24/08/2026
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ከመንግስት ጥረት ባሻገር የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
ሆሳዕና፤ ነሐሴ 18/12/2018 በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ሕጋዊ የውጭ አገር የሥራ ስምሪት "የዉጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አቋራጭ መንገድ የለዉም" በሚል መሪ ቃል ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩ በሀዲያ ዞን ኢንተርፕራይዝና ሥራ ዕድል ፈጠራ መምሪያ፣ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያና በቴክኒክና ትምህርት ስልጠና መምሪያ ቅንጅት መዘጋጀቱም ተመላክቷል።
ለንቅናቄዉ መድረክ ዉይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ በአቶ አብርሃም ባቦሬ እና በአቶ አዲሴ አዉቶ ቀርቦ ዉይይት ተካሂዷል።
የሀዲያ ዞን ኢንተርፕራይዝና ሥራ ዕድል ፈጠራ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም ባቦሬ በወቅቱ እንደተናገሩት፥ ወጣቶች በአካባቢያቸዉ እንዲረጋጉ መንግስት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እስካ ቀበሌ ድረስ በርካታ ሥራዎችን እየሰረ ይገኛል ብለዋል።
አክለዉም በበጀት ዓመቱ ከ7 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ከክልል መንግስት መዉረዱን ጠቁመዉ፥ ይህም ገንዘብ በየመዋቅሩ ማህበር ተደራጅተዉና ቢዝነስ ፕላን አዘጋጅተዉ ለተዘጋጁ ወጣቶች መሰራጨቱን ያሳወቁት አቶ አብርሃም፥
በዘርፉ መንግስት በተቋም ግንባታ ላይ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዉ፤ ይህ ማለትም በሰዉ ሀይልና በመረጀ ተደራሽነትና ማዘመን ላይ ጠንከራ ስራ መስራት ነዉ ብለዉ፥
ይህ መድረክ በተዋረድ በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች መካሄድ እንዳለበትና ሪፖርት ለሚመለከታቸዉ አካላት በተቀመጠለት መርሃ ግብር መሰረት መድረስ አለበት ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሀዲያ ዞን ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሴ አውቶ በበኩላቸዉ፤ የመድረኩ ዋና ትኩረት ግንዛቤ የመፍጠር፣ ስልጠና የመስጠትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ናቸዉ ብለዋል።
ትልቁ የመንግስት ግብ ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለሀገሩ የሚጠቅም ዜጋ መፍጠር ነዉ ያሉት አቶ አዲሴ አዉቶ፥
ለዚህም በሀይማኖት ተቋማት፣ በዕድሮችና መሰል ማህበራዊ መድረኮች ላይ በማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዉጭ ሀገር እና ለሀገር ዉስጥ የሥራ ስምሪት ለሚፈልጉ ዜጎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጀምሮ በየደረጀዉ ያሉ ባለድርሻ የሆኑ ተቋማት በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደምገኙ ገልፀዉ፥ ዘርፉ ለተገልጋዮች የተሳለጠ አገልግሎት እንዲሰጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።