምርጫ ሂደት እና ውጤት ፍትሀዊ እንዳይሆን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ኢ ፍትሀዊ የሆነው የምርጫ ስርዓታችን ነው። በመሆኑም ይህ ኢፍትሀዊ የምርጫ ስርዓት ይቀየር ዘንድ በቀጣይ በሀገራችን በሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በትብብር እንዲሰራ፣

7. ፡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲው የተሻለ ውጤት ያገኘባቸው አካባቢዎች፣ የተሻለ አደረጃጀት እና የተሻለ አመራር ያለባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል። የተሻለ የምርጫ ውጤት፣ ሰፊ እና ተከታታይ የአደረጃጀት ስራ የሚሻ ተግባር ነው። በመሆኑም ከምርጫ ማግስት ጀምሮ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የፓርቲውን ነባር አደረጃጀት ይበልጥ ለማጠናከር እና አደረጃጀት ባልተዘረጋባቸው አካባቢዎች የፓርቲውን መዋቅር ለመዘርጋት ሰፊ የአባላት ምልመላ እና አደረጃጀት ስራ እንዲሰራ፣

8. ፡ የሀገር ሰላም እና የዜጎች ደህንነት በሀገራችን ነጻ፣ ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው። በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የቀጠለው የሰላም መደፍረስ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እንቅስቃሴአችን ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አሳድሯል። በመሆኑም ነእፓ ሁሌም ለሰላም መስፈን የሚያደርገውን ጥረት በቀጣይ አጠንክሮ በመቀጠል፣ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ይሰፍን ዘንድ የድርሻውን መወጣት የሚያስችለው ስራዎችን መስራት። ከዚህ አንጻር ቀደም ሲል ነእፓ የጀመረው “ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ” የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆን የሚችልበትን ሌላ እድል መሞከር፣

9. ፡ 7ኛ ጠቅላላ ምርጫን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀው የፓርቲው የመጀመሪያ የሶስት ዓመት (2016-2018) ስትራቴጂክ እቅድ ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር ተጠናቋል። በመሆኑም 2ኛው የፓርቲው ስትራቴጂክ እቅድ (2019- 2023) 8ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ታሳቢ አድርጎ እንዲዘጋጅ፣

10. ፡ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም ደረጃ ያደረገው እንቅስቃሴ፣ መልካም ተሞክሮዎች፣ ተግዳሮቶች፣ በዝርዝር ተጠንተው ለቀጣይ ምርጫ ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ተሰንደው እንዲቀመጡ፤ እንዲሁም የሀገራችንን የምርጫ ስርዓት እና አሰራር እንዲሁም የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር ለማዘመን ልዩ ልዩ የህግ እና የስርዓት ማሻሻያ ጥናቶች እንዲካሄዱ እና የጥናቶቹ ግኝቶች ለፖሊሲ አውጪ አካላት በግብአትነት እንዲቀርቡ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።



#ምስጋና፡ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ልዩ ልዩ አስተዋጾ ላበረከቱ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን። ከሁሉም በማስቀደም ውስብስበ አሰራር፣ ሰፊ የሎጂስቲክስ፣ ጠንካራ የስራ እና የፋይናንስ እቅድ እና ዲሲፕሊን የሚሻውን ጠቅላላ ምርጫ እንዲሳካ፣ ነእፓን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደት ያጋጠሟቸው ችግሮች እንዲፈቱ ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉ የምርጫ ቦርድ ስራ አመራር አባላት እና ሰራተኞች ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን።

በተለያዩ ክልሎች እና ከተማዎች ምርጫ ቅስቀሳ በምናካሂድበት ወቅት ልዩ ልዩ ድጋፍ ላደረጉልን የክልል እና የከተማ መስተዳድሮች፣ የጸጥታ አካላት፣ ለምርጫው ማስፈጻሚያ የፋይናንስ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ላደረጉ የፓርቲያችን አባላት እና ደጋፊዎች፣ በምርጫ ክርክር እና በነጻ የአየር ሰዓት አጠቃቀም ወቅት ድጋፍ ላደረጉልን የሚዲያ ተቋማት እና ሌሎች በምርጫ ሂደት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ድጋፍ ላደረጉልን አካላት ላቅ ምስጋና እናቀርባለን። የሀገር ባለቤትነቱን በድምጹ ለማረጋገጥ ረዢም ሰዓት ተሰልፎ ድምጻቸውን ለሰጡ ኢትዮጵያውያን ያለንን ከፍተኛ አድናቆት እና ምስጋና እንገልጻለን።


ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝብ ድጋፍ አግኝተው ለመመረጥ ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉበት የፖለቲካ ሂደት ሲሆን፣ በምርጫ ማግስት የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ እና እድገቷን ለማስቀጠል ከፉክክር ይልቅ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ይገነዘባል። በመሆኑም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መጠናቀቁን እና የምርጫው ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ፓርቲያችን ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በሁሉም መስክ በትብብር ይሰራል።

ፉክክርን እና ትብብርን በሚዛን ጠብቆ ድርጅታዊ እና ሀገራዊ ተግባር እና ኃላፊነትን መወጣት የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሚዛናዊ ፖለቲካ አንዱ መገለጫ ነው። ነእፓ የሚከተለው ሚዛናዊ የትብብር እና ፉክክር መርህ በተለይ ሀገራችን በተለያዩ ውስጣዊ ፈተናዎች እና የውጭ ጫናዎች ውስጥ እያለፈች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት እጅግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።

በዚሁ መሰረት የሀገራን ሰላም በማስጠበቅ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ብሄራዊ ጥቅምን በማስከበር እና ሌሎች ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንሰራለን። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የፓርቲው መዋቅሮች ብሄራዊ ምክክርን ጨምሮ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይሰራሉ።

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውይይቱን ሲያጠናቅቅ በምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ በሀገራችን ጠንካራ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ለመገንባት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እንዲሰራ፣ በተመሳሳይ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በክልል ምክር ቤቶች ድምጽ ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጣቸውን የህዝብ ውክልና በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ አስተላልፏል።

በመጨረሻም ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በተለያዩ የክልል መስተዳድር ምክር ቤቶች ያገኛቸውን ወንበሮች በመጠቀም በሀገራችን ሰላም፣ ልማት እና መልካም አስተዳደር እውን ይሆኑ ዘንድ ለዜጎች የገባነውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ፣ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ በድጋሜ እያረጋገጥን፣ መጪው ጊዜ በሀገራችን አስተማማኝ ሰላም፣ ልማት እና ሀገራዊ መግባባት የሚረጋገጥበት ዘመን ይሆን ዘንድ ምኞታችንን እንገልጻለን።

!!

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ
ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
ሰኔ፣ 2018

የመጨረሻው ምዕራፍ እና የማይቀረው ብሔራዊ ኃላፊነትየትግላችን ጉዞ፦ ከእኩልነት ወደ መሪነት  ጠቅላላ ምርጫ" "በዚህ ምዕራፍ መሠረታዊ መደላድል ገንብተናል፦➾ በድርጅታዊ ቁመናችን፣ በሰነድ ዝ...
20/06/2026

የመጨረሻው ምዕራፍ እና የማይቀረው ብሔራዊ ኃላፊነት

የትግላችን ጉዞ፦ ከእኩልነት ወደ መሪነት

ጠቅላላ ምርጫ

" "

በዚህ ምዕራፍ መሠረታዊ መደላድል ገንብተናል፦

➾ በድርጅታዊ ቁመናችን፣ በሰነድ ዝግጅታችን፣ በአደረጃጀትና መዋቅራችን ራሳችንን አጠናክረናል
➾ በሀሳብና በፖሊሲ አማራጮቻችን ግልጽና ተጨባጭ አቋም ወስደናል
➾ ለህዝባችን አማራጭ ሀሳቦቻችንን በማስተዋወቅ ከዳር ወደ መሀል ጅማሮአችንን አጠናክረናል
➾ መልካም ዘርን በመዝራት የወደፊት ትውልድን መሰረት ጥለናል

👉 ውጤታችን፦ ከተፎካካሪዎቻችን ጋር እኩል ተራምደናል።

ጠቅላላ ምርጫ

" "

በዚህ ምዕራፍ ጉልህ እድገት አሳይተናል፦

➾ በድርጅታዊ ቁመናችን ከዓለት የጠነከረ አቋም ገንብተናል
➾ በተግባር ተኮር ሰነዶች ዝግጅታችን ጥራትን አሳድገናል
➾ በዲፕሎማሲ አቋማችንና በብሔራዊ ጥቅም እይታችን ብዙ አጋሮችን ከጀርባችን ማሰለፍ ችለናል
➾ ቀድመን የዘራነው መልካም ዘር ማፍራት ጀምሯል
➾ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ መጫወት ችለናል
➾ የመረጃ መረባችንን አጠናክረናል

👉 ውጤታችን፦ ከተፎካካሪዎቻችን አንድ እርምጃ ቀድመን መርተናል።

#በ2023 ለ8ኛው ጠቅላላ ምርጫ

" "

የቀጣይ የመጨረሻ ምዕራፍ ስራችን፦

ሀ. ስለ ህዝባችን መከራ ስቃይ

➾ በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን መንግስታዊ በደልና መከራ አጥብቀን እንታገላለን
➾ የህዝባችንን የመልማት ፍላጎት ሰፊ ድምጽ እንሰጣለን
➾ ስርዓቱ የፈጠረውን የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ ረሀብና ስደት፣ ጦርነት፣ ሞትና መፈናቀል፣ መንግስታዊ ሙስናና ብልሹ አሰራር በግልጽ እንቃወማለን

ለ. ስለ መሰረታዊ አገልግሎቶች

➾ ትምህርት፦ ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት (የትምህርት መር ብሔራዊ የልማት ስትራቴጂ) በቂ ግብዓት እንዲቀርብ እንጮሃለን
➾ ጤና፦ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ሳናሰልስ እንሞግታለን
➾ ፋይናንስ፦ የውስጥ ፋይናንስ አቅማችንን እናጠናክራለን
➾ ሙከራ ፕሮጀክቶች፦ የሙከራ ፓይለት ፕሮጀክቶቻችንን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ይፋ እናደርጋለን

ሐ. ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት

➾ ለመጭበርበር ክፉት የሆነውን የምርጫ ሂደት ወደ ተዓማኒና ገለልተኛ አሰራር እንዲቀየር እንታገላለን
➾ የሚድያና ኮሙኒኬሽን ተሳትፏችን በእያንዳንዱ ቤት ይነፍሳል
➾ የጉዞ ግስጋሴችን ወደማይቀረው አካታች፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትህ የሰፈነበት ሀገረ-መንግስት የመገንባት ኃላፊነት ይሆናል።

👉 የህዝባችን ክንድና ማዕበል ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ፣ ለዘላቂ ልማትና ሰላም!

አሳሳቢ ጥያቄያችን

አንድ ሀሙስ የቀረው ውስጡ የተፈረካከሰው ሀገርን እንደ እንቁላል በመዳፉ ይዞ እንደ ህጻን የሚጫወተው ስርዓት፦

➾ የነእፓን ሰላማዊ፣ ተቀባይነት ያለው፣ ምክንያታዊ ሚዛናዊ የትግል ስልት ተቋቁሞ ቀጣይ ምርጫ ደርሶ ስልጣኑን ማስረከብ ይችላል ወይ?

ለምን ነእፓ?

1. ሚዛናዊና ምክንያታዊ ፖለቲካ

ሚዛናዊና ምክንያታዊ (Moderate Liberal) ፖለቲካን መከተል መቻላችን

2. ትምህርት መር ብሔራዊ የልማት ስትራቴጅ

የፖሊሲዎቻችን ሁሉ ማጠንጠኛ "ትምህርት መር ብሔራዊ የልማት ስትራቴጅ" በመሆኑ

3. ጥበብ የተሞላ ትግል ስልት

የምንከተለው ትግል ስልታችን "ፖለቲካ ጠብ ሳይሆን ጥበብ ነው" (ትብብር፣ ድል-ድል፣ መካከለኛ መንገድ) መርህ በመሆኑ

4. ጥናትና መረጃ ተኮር አቋም

ንግግራችንም ሆነ ተግባራችን በፊት ሰፊ ጥናትንና በቂ መረጃን መሰረት ያደረገ በመሆኑ

5. ቀስ በቀስ፣ ተፈጥሯዊና ዘላቂ ለውጥ

የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንጠሌጥ እና የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል አይነት የተሳሳተ አካሄድን ሳይሆን ተፈጥሯዊ፣ ቀስ በቀስና ዘላቂ ለውጥን ተከትለን በትዕግስትና በስሌት የምንሰራ መሆኑ

6. ከዳር ወደ መሀል ግስጋሴ

ከዳር የጀመርነው ጉዞ አሁን ወደ መሀል ግስጋሴ ጫፍ ላይ በመድረሱ

7. የህዝብ ድምጽ

ምንም እንኳ የህዝብን ድምጽ ቢያጭበረብሩ ህዝባችን በድምጹ በቃችሁን በማለቱ

8. ታማኝነት

እንደ ሌሎቹ የህዝብ አደራ ክደን በብልጽግና እግር ስር ተጥመልምለን የማንወድቅ መሆናችን

"ነጻነትን፣ እኩልነትን፣ ፍትህን ያሰፈነ አካታች ሀገረ-መንግስት ለመገንባት ቁርጠኞች ነን!"

እንኳን ደስ አለን!! ጉዞ ወደ ፓርላማ!! የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንት ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት ሪፖርት ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮ...
18/06/2026

እንኳን ደስ አለን!!
ጉዞ ወደ ፓርላማ!!

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንት ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት ሪፖርት ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካቀረባቸው እጩዎች መካከል ሶስቱ ማሸነፋቸውን አሳውቋል።

ነእፓ ፓርቲያችንን እና ያቀረባቸውን እጩዎች ተቀብሎ በየምርጫ ክልሎቹ ድምጹን ለሰጠን ህዝብ እጅግ ላቅ ያለ ምስጋና ያቀርባል።

ተመራጭ የህዝብ እንደራሴዎቻችን የመረጣቸውን ማህበረሰብ እና መላ የሀገራችንን ህዝቦች በቅንነት፣ በታማኝነት እና በቁርጠኝነት እንደሚያገለግሉ ነእፓ ያረጋግጣል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የህዝብ ተወካዮቹ አማካኝነት በሀገራችን ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ልማት እውን እንዲሆን፣ የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ፣ ዜጎች በቂ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ማግኘት እንዲችሉ ይሰራል። የዜጎች የነጻነት፣ የእኩልነት እና የፍትህ ድምጽ እንዲሰማ አጥብቆ ይታገላል።

የሌሎች የፓርቲያችን ተወዳዳሪዎች ውጤት በቦርዱ ይፋ ሲደረግ እናሳውቃለን።

ለፓርቲያችን ተወካዮች መልካም የስራ ዘመን እንመኛለን!!

ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ!!
ሰኔ 11 2018

04/06/2026

Address

Bistima

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ - ወሎ Freedom & Equality Party - Wollo posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share