31/12/2021
የጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ/ ለፌዴራል ጠበቆች በሙሉ
በፌዴራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 መሰረት የጠበቆች ማህበር የተቋቋመ ሲሆን፣ ማህበሩን ስራ ከማስጀመር አንፃር የማህበሩን የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራው ፍትሀ ሚኒስቴር መሆኑን በአዋጁ አንቀፅ 59 (1) ላይ ተመልክቷል፡፡
በዚሁ መሰረት ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር እና ከኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች የተካተቱባቸው አብይ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው የማህበሩን የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድና ማህበሩን ስራ ለማስጀመር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን በዚሁ አግባብ የማህበሩ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባዔው ጥር 8 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ 24 ቀበሌ በሚገኘው ኮከብ አዳራሽ ይካሂዳል፡፡
በአዋጁ አንቀፅ 52(3) መሰረት ማኅበሩ ሁሉንም የፈዴራል ጥብቅና ፍቃድ የተሰጣቸውን ጠበቆች እና የጥብቅና ድርጅቶች በአባልነት ያቀፈ በመሆኑ ማናቸውም የፌዴራል ጥብቅና ፈቃድ ያላችሁ ጠበቆችና የጥብቅና ድርጅቶች በጉባኤው ላይ እንድትሳተፉ ይህ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን፣ ጉባኤው የተሳታፊዎች ቁጥር ግምት ውስጥ ሳይገባ በጉባኤው ላይ በተገኙ አባላት የሚካሄድና የተለያዩ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍ በመሆኑና ይህም ውሳኔ በሁሉም የፌዴራል ጥበቅና ፈቃድ ባላቸው የህግ ባለሙያዎችና የጥብቅና ድርጀቶች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን በመሆኑ፣ ይህንን ተገንዝባችሁ በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ እንድትሳተፉ ፍትህ ሚኒስቴር ጥሪውን ያቀርባል::
በዚህ ጉባዔ ላይ የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ አባላት እንዲሁም የማህበሩ ፕሬዘዳንት እና ምክትል ፕሬዘዳንት የሚመረጡ ሲሆን ሌሎችም ክንውኖች የሚካሄዱ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር