02/09/2026
ፓርቲው የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት ይሠራል - አቶ ጌቱ ወዬሳ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2018 (ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሠራ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በክልሉ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
የፓርቲውን እሳቤዎች በተግባር በመተርጎም በየዘርፉ የተመዘገቡ ድሎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
በያዝነው አዲሱ የበጀት ዓመትም ፓርቲው ለሕዝብ የገባውን ቃል አልቆ የሚፈጽምበትና እንደ ሀገርና ክልል አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የሚከፈትበት እንዲሆን በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ እሳቤዎችና የፖለቲካ ፕሮግራሞች ወደ ተግባር በመቀየር የሕዝባችንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ነው ያነሱት።
እነኚህ ድሎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም በተለይ በአገልግሎት አሰጣጥ የሕዝብን እርካታ ማሳደግ እንዲሁም ብልሹ አሠራሮችን ከማስወገድ አንጻር በልዩ ትኩረት መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በፓርቲና በመንግሥት የተቀናጀ አመራር የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት፣ ገበያን የማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የፓርቲ አደረጃጀቶችና አባላት በዘርፉ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ በማሳሰብ፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ሥራዎችን በማላቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ልመናንና ተረጂነትን ለመቀነስ ይሠራል ሲሉ አብራርተዋል።
"አዲሱ በጀት ዓመት ሕዝባችንን ይበልጥ የምናገለግልበት፣ ክልሉን የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ጉዟችንን የምናረጋግጥበት እንዲሆን ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል።
የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዶች በተሻለ አፈጻጸም እንዲተገበሩ ሁሉም የፓርቲ መዋቅሮችና የመንግሥት ተቋማት በቅንጅት፣ በተጠያቂነትና በውጤት ተኮር አሠራር ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የታቀዱ ግቦችን ለማሳካት በየደረጃው የሚገኘው አመራር በቁርጠኝነትና በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መሥራት እንደሚገባውም አጽንኦት ሰጥተዋል።