02/09/2026
ምክር ቤቱ የዞኑን የምክር ቤት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ
የሀዲያ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 14ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 27ኛ መደበኛ ጉባኤ በሁለተኛ ቀን ውሎው የዞኑን የ2018 በጀት ዓመት የምክር ቤት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና የ2019 ዕቅድ ለምክር ቤቱ ቀርበው በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
ነሐሴ 27/2019 ዓ.ም (ሀዲያ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ)-ሆሳዕና
የበጀት ዓመቱን የምክር ቤት ዕቅድ አፈፃፀም ርፖርት ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ክብርት ወ/ሮ አለሙነሽ ክፍሌ ባለፈው በጀት ዓመት ምክር ቤቶች የመንግሥትና የህዝብ ሀብት በአግባቡ በሥራ ላይ ማዋላቸውን የመከታተል ሥራ ማከናወኑን በሪፖርቱ አመላክተዋል ።
በተያዘው በጀት ዓመት ምክር ቤቶች ባለፈው ዓመት በዕቅድ አፈፃፀም ላይ የተስተዋሉ የመልካም አስተዳደርና በአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራም በሪፖርቱ ተብራርቷል።
ምክር ቤቶች የህዝብ ያለአግባብ የምባክነውን ሀብት የማስመለስ ሥራ በትኩረት ይሠራል ያሉት ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ተቋሙ የመንግስትን መመሪያዎችና ደንቦችን ለህዝብ የማድረስና የማስገንዘብ ኃላፊነት እንደሚወጣ አስረድተዋል።
የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ እቴነሽ ሙሉጌታ
ባለፈው በጀት ዓመት ምክር ቤቱ እናቶችንና ህፃናትን በበጎ አገልግሎት ሥራ የመደገፍና የማጠናከር ሥራ ማከናወኑን አብራርተዋል።
ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማት እንደመጣ ከተፈለገ ምክር ቤቶችን ማጠናከርና መደገፍ እንደሚገባ ዋና አፈ-ጉባኤዋ ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ በቀረበው የምክር ቤት ዕቅድ አፈፃፀምና በተያዘው የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ላይ አስተያየቶችና ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።
በደገለ በምቦሬ