Harari Regional Transport and Road Development Bureau

Harari Regional Transport and Road Development Bureau ይህ የሐረሪ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ትክክለኛው የፌስቡክ ገፅ ነው ።

በሐረሪ ትራንስፖርትእና መንገድ ልማት ቢሮ የመሶብ ቤተሰብ አባላት የሐረር መቄዶንያ አረጋውያን መጦሪያ ማዕከልን ጎበኙ።ሐረር፣ ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም. — በሐ/ት/መ/ል/ቢሮ የአሽከርካሪና ...
05/09/2026

በሐረሪ ትራንስፖርትእና መንገድ ልማት ቢሮ የመሶብ ቤተሰብ አባላት የሐረር መቄዶንያ አረጋውያን መጦሪያ ማዕከልን ጎበኙ።

ሐረር፣ ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም. — በሐ/ት/መ/ል/ቢሮ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት የመሶብ ቤተሰብ አባላት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣትና ለአረጋውያን ያላቸውን ክብርና አክብሮት ለመግለጽ በሐረር የሚገኘውን መቄዶንያ አረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ጎበኙ።
የመሶብ ቤተሰብ አባላቱ በጉብኝታቸው ወቅት ከማዕከሉ አረጋውያን ጋር ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ የደስታና የአጋርነት ስሜት የፈጠሩ ሲሆን፣ ማዕከሉ ለአረጋውያኑ የሚሰጠውን እንክብካቤና አገልግሎትም ተመልክተዋል።

በተጨማሪም ለአረጋውያኑ ያላቸውን አጋርነትና ድጋፍ በተግባር ለማሳየት የንጽህና መጠበቂያ የገላና የልብስ ሳሙናዎችን በድምሩ 3,500 ብር የሚገመት ድጋፍ አበርክተዋል።

የመሶብ ቤተሰብ ሰብሳቢ አቶ ጃዕፈር ኢብራሒም በጉብኝቱ ወቅት በሰጡት አስተያየት፣ “ይህ ጉብኝት ማኅበራዊ ግዴታችንን ከመወጣት ባለፈ፣ ለአገር ባለውለታ የሆኑትን አረጋውያን ለመንከባከብና ለማስደሰት ትልቅ ዕድል ፈጥሮልናል” ብለዋል።

በማዕከሉ የሚገኙ አረጋውያንም ለተደረገላቸው ሰብአዊ ድጋፍና እንክብካቤ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል። እንዲህ ያሉ የማኅበራዊ ኃላፊነት ተግባራት አረጋውያን የሚሰማቸውን ተስፋና ደስታ ከማጠናከር ባለፈ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የመረዳዳትና የአጋርነት ባህልን ለማጎልበት የሚያበረክቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመሶብ ቤተሰብ አባላት በቀጣይም መሰል የማኅበራዊ ድጋፍና በጎ ተግባራትን በማጠናከር ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።
በሐ/ት/መ/ል/ቢሮ

የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት

የመሶብ ቤተሰብ አባላት

ሐረር

03/09/2026
የሐረሪ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ከ190ሺህ ብር በላይ የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።ሐረር፣ ነሐሴ 28/ 2018 ዓ.ም. – የሐረሪ ትራን...
03/09/2026

የሐረሪ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ከ190ሺህ ብር በላይ የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ሐረር፣ ነሐሴ 28/ 2018 ዓ.ም. – የሐረሪ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ከ100 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ የተደረገው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የቢሮው ሠራተኞች ፣ ለተስፋ ብርሃን ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ ማህበር፣ ለአካል ጉዳተኞች ማህበር እንዲሁም ለቀላድ አንባ ቁጥር 2 ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነው።

የቢሮው ም/ቢሮ ሐላፊ ኢ/ር ፈትሒ ቶውፊቅ እንደገለጹት፣ የመደጋገፍ ባህልን ማጠናከር በማህበረሰብ ውስጥ መተሳሰብንና አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ ለሌሎች እገዛ ማድረግ ለሚያደርገው አካልም ልዩ እርካታ የሚሰጥ ነው።

“የተቸገሩትን መደገፍ የሁላችንም ሀላፊነት ነው፤ በተለይም ትውልዱን በትምህርት ለማገዝ የምናደርገው ድጋፍ የሚያስገኘው ጥቅም ዘላቂ ነው” በማለት ገልጸዋል።

ቢሮው ከዚህ በፊትም በተለያዩ የበጎ ፈቃድና የድጋፍ ሥራዎች በንቃት ሲሳተፍ መቆየቱን የጠቆሙት ኢ/ር ፈትሒ፣ ይህም የመደጋገፍ ባህልን በማጠናከር ማህበራዊ ኃላፊነትን በተግባር ለመወጣት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፉን የተቀበሉ አካላት በበኩላቸው፣ በርካታ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች የትምህርት ቁሳቁስ ለመግዛት በሚቸገሩበት ወቅት የተደረገው ድጋፍ ለተማሪዎችና ለቤተሰቦቻቸው ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ተግባር መሆኑን ገልጸው፣ ቢሮውን ከልብ አመስግነዋል።

የቢሮው ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ይርጋለም በለጠ በበኩላቸው ድጋፉ የመማር ፍላጎት እያላቸው የመማሪያ ቁሳቁስ በማጣት ከትምህርት ገበታቸው ለሚቀሩ ተማሪዎች ትልቅ እረፍትን ይሰጣል ከአሉ በኋላ ቢሮው አቅም በፈቀደ ለወገን ለመድረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

“ አክለውም ይህ ድጋፍ በእጅጉ የሚያስፈልጋቸውን ቤተሰቦችና ተማሪዎች ያግዛል። በተለይ የትምህርት ቁሳቁስ መግዛት ለማይችሉ ቤተሰቦች እፎይታ የሚሰጥ የተቀደሰ ተግባር ነው ብለዋል።

የተደረገው ድጋፍ የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ከማጎልበት ባለፈ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የመደጋገፍ፣ የመተሳሰብና የበጎ ተግባር ባህልን ለማጠናከር የሚያበረክት መሆኑ ተገልጿል።

📢✍️ ሦስት ወሳኝ የመንገድ ደህንነት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ                       ተካሄደ➖🟰➖🟰➖🟰➖🟰➖🟰➖🚦👥 ሐረር፣ ነሐሴ 28/2018 — በሐረሪ ...
03/09/2026

📢✍️ ሦስት ወሳኝ የመንገድ ደህንነት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ
ተካሄደ
➖🟰➖🟰➖🟰➖🟰➖🟰➖
🚦👥 ሐረር፣ ነሐሴ 28/2018 — በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት በመንገድ ደህንነትና በትራንስፖርት ዘርፉ የተሻለ የአሠራር ሥርዓት ለመፍጠርና የትራፊክ አደጋን በተግባር ለመቀነስ በመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎትና በቢሮ ቅንጅት የተዘጋጁ ሦስት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሄደ።

መድረኩ በመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ከሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ጋር በቅንጅት የተዘጋጀ ሲሆን፣ ዓላማውም ረቂቅ መመሪያዎቹ በተግባር የሚፈጸሙ፣ ግልጽና ውጤታማ እንዲሆኑ ከተለያዩ ዘርፎች የሚመጡ ሙያዊ ግብዓቶችን ማሰባሰብ ነው።

በመድረኩ ላይ የትራፊክ ሕግ ማስከበር ተቆጣጣሪዎች፣ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች፣ የትራፊክ ፖሊስ አባላት፣ የትምህርትና የጤና ዘርፍ ባለሙያዎች፣ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛና የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት ተወካዮች፣ የሕዝብና የጭነት ትራንስፖርት ማህበራት እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ፈትሂ ተውፊቅ ፣ የመንገድ ደህንነት ሥራ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ሳይሆን የሁሉም ተቋማትና የማህበረሰቡ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም የመንገድ ደህንነት ሥራ ከአደጋ በኋላ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አደጋ ከመከሰቱ በፊት በመከላከል ላይ ሊያተኩር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

“የምንፈልገው የሰነዶችን ብዛት ማሳደግ ሳይሆን በመንገድ ላይ የሚታይ ለውጥ ነው” ያሉት ኢንጂነር ፈትሂ፣ ረቂቅ መመሪያዎቹ በወረቀት ላይ ብቻ የሚቀሩ ሳይሆኑ በተግባር የሚውሉና የሰው ሕይወትን የሚታደጉ መሆን እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተዋል።

በመድረኩ የሚወያዩባቸው ረቂቅ መመሪያዎች፦
🔹 በትምህርት ቤቶች አካባቢ የትራፊክ ደህንነትን ማስጠበቅ፣

🔹 በሚያነቃቁና በሚያደነዝዙ ነገሮች ተጽዕኖ ሥር ሆኖ ተሽከርካሪ ማሽከርከርን መቆጣጠር፣

🔹 የባለሞተር ተሽከርካሪዎችን የፍጥነት ወሰን አተገባበር መቆጣጠር ናቸው።

እንደ ኢንጂነር ፈትሂ ገለጻ፣ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ለሚደረገው የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥር ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል፤ ምክንያቱም ሕፃናት በመንገድ ላይ በሚፈጠር የትራፊክ ስህተት ሕይወታቸውን ሊያጡ አይገባም።

በተመሳሳይም በአልኮልና በሌሎች አእምሮን በሚያደነዝዙ ወይም በሚያነቃቁ ነገሮች ተጽዕኖ ሥር ሆኖ ማሽከርከር ለአሽከርካሪው ብቻ ሳይሆን ለተሳፋሪዎችና ለሌሎች የመንገድ ተጠቃሚዎችም ከፍተኛ አደጋ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፍጥነት ወሰንን በተመለከተም፣ ፍጥነት የጉዞ ጊዜን ሊያሳጥር ቢችልም የጠፋ ሕይወትን መመለስ እንደማይችል በመጥቀስ፣ የፍጥነት ወሰን በግልጽ እንዲታወቅ፣ እንዲከበርና በተግባርም በተከታታይ እንዲቆጣጠር ጥሪ አቅርበዋል።

ኢንጂነር ፈትሂ በመጨረሻም የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ ተቋማት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸው፣ በዚህ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ የሚቀርቡ ሙያዊ ሀሳቦችና ልምዶች የረቂቅ መመሪያዎቹን ተግባራዊነት በማጠናከር በዘርፉ የሚፈለገውን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ከትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ይህን የመሰለ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ማዘጋጀቱ ተመስግኗል።

“የመንገድ ደህንነት የአንድ ተቋም ሥራ አይደለም፤ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ነው” በሚል መልዕክት፣ ከዚህ በኋላም መሰል የጋራ ውይይትና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ቢሮው ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ተገልጿል።

በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ከፌዴራል የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ጋር በቅንጅት የተዘገጀ
ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም
ሐረር

02/09/2026

የጳጉሜ ቀናት ስያሜዎች

ጳጉሜን 1 - የእመርታ ቀን፣
ጳጉሜን 2 - የማንሰራራት ቀን፣
ጳጉሜን 3 - የፅናት ቀን፣
ጳጉሜን 4- የኅብር ቀን እና
ጳጉሜን 5 - የነገ ቀን

መንገዶች ለሰዎች፣ ጤና ለማህበረሰብ!    127ኛው ዙር የሞተር አልባ ስፖርታዊና ማህበራዊ      እንቅስቃሴ በሐረሪ ክልል በደመቀ ሁኔታ ተካሄደ➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም.በሐ...
30/08/2026

መንገዶች ለሰዎች፣ ጤና ለማህበረሰብ!
127ኛው ዙር የሞተር አልባ ስፖርታዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ በሐረሪ ክልል በደመቀ ሁኔታ ተካሄደ
➖➖➖➖➖➖➖➖➖➖

ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም.
በሐረሪ ክልል እግረኞችና ብስክሌተኞች በአስተማማኝ፣ ምቹና ሰው-ተኮር በሆነ የመንገድ አጠቃቀም እንዲንቀሳቀሱ፣ ንቁ መጓጓዣን ለማስፋፋትና ጤናማ አኗኗርን ለማበረታታት በየሳምንቱ የሚካሄደው የሞተር አልባ ስፖርታዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ በሰፊ ተሳትፎ ቀጥሏል።

በዚህ መሠረት በዕለቱ በሸንኮር ወረዳ “ሰላም ጎዳና” 127ኛው ዙር የሞተር አልባ እንቅስቃሴ ሲካሄድ፣ በሐኪም ወረዳ ከ4ኛ ቶታል እስከ ኦጋዴን አንበሳ 40ኛው ዙር በተመሳሳይ መልኩ ተካሂዷል።

እግር ጉዞና ብስክሌት፣ ከስፖርት ባሻገር የጤናና የደህንነት መልዕክት!
በእንቅስቃሴው ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች በእግር ጉዞና በብስክሌት በመሳተፍ ለጤናማ አኗኗር፣ ለንቁ መጓጓዣና ለአስተማማኝ የመንገድ አጠቃቀም ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል። የተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎም ዝግጅቱን በደስታ፣ በአንድነትና በመንፈስ የተሞላ አድርጎታል።

የሞተር አልባ እንቅስቃሴው ሰዎችን ለአካል ብቃት ከማነሳሳት ባሻገር፣ እግረኞችና ብስክሌተኞችም የመንገድ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን በማስገንዘብ የጋራ የመንገድ ደህንነት ባህልን ለማጠናከር ጠንካራ መልዕክት አስተላልፏል።

ይህ መደበኛ ሳምንታዊ እንቅስቃሴ የሕብረተሰቡን የአካል ብቃትና ጤና ከማሻሻል ባሻገር፣ የንቁ መጓጓዣ ባህልን ለማጎልበት፣ ለእግረኞችና ለብስክሌተኞች የተሻለ የመንገድ አካባቢ እንዲፈጠር ለማበረታታት እና የመንገድ ደህንነት ግንዛቤን በሕብረተሰቡ ውስጥ ለማስረጽ የሚጫወተውን ሚና እያጠናከረ ይገኛል።

ጤናማ ሰው፣ ንቁ ማህበረሰብ፣ አስተማማኝ መንገድ!
“መንገድ ለሰው ነው!”
የሐረሪ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ

የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት

27/08/2026
የትራፊክ መብራት ጥገና ተከናወነበሐረር ከተማ በልዩ ስሙ አራተኛ መስኪድ አካባቢ ለትራፊክ ፍሰት መቆጣጠርና ለመንገድ ተጠቃሚዎች ደህንነት ሲያገለግል የነበረው የትራፊክ መብራት በተከሰተበት ብ...
27/08/2026

የትራፊክ መብራት ጥገና ተከናወነ

በሐረር ከተማ በልዩ ስሙ አራተኛ መስኪድ አካባቢ ለትራፊክ ፍሰት መቆጣጠርና ለመንገድ ተጠቃሚዎች ደህንነት ሲያገለግል የነበረው የትራፊክ መብራት በተከሰተበት ብልሽት ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ከአገልግሎት ውጭ መሆኑ ይታወሳል።

የትራፊክ መብራት በመንገድ ላይ የተሽከርካሪና የእግረኛ ፍሰትን በሥርዓት ለመምራት፣ በመገናኛ መንገዶች የሚፈጠርን መጨናነቅ ለመቀነስ እና የመንገድ ተጠቃሚዎች የሚያሳልፉትን ጊዜና ድካም ለመቀነስ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በተለይም የትራፊክ ፍሰቱ በበዛባቸው መገናኛዎች ተገቢው የመብራት ምልክት መኖሩ እያንዳንዱ የመንገድ ተጠቃሚ ተራውን እንዲጠብቅና በተገቢው ጊዜ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የተደራጀ የትራፊክ እንቅስቃሴን ያረጋግጣል።

በተጨማሪም የትራፊክ መብራት በትክክል መሥራቱ በመገናኛ መንገዶች የሚከሰቱ የተሽከርካሪ ግጭቶችን፣ የእግረኞችን አደጋ እና ከአደጋ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የሰውና የንብረት ጉዳቶችን ለመቀነስ ያግዛል።

ስለሆነም ብልሽት ያጋጠመው የትራፊክ መብራት በፍጥነት መጠገኑ የትራፊክ ሥርዓቱን ወደ ተረጋጋ አሠራር ለመመለስ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የትራፊክ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችን ጤንነት በቀጣይነት በመከታተል፣ ብልሽት ወይም ችግር ሲያጋጥምም በኃላፊነቱ መሠረት በፍጥነት ለማስጠገንና ወደ አገልግሎት ለመመለስ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል። ይህም በከተማዋ የተደራጀ፣ የተሳለጠና ደህንነቱ የተጠበቀ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር የዳይሬክቶሬቱን ቁርጠኝነት ያሳያል።

ይህ ጥገና የትራፊክ ፍሰቱን ወደ ተሻለ ሥርዓት ከማስመለስ ባለፈ፣ አሽከርካሪዎች ከአላስፈላጊ መጠባበቅና መጨናነቅ እንዲቀነስላቸው፣ እግረኞችም መንገዱን በተገቢው ጊዜና ሁኔታ እንዲሻገሩ ከማገዝ ባለፈ የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ ያግዛል።

በመንገድ ላይ የሚታየው ትክክለኛ ምልክት የትራፊክን ሥርዓት ያስጠብቃል፤ የተጠበቀ የትራፊክ ሥርዓት ደግሞ ሕይወትን ያድናል!
የትራፊክ መብራቶችን በወቅቱ መከታተል፣ ብልሽት ሲያጋጥም በፍጥነት መጠገን እና በየጊዜው ጥገና ማድረግ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ለተሽከርካሪና ለእግረኛ ምቹ የከተማ ትራፊክ ሥርዓት መገንባት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት ነው።

የትራፊክ አደጋን በጋራ እንከላከል!

በሐረሪ ክልላዊ መንግስት ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዳይሮክቶሬት
ነሐሴ 21/2018
ሐረር

የትራፊክ አደጋን በትብብርና በቅንጅት ለመቀነስ የሥራ ግምገማና ውይይት ተካሄደ።   ============ ሐረር | ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም.የትራፊክ አደጋን በተጨባጭ ለመቀነስ፣ የአደጋ መከላ...
24/08/2026

የትራፊክ አደጋን በትብብርና በቅንጅት ለመቀነስ የሥራ ግምገማና ውይይት ተካሄደ።
============
ሐረር | ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም.
የትራፊክ አደጋን በተጨባጭ ለመቀነስ፣ የአደጋ መከላከልና መቆጣጠር አቅምን ለማጠናከር እንዲሁም በመንገድ ደህንነት ሥራ በሚሳተፉ ተቋማት መካከል የተቀናጀና የተናበበ አሠራርን ለማጠናከር ያለመ የሥራ ግምገማና የውይይት መድረክ ተካሄደ።

መድረኩ በሐረሪ ክልላዊ መንግስት ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥር ባለሙያዎችና የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ዲቪዚዮን አባላትን በማሳተፍ ተካሂዷል።

በመድረኩ የትራፊክ አደጋ መረጃዎች፣ የቁጥጥርና የሕግ ማስከበር ሥራዎች እንዲሁም በተቋማቱ መካከል ያለው የትብብር አሠራር በጥልቀት ተገምግሟል። በግምገማውም የተገኙ ጥንካሬዎችን ማስፋት፣ ያሉ የአሠራር ክፍተቶችን መለየትና በጋራ መፍታት የሚያስችሉ የሥራ አቅጣጫዎች ተነስተዋል።

የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ፈትሂ ተውፊቅ በላኩት መልዕክት፣ የሐረር ከተማን ፈጣን እድገትና የመንገድ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ያገናዘበ ዘመናዊና ውጤታማ የትራፊክ ማኔጅመንት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። የወጡ የመንገድ ደህንነት ሕጎችና መመሪያዎች በተግባር እንዲውሉ፣ የሕግ ማስከበር፣ የሕዝብ ግንዛቤ፣ የቁጥጥርና የድህረ-አደጋ ምላሽ ሥራዎችም በተቀናጀ ሥርዓት እንዲመሩ ጠይቀዋል።

የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ነገራ ዱፌራ በበኩላቸው፣ የትራፊክ አደጋን መቀነስ የአንድ ተቋም ሥራ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል። ተቋማት በተሰጣቸው ሕጋዊ ሥልጣንና ኃላፊነት በንቃት መሥራት፣ መረጃን በወቅቱ መለዋወጥና በጋራ መተንተን፣ የአደጋ መንስኤዎችን ቀድሞ በመለየት የመከላከያ ሥራን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዳይሬክተር ኢንጂነር በቀለ አንጊያ የትራፊክ አደጋ መከላከል የሚቻለው ተቋማት በተናጠል በሚያከናውኑት ሥራ ሳይሆን በመደመር፣ በመተባበርና በመናበብ እንደ አንድ አካል በመንቀሳቀስ መሆኑን አስረድተዋል። በተበታተነ አሠራር የሚፈጠሩ የሥራ መደራረቦችና ክፍተቶች ውጤታማነትን እንደሚቀንሱ ጠቁመው፣ የአደጋ መረጃዎችን በጋራ በመተንተን የችግሩን ምንጭ መለየት፣ ቅድመ-መከላከያ ሥራዎችን ማጠናከርና የተለዩ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የትራፊክ ዲቪዚዮን ኃላፊ ኮማንደር ሙክታር አብዶሽ በበኩላቸው፣ በተቋማት መካከል በቂ መናበብ ባለመኖሩ የሚታዩ የአሠራር ክፍተቶችን በማንሳት፣ እነዚህ ክፍተቶች በቀጣይ የጋራ ውይይትና የመፍትሔ ሥራ እንዲታረሙ ጠይቀዋል። የትራፊክ ደህንነት ሥራም በተወሰኑ ባለሙያዎች ብቻ ሳይወሰን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሌሎች ክፍሎች በማሳተፍ ቀጣይነት ባለው የጋራ አሠራር መመራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የትራፊክና የመንገድ ደህንነት ሕጎችን በተግባር ስለማስፈጸም፣ የተበላሹ የትራፊክ ምልክቶችንና ማመላከቻዎችን በፍጥነት ስለማስተካከል፣ የመንገድ ተጠቃሚዎችን በአግባቡ ስለማስተናገድ፣ የሥራ ቦታ ዲሲፕሊንና ሙያዊ አመለካከትን ስለማጠናከር እንዲሁም ተከታታይ የጋራ የሥራ ዕቅድ ስለማውጣትና አፈጻጸሙን ስለመገምገም ሰፊ ሐሳብ ተለዋውጧል።

በመጨረሻም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በተናጠል የሚደረግ ጥረት በቂ እንዳልሆነ በመግባባት፣ የሁለቱ ተቋማት የመረጃ ልውውጥ፣ የጋራ ቁጥጥር፣ የሕግ ማስከበር፣ የግንዛቤ ሥራ፣ የአደጋ ትንተናና የድህረ-አደጋ ምላሽ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን የጋራ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመደመር፣ በመተባበርና በመናበብ ሕይወትን እንጠብቃለን፤ የትራፊክ አደጋንም እንቀንሳለን!

የሐረሪ ክልላዊ መንግስት
ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት

“በክረምት በጎፈቃድ አገርህን እወቅ” ፕሮግራም፦ የጀጎል ታሪካዊ ስፍራዎች ጉብኝት ተካሄደሐረር፣ ነሐሴ 17 ቀን 2018 ዓ.ም.በሐረሪ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የህዝብና ጭነት ...
23/08/2026

“በክረምት በጎፈቃድ አገርህን እወቅ” ፕሮግራም፦ የጀጎል ታሪካዊ ስፍራዎች ጉብኝት ተካሄደ

ሐረር፣ ነሐሴ 17 ቀን 2018 ዓ.ም.

በሐረሪ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የህዝብና ጭነት ትራንስፖርት ዳይሬክቶሬት ያዘጋጀው “አገርህን እወቅ” ልዩ የጉብኝት ፕሮግራም በሐረር ከተማ የሚገኙ የጀጎል ታሪካዊ ስፍራዎችንና በውስጡ የሚገኙ የባህል፣ የሃይማኖትና የታሪክ ቅርሶችን በመጎብኘት ተካሄደ።

ጉብኝቱ በቢሮው ከታቀዱት የክረምት ፕሮግራም ተግባራት መካከል አንዱ ሲሆን፣ ለችግረኛ ቤተሰቦች የመማሪያ ደብተር ማሰባሰብ፣ የደም ልገሳ፣ አቅም ለሌላቸው ዜጎች ነፃ ትራንስፖርት ማመቻቸት፣ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ እና ለበጎ ፈቃደኛ አገልጋዮች ልዩ የክህሎት ሥልጠና መስጠትን የመሳሰሉ ተግባራትንም ያካተተ ነው።

በዕለቱ በተካሄደው ጉብኝት የዳይሬክቶሬቱ ሠራተኞች፣ የመናኸሪያ ሠራተኞችና የማኅበራት አመራሮች፣ የባጃጅ ታክሲ ባለንብረቶች ማኅበራት አመራሮች እንዲሁም የቢሮው የክረምት ሥራዎች አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ተሳትፈዋል።

ተሳታፊዎቹ በጀጎል ግንብ ውስጥ በሚገኙ ጠባብና ታሪካዊ መንገዶች እየተዘዋወሩ፣ በሐረሪ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን በተመደበ ባለሙያ አስጎብኚ ስለ ታሪካዊ ቅርሶቹ፣ ስለ ባህላዊ እሴቶቹና ስለ ከተማዋ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ ዝርዝር ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል። ተሳታፊዎቹም በጉብኝቱ ወቅት ጥያቄዎችን በማቅረብ በርካታ አዳዲስ እውቀቶችን አግኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ሀሳባቸውን የገለጹ ተሳታፊዎች፣ “በሐረር ተወልደን ያደግን በመሆናችን የከተማችንን ታሪካዊ ስፍራዎች በበቂ ሁኔታ እናውቃለን ብለን ነበር፤ ነገር ግን በጉብኝቱ ወቅት የተሰጠን ማብራሪያ በርካታ ያላወቅናቸውን ታሪኮችና ቅርሶች እንድናውቅ አድርጎናል” በማለት አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

በተጨማሪም ከመላው ዓለም ወደ ሐረር የሚመጡ ጎብኚዎች ስለ ከተማዋ ታሪክና ቅርስ በስፋት ሲያጠኑና ሲያስተዋውቁ መታየቱን በመጥቀስ፣ የክልሉ ነዋሪዎችም ታሪካዊ ቅርሶቻቸውን በተደጋጋሚ መጎብኘት፣ ማወቅና ለሌሎች ማስተዋወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የህዝብና ጭነት ትራንስፖርት ዳይሬክተሩ፣ የቡድን መሪዎችና የማኅበራት አመራሮችም እንደገለጹት፣ የጀጎልን የመሳሰሉ ውድ ታሪካዊ ሀብቶች ለትውልድ ማስተዋወቅና ማስጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ እንደዚህ ያሉ የ“አገርህን እወቅ” ፕሮግራሞች በቀጣይም በዕቅድ ተይዘው መቀጠል ይገባቸዋል።

የጉብኝቱ መርሃ ግብር እንዲሳካ ያመቻቹት የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኢ/ር ፈትሒ ቶውፊቅ፣ የሐረሪ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽነር ሳሚ አብዱልዋሲ፣ የህዝብና ጭነት ትራንስፖርት ዳይሬክቶሬት አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም የክረምት ሥራዎች ኮሚቴ አባላት በመሆን የጉብኝቱን ስኬት አስተባብረዋል።

በመጨረሻም ጥሪውን አክብረው በጉብኝቱ ላይ ለተሳተፉ የመናኸሪያ ሠራተኞች፣ የአውራጅ ጫኝና የተራ አስከባሪ ማኅበራት አመራሮች፣ የባጃጅ ታክሲ ባለንብረቶች ማኅበራት አመራሮችና ሌሎችም ተሳታፊዎች የሐረሪ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምስጋናውን አቅርቦ፣ የዕለቱ የ“አገርህን እወቅ” የጉብኝት መርሃ ግብር በስኬት ተጠናቋል።

Address

Aboker
Harar
302

Telephone

+251256669239

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Harari Regional Transport and Road Development Bureau posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share