03/09/2026
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቱን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጥምረት እየሠራ እንደሆነ አስታወቀ
#ጅግጅጋ:-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እና ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያስችለውን ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጥምረት እየተገበረ መሆኑን ገልፆአል።
የተቋሙ የውስጥ የኃይል ማመንጨት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን እንደገለጹት፣ አሰራሩን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል በጥናት የተደገፈ የኢንቨስትመንት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
አቶ ኤፍሬም አክለው እንዳብራሩት፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይን ለማሳካት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ በመሆኑ ተቋማቸው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
የኃይል አቅርቦትን ማዲጂታላይዝ ማድረግ የአገልግሎት ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ በዘርፉ አጠቃላይ እድገት ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የሀገሪቱ ኃይል የማመንጨት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የጠቆሙት ኃላፊው፣ የዲጂታል ስርዓቱን በመተግበር አገልግሎቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ልዩ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል።