03/09/2026
“ሰላማችን ለዘላቂ ብልፅግናችን” በሚል መሪ ቃል የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና የ2019 ዓ.ም ዕቅድን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ።
#ቡታጅራ ነሐሴ 28/2018
የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ “ሰላማችን ለዘላቂ ብልፅግናችን” በሚል መሪ ቃል የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የገመገመና የ2019 ዓ.ም ዕቅድን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
መድረኩ በባለፈው ዓመት በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎችን መገምገም የታዩ ክፍተቶችን መለየትና በ2019 ዓ.ም በተሻለ መልኩ ለመሥራት እገዛ እንደነበረው ተመላክቷል።
የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተካልኝ ንጉሴ በዞኑ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ህብረተሰቡን በሰላም ግንባታ ሥራዎች ጠንካራ ተሳትፎ አንዲኖረው ማድረግና ማሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ የራስን አቅም ማጠናከር፣ በተቋማትና በህብረተሰቡ መካከል ትብብርን ማጎልበትና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን በቀጣይነት ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።
በየአካባቢው የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የቅሬታ ጉዳዮች በጊዜ ተለይተው በአግባቡ ካልተፈቱ ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ ስለሚችሉ በቅድሚያ መለየትና መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዞኑ በሶዶ ወረዳ ኦሮሚያ አጎራባች ቀበሌዎች አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የሽብር ቡድን በህብረተሰቡ ላይ የሰላም መደፍረስና የህይወትና የንብረት ጉዳት እያደረሰ የሚገኘውን ጥቃት ለመመከት የፀጥታ መዋቅሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እየሰራ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ በሚያደርገው ተሳትፎና በፀጥታ አካላት በሚከፈለው መስዋዕትነት የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ በመመከት አካባቢዎቹን ሰላማዊ ለማድረግ ተግባራዊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አቶ ተካልኝ ገልጸዋል።
እንዲሁም በዞኑ በምስራቅ መስቃን ወረዳና እንሴኖ ከተማ አካባቢዎችም ከፀጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸው አንስተው ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታትም መንግስት በየደረጃው የሰላምና ፀጥታ መዋቅሩን በማጠናከር የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን በማሳደግና ከህብረተሰቡ ጋር ትብብሩን በማጠናከር እየሰራ መሆኑ ገልፀዋል።
የፀጥታ መረጃ ጥራትና ተደራሽነትን ማሻሻል፣ የሚገኘውን መረጃ በተገቢው መጠቀምና በመረጃ ላይ የተመሠረተ የቅድመ ጥንቃቄ ሥርዓት በማጠናከር የፀጥታ ክስተቶችን ቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰቱም በፍጥነት ለማረም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ነጠላ ትርክቶችን በመዝራት ህብረተሰቡን ለመከፋፈል የሚጠቀሙ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘቶችን በመከታተል፣ ትክክለኛ መረጃን በፍጥነት በማቅረብና የህዝብ የመረጃ ግንዛቤን በማሳደግ ላይ መሥራት እንደሚገባ ያመላከቱ ሲሆን የፀጥታ ምክር ቤት የሚያስቀምጣቸውን አቅጣጫዎች በየደረጃው ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚገባ አንስተው በየደረጃው የወሳኝ ኩነቶችን በትክክለኛ መረጃ ላይ መደገፍና መረጃዎችን ዲጂታላይዝድ በማድረግ አገልግሎቱን በተቀመጠው አግባብ ማድረስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ሙሰማ ጀማል ባለፈው በጀት ዓመት የፀጥታ መዋቅር በቅንጅት በተሰሩት ስራዎች በርካታ ስኬቶች ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
የሰላም ከማስጠበቅ አንፃር በተሰሩ ጠንካራ ተግባራት የፀጥታ መዋቅሩና ህብረተሰብ በጀግንነት ተላላኪ የሆነው ሼኔ የሽብር ቡድን መመከት መቻሉን አንስተዋል።
የፀጥታ ሃይሉ ምስራቅ መስቃንና እንሴኖ አካባቢ የሚፈጠሩ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት እንደሚገኝ ገልፀው በቀጣይ ይበልጥ ተጠናክሮ የዞኑን ህብረተሰብ ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚደረጉት ጥረቶች የበኩሉን እንደሚወጣ አብራርተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በ2018 ዓ.ም አፈፃፀም ላይ ያሉ ጥንካሬዎችንና ክፍተቶችን በመገምገም ሃሳብ አስተያየት የሰጡ ሲሆን የሚሊሻና ሌሎች የፀጥታ አካላትን በሥነ-ምግባር ማነፅና ሙያዊ አቅማቸውን ማጠናከርም በመድረኩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ሆኗል። ይህም የአካባቢና የሀገር ሰላምና ፀጥታን በተሻለ ሁኔታ ለማስከበር የሚያስችል ቁመና እንዲኖራቸው የሚያግዝ መሆኑን በማንሳት የዞኑ የሰላምና ፀጥታ ሥራዎች በተቀናጀ አሠራር፣ በተገቢ መረጃና በህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲመሩም አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመጨረሻም በዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ የ2019 የግብ ስምምነት ከወረዳና ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤቶች ጋር ተፈራርመዋል።
ከግምገማው መድረክ በተጨማሪም መምሪያው ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ፣ በግዳጅ እያሉ ለተሰው የፀጥታ አካላት የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የአልባሳት ድጋፍ አድርገዋል።
ዘገባው የምስራቅ ጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።