04/09/2026
የዲላ ከተማ የመሬት አስተዳደር መምሪያ ለ205 የልማት ተነሺዎች ተለዋጭ መሬት አስረከበ
ዲላ፡ ነሐሴ 29/2018 ዓ.ም ምትክ ቦታው ከጪጩ ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ ከክልል ግብርና ቢሮ፣ በ20 እና በ30 ሜትር መንገድ ግንባታ እንዲሁም አባገዳ ሶንጎ ቦታ ተነሺ ለሆኑ ግለሰቦች የተሰጠ ነው።
ለልማት ተነሺዎቹ የመሬት ርክክቡ የተከናወነው ፍትሐዊ ሂደትን በተከተለ የዕጣ ስነ-ስርዓት ነው።
በወቅቱ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሬት አስተዳደር ቢሮ ም/ኃላፊ ኢንጂነር ፍሬው ፍሻለሁ ውድ የሆነውን የመሬት ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚገባ ገልፀዋል።
በዚህ ሂደት ለጋራ ጥቅም ሲባል ህዝቦች ከይዞታቸው ሊነሱ እንደሚችሉ ገልፀው፣ ተነሺዎች ግን ጥቅማቸው ተጠብቆ ሊነሱ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ይህንኑ ዲላ ከተማ አስተዳደር መተግበሩን የተናገሩት ም/ኃላፊው፣ እርምጃው ከክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ እውቅና ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
አክለውም ቦታውን በፍጥነት በማልማት ለኑሮ ምቹ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ(ዶ/ር) በበኩላቸው በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ከነዋሪዎች ጋር የጋራ መግባባት እና ግልፀኝነት በመፍጠር የሚከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
ዛሬ የተከናወነው የምትክ ቦታ ርክክብም የነዋሪውን ክብር በጠበቀና ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ ሁኔታ የተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህም የረጅም ጊዜ የልማት ተነሺዎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
ምትክ ቦታው 10 ሄክታር መሆኑን ጠቅሰው፣ ለ205 ልማት ተነሺዎች የተሰጠ ሲሆን የልማት ተነሺዎች ረጅም ጊዜ ታግሰው በመቆየታቸው ከንቲባው ምስጋና አቅርበዋል።
የዲላ ከተማ የመሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ምህረቱ አበበ እንደገለፁት ሀገር እየበለፀገ ሲሄድ ከተሞች እንደሚሰፉ ተናግረዋል።
በዚህ ሂደትም በዲላ ከተማ በሚከናወኑ የልማት ተግባራት ምክንያት ለተነሱ ነዋሪዎች መምሪያው ዛሬ የምትክ ቦታ መስጠቱን ገልጸዋል።
ምትክ የተሰጠበት ቦታ በግብርና ልማት ላይ የነበረ መሆኑን ጠቅሰው የመንገድ ከፈታ፣ መዝናኛ ስፍራዎችና የግብይት ቦታዎች ተሸንሸነውለት ለልማት ተነሺዎች ርክክብ ተከናውኗል።