03/08/2026
የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በንቃት ተሳተፈ
በጋምቤላ ክልል በጋምቤላ ወረዳ ቃርሚ ቀበሌ ዛሬ በተካሄደው ክልል አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አመራር እና አባላት በንቃት በመሳተፍ የድርሻቸውን ተወጥተዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ እና ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ ቾት ኒት ፓል የተመሩት የፖሊስ አባላት በሥፍራው በመገኘት ችግኞችን ተክለዋል።
በዚህ ወቅትም ምክትል ኮሚሽነሩ ለአመራሩና ለአባላቱ ባስተላለፉት መልእክት፤ መርሐ ግብሩ የደን ሽፋንን ከማሳደግ እና የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ባሻገር የአፈር ለምነትን በመጠበቅ የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር እና ለቀጣይ ትውልድ ዘላቂ አረንጓዴ አካባቢን ለማስተላለፍ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የፖሊስ አመራር እና አባላት በበኩላቸው፣ የችግኝ ተከላ ሥራው ችግኞችን በመትከል ብቻ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በቀጣይነት በመንከባከብ እና በማጽናት ሂደት ውስጥም የድርሻቸውን ንቁ ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።