21/08/2026
የፓይለት የተማሪ ምዝገባ በስረ-ገደል አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ እና መካከለኛ ት/ቤት እየተካሄ ይገኛል
======== ======== ======
የለገሂዳ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ለሚመለከታቸዉ የትምህርት ባለድርሻ አካላት የተማሪ ምዝገባ ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ ማካሂዱ ይታወቃል፤ በዚህም የ03 በስረገደል ቀበሌ ለፓይለት የተማሪ ምዝገባ ስራዉ ከተመረጡ ቀበሌዎች ዉስጥ አንዱ ነዉ፡፡
የ03 ስረ-ገደል ቀበሌ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ እና መካከለኛ ት/ቤት ዛሬ ነሃሴ 15/2018 ዓ.ም ሁሉም ባለድረሻ አካላት በተገኙበት የተማሪ ምዝገባ ስራዉን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በትምህርት ቤቱ ሲያስተባብሩ ያገኘናቸው የለገሂዳ ወረዳ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ እና የቀበሌው ምድብተኛ አመራር አቶ መስዑድ ሲራጅ ትምሀርት የሃገር ችግር መፍቻ ቁልፍ መሳሪያ ነው ያሉ ሲሆን፤ አሁን ላይ ትውልዱን በትምህርት መቅረጽ ካልተቻለ ቀጣይነት ያለው የሃገርን ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ አይቻልም ብለዋል፡፡
በዚህም ማንኛውም ህጻን የከብት ጭራ እንዳይከተል በሚል በዛሬው እለት የ2018/19 የትምህርት ዘመን ምዝገባ ከትምህርት አመራሩ እስከ ማህበረሰቡ የተደረገው ርብርብ ይበል የሚያሰኝ ነው ያሉት አቶ መስዑድ ለተግባሩ አስዋጽዖ ላደረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በምዝገባው የተደረገው እንቅስቃሴ መማር ማስተማሩን ለማስጀመር መደገም እንዳለበት መልእክታቸውን ያስተላለፉት የለገሂዳ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ ሱለይማን ከበዴ ናቸው፡፡
የትምህርት ቤቱ ኮሚቴ አቶ ሃብታሙ መኮንን እና የትምህርት ቤቱ የወመህ ሰብሳቢው አቶ ሙሃመድ ሰይድ በበኩላቸው የ2018/19 የትምህርት ዘመን ምዝገባ ለማሳካት ከወረዳ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች በጋራ በመሆን የቅድመ ዝግጅት ተግባር በአጭር ጊዜ በማከናወን ዛሬ ላይ ሁሉም ባለድረሻ አካላት በተገኙበት ተማሪዎችን በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ሲመዘገብ ያገኘነው የ8ኛ ክፍል ተማሪ አሊ ሙሃመድ ዛሬ ላይ ለመመዝገብ መምጣቱን ገልጾ፤ መስከረም አምስት ለሚጀመረው ትምህርት የመማሪያ ቁሳቁስ አሞልቸ ለመጀመር ዝግጁ ነኝ ብሏል፡፡
የስረ-ገደል አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ እና መካከለኛ ት/ቤት ርዕሰ መምህሯ ወ/ሮ ሰናይት ወንዶሰን በበኩሏ የ2018/19 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ለማከናወን ከልየታ ጀምሮ የቅድመ ዝግጀት ተግባር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እያከናወኑ መቆየታቸውን ገልጻ፤ ዛሬ ላይ በንቅናቄ የምዝገባ ሂደቱ እየተካሄደ ይገኛል ብላለች፡፡