የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት/ Supreme Court of Amhara Region

  • Home
  • Ethiopia
  • Kebele 13
  • የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት/ Supreme Court of Amhara Region

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት/ Supreme Court of Amhara Region ራዕያችን በአገር አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት የሆነ ፍርድ ቤት መገንባት ነው ! / Our vision is excelling to become a model judiciary in Ethiopia !

06/07/2026

“የፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር መስራት ያስፈልጋል” ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው-የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት ለማሻሻል በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በተፈራረመበት ወቅት Amhara Media Corporation/ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያጠናቀረው ዘገባ

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በትብብር በመስራት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማጠናከር ስምምነት ተፈራረሙባሕር ዳር፣ ሰኔ 27/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)የአማ...
04/07/2026

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በትብብር በመስራት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማጠናከር ስምምነት ተፈራረሙ

ባሕር ዳር፣ ሰኔ 27/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በክልሉ የዳኝነትና የፍትሕ ሥርዓትን ለማዘመን፣ ተደራሽና ውጤታማ ለማድረግ በተለያዩ የትብብር መስኮች በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።

በስምምነቱ ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ወቅትም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በትምህርት፣ በምርምር፣ በማሕበረሰብ አገልግሎት እና በሌሎች የአጋርነት ሥራዎች ያስመዘገበው ስኬት ከፍተኛ በመሆኑ ከተቋሙ ጋር የሚደረገው ትብብር የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት ለማሻሻል ወሳኝ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ ፍርድ ቤቱ ፍትሕን ተደራሽ፣ ፈጣንና ዘመናዊ ለማድረግ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፣ በዚህም የአማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ የባህል ፍርድ ቤቶችን ማስፋፋት፣ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ማሻሻል፣ የጠበቆችን አቅም መገንባት፣ የፍርድ ቤት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግና የሰው ኃይል ልማትን ማጠናከር ዋና ትኩረቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የተጀመሩ ሥራዎችን በተሻለ ውጤት ለማሳካት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በአቅም ግንባታ፣ በአጫጭርና ረጅም ጊዜ ስልጠናዎች፣ በሀገር በቀል የፍትሕ ሥርዓቶች ማጠናከር፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ልማት፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም አለም አቀፍ ኮንፈረንሶችንና የጋራ መድረኮች በማካሄድ በስፋት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ከ350 በላይ የትምህርት መርሃ ግብሮች እንዳሉት ጠቅሰው፣ በተለይም የሕግ ትምህርት ቤቱ በፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ፣ በነጻ የሕግ ድጋፍ፣ በአቅም ግንባታና በቴክኖሎጂ ልማት ዘርፎች ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 16 ነጻ የሕግ ድጋፍ ማዕከላት እንዳሉት የተናገሩት ዶክተር አስራት ፣ የውሃ ሕግና ሜዲኮ-ሊጋል የመሳሰሉ ልዩ የሕግ ፕሮግራሞችን እያስፋፋ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል።

ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር የሚደረገው ይህ ትብብር የፍትሕ ሥርዓቱን በማዘመን፣ የሰው ኃይል አቅም በመገንባት፣ ለተማሪዎች የተግባር ልምምድ (ኢንተርንሺፕ) እድል በመፍጠርና የጋራ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስታውቀዋል።

ዶ/ር አስራት አክለውም፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ለመሥራት የጀመረው አዲስ አሰራር በፍትሕ ሥርዓቱ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፣ በጋራ የሚዘጋጁ የአጭር፣ መካከለኛና ረጅም ጊዜ እቅዶች ተቋማቱን ብቻ ሳይሆን ክልሉንና ሀገሪቱን የሚጠቅሙ ተምሳሌታዊ ውጤቶችን እንደሚያስገኙ ገልጸዋል።

ሁለቱ ተቋማት በጥናትና ምርምር፣ በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥና የሕግ ትምህርት ጥራት ፣ በአቅም ግንባታ፣ በዲጂታል የፍትሕ አገልግሎቶች ልማት፣ በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት፣ በአማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶች ማጠናከር፣ አለምአቀፍ ጉባኤዎችን በትብብር ለማዘጋጀትና በሌሎች የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት ማሻሻል በሚችሉ የጋራ ስራዎች ላይ በቅርበት ለመሥራት ተስማምተዋል።

የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ እና የዘርፉ አሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ላይ  ውይይት ተካሄደባሕር ዳር ፣ ሰኔ 26/2018 (...
03/07/2026

የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ እና የዘርፉ አሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሄደ

ባሕር ዳር ፣ ሰኔ 26/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ፣ የሕግ መሰረት እንዲኖረው የተደረገ ሲሆን፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢነት፣ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እና የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በጋራ የሚይዝ ነው።

የትብብር መድረኩ አባል ተቋማት ነጻነታቸውን ባከበረ መልኩ የፍትሕ አስተዳደሩን ውጤታማ ለማድረግ በሚያገናኟቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ እቅድ በማውጣት የሚሰሩ ሲሆን፣ አፈጻጸሙን በሚመለከት አብይ ኮሚቴው በእየጊዜው እየገመገመ ሲሰራ ቆይቷል።

በዛሬው እለትም፣ የትብብር መድረኩ የ2018 ዓ ም የእቅድ አፈጻጸም እና የዘርፉ የአሻጋሪ እና ዘላቂ ልማት እቅድ የአንድ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት አመራሮች፣ ዳኞች፣ ዐ/ህጎች፣ የፖሊስ አባላት፣ ሌሎች ባለሙያዎች እና አጋር አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል።

የትብብር መድረኩ፣ የተቋማትን ሙያዊ ነጻነት እና ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ ሰብአዊ መብት ማክበር እና ማስከበር፣ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውጤታማነት ማረጋገጥ፣ የአገልግሎት ቅልጥፍና ጥራት እና ውጤታማነት ማሳደግ፣ውጤታማ የሆነ የቴክኖሎጂ አቅርቦት እና ተጠቃሚነት፣ ቅንጅታዊ አሰራር፣ሙያዊ ስነ ምግባር መገንባት፣ ሙስና መከላከል እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ የአቅም ግንባታ ማጠናከር፣ የክርክር አቀራረብ እና አመራር ሥርዓት ማሻሻል፣ ማረም፣ ማነጽ እና ይቅርታ አሰጣጥ ስርዓትን ማሻሻል፣ የሪፎርም ሕጎችን አተገባበር ማጠናከር የሚሉ 11 አበይት ግቦችን በመያዝ ዝርዝር ተግባራትን በማቀድ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፣በየዘርፉ የተሰሩ ስራዎች ዝርዝር ሪፖርት ቀርቧል።

የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የ25 ዓመት አሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ ልማት እቅድ ለመጀመሪያ ጊዜ እራሱን ችሎ በክልሉ ምክር ቤት ጸድቆ የአምስት ዓመት እና የአንድ አመት እቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑ የሚታወስ ነው።

የዘርፉ የአሻጋሪ እና ዘላቂ ልማት እቅድ በዳኝነት እና የፍትሕ አካላት አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና በሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዛሬው እለትም የ2018 በጀት አመት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በዘርፋ የተያዙት ዋና አላማዎችም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና ዘላቂ ሰላም መገንባት፣ የላቀ ፍትሕ አገልግሎት ማረጋገጥ እና የፍትሕ ተደራሽነት እና ሰብአዊ መብት ማረጋገጥ የሚሉ ሲሆኑ፣ ዝርዝር ተግባራቶችን በሚመለከት በዓመቱ በሁሉም የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት የተተገበሩ ስራዎች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የዘርፎችን የ2018 በጀት ዓመት ሪፖርት ያቀረቡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አማካሪ እና የትብብር መድረኩ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ቢኒያም ዮሀንስ ሲሆኑ፣ ተሳታፊዎች በቀረበው ሪፖርት ላይ ሀሳብና አስተያይታቸውን ሰጠዋል።

የትብብር መድረኩ አባል ተቋማት መካከለኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የዳኝነት እና የፍትሕ መድረኩ በቅንጅት መስራቱ ተቋማቱ ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻሉን፣ በተቋማቱ መሪዎች እና ባለሙያዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ማስቻሉን አንስተዋል።

የትብብር መድረኩ መቋቋም ሙያዊ ስልጠናዎችን በጋራ ማግኘት እንዲችሉ እንዳስቻላቸው የተናገሩት ተሳታፊዎቹ፣ይሄም ከትብብር መድረኩ ባለፈ ለተቋማቸው እና ለግል ህይወታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ተሳታፊዎችን ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና ከትብብር መድረኩ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ጋር ያወያዩት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሀላፊ አቶ ብርሀኑ ጎሽም፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እና የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ኮሚሽነር ሀብታሙ ሲሳይ በተነሱ ሀሳብና አስተያይቶች ላይ ከተቋሞቻቸውና ከትብብር መድረኩ የጋር ስራዎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ አስተያይት ሰጠዋል።

መድረኩን ያጠቃለሉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በበኩላቸው፣ የትብብር መድረኩ ተቀዳሚ አላማ ለፍትሕ ፈላጊው የክልሉ ህዝብ የተቀናጀ ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ እና አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት በላቀ ትብብር መስጠት መሆኑን ገልጸው፣ ይሄንን እውን ለማድረግ ሁሉም የትብብር መድረኩ አባል ተቋማት፣ መሪዎች እና ባለሙያዎች በጀመሩት የላቀ ቁርጠኝነት እና የትብብር መንፈስ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

"የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው" ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው- የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንትባህር ዳ...
03/07/2026

"የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው" ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው- የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት

ባህር ዳር፣ ሰኔ 26/2018 ዓ.ም (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ እና የዘርፉ የአሻጋሪ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ዕቅድ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም የጋራ ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።

መድረኩን የከፈቱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የፍትሕ ተቋማት በተናጠል ሳይሆን በቅንጅትና በትብብር ሲሠሩ ለሕዝብ ፈጣን፣ ተደራሽ፣ ውጤታማና አመኔታን ያተረፈ የፍትሕ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ክቡር ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት፣ በመስከረም 2017 ዓ.ም በጋራ ስምምነት የተጀመረው የትብብር ሥራ በኋላ በአዋጅ ቁጥር 297/2017 የሕግ ማዕቀፍ በማግኘት በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ተደራጅቶ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው አክለውም፣ በክልሉ የ25 ዓመት የአሻጋሪ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ውስጥ የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፉ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለየ የዘርፍ ዕቅድ መካተቱ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፣ ለክልሉ መንግሥት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የተከናወኑ ሥራዎች ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ አፈጻጸም ማሳየታቸውን የገለጹት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ በሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ፣ በሰው ኃብት ልማት፣ በዲጂታል የፍትሕ አገልግሎቶች፣ በስማርት ችሎት፣ በአማራጭ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች፣ በባህል ፍርድ ቤቶች፣ በየተቋማቱ የመረጃ መጋራት እና በተቀናጀ የወንጀል መከላከል ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ጠቁመዋል።

የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት በድጋሚ በማደራጀት የልህቀት ማዕከል እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን፣ የፖሊስ ኮሌጅ ወደ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ማደጉን ይህም የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በስፋት እንዲያገኙ ማስቻሉን ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ጨምረው ገልጸዋል።

በትብብር መድረኩ በኩል የክልል አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ፣ የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የመረጃ ማዕከል ማቋቋሚያ እና የመረጃ መጋራት ስምምነት መዘጋጀታቸው በቀጣይ የፍትሕ አስተዳደሩን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጉትም ገልጸዋል።

የፍትሕ ዘርፉ የመጨረሻ ግብ ውጤታማ ፍትሕን ለሕዝብ ማረጋገጥ መሆኑን የገለጹት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ ሁሉም የዘርፉ ተቋማት የተጀመረውን መልካም የትብብር ሥራ በማጠናከር ለጋራ ዓላማ በተቀናጀ መንገድ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ አብይ ኮሚቴ  የትብብር መድረኩን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የ2018 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸም እና የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ የአ...
02/07/2026

የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ አብይ ኮሚቴ የትብብር መድረኩን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የ2018 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸም እና የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ የአሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት እቅድ የአንድ ዓመት አፈጻጸም ገመገመ

ባሕር ዳር፣ ሰኔ 25/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ አብይ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ የ2018 ዓ.ም የትብብር መድረኩ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና በአማራ ክልል የአሻጋሪ የዕድገትና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ማዕቀፍ የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፉን የአንድ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

ሁለቱ ሪፖርቶች በትብብር መድረኩ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለአብይ ኮሚቴው ቀርበዋል።

በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ በዝርዝር የተወያዩት የአብይ ኮሚቴው አባላት ፣ ሪፖርቶቹ፣ የተቋማቱን ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጨምሮ ሌሎች አጋርና ባለድርሻ አካላት በሚሳተፉበት የጋራ የውይይት መድረክ ላይ ለተጨማሪ ውይይትና ግምገማ እንዲቀርቡ ተስማምተዋል።

የጋራ የውይይት መድረኩ ሰኔ 26 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድም ተገልጿል።

የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፍትሕ ቢሮ፣ የፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ያቀፈ ሲሆን፣ የአብይ ኮሚቴው አባላትም፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት፣ የፍትሕ ቢሮ ሀላፊ፣ የፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ኮሚሽነር እና የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ናቸው።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ጋር በትብብር ለመስራት ተወያዩባህርዳር፣ ሰኔ 25/20...
02/07/2026

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ጋር በትብብር ለመስራት ተወያዩ

ባህርዳር፣ ሰኔ 25/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገልጋዩን ወጭ፣ እንግልት፣ ጊዜ እና ጉልበት የቀነሰ፤ ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ተገማች የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት በሁሉ አቀፍ የለውጥና የአሰራር ማሻሻያ ላይ ይገኛል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ አሰራሮቹን በማጠናከር አገልግሎቱን በላቀ ጥራትና ተደራሽነት ለማቅረብ፣ እና በሌሎች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ማሻሻያዎች ላይ በአጋርነት እና በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ውይይት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ከአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሸኽ ኑረዲን ቃሲም ጋር አድርገዋል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ኑረዲን ቃሲምና ሌሎች የምክር ቤቱ አመራሮችን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ የክልሉን ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በተጨባጭ ለማሻሻል የተተገበሩ እና እየተተገበሩ ያሉ ለውጦችን በሚመለከት ገለጻ አድርገውላቸዋል።

ከውይይቱ በተጨማሪ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ምቹ የስራ ከባቢ እና ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ተዘዋውረው የጎበኙት ሸኽ ኑረዲን ቃሲም፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጀመራቸው የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች መደነቃቸውን ገልጸው፣ በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች እና በሌሎች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ስራዎች ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

29/06/2026

“ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የለውጥ ስራዎች የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፉን ያሻሻሉ ናቸው” ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው-የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት
በክልሉ የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ የለውጥ ስራዎችና ውጤታማነት ላይ ከዘርፉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር የተካሄደውን ውይይት ተክትሎ የ Amhara Media Corporation/ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያሰናዳው ዘገባ

የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች አካል ጉዳተኞች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባ እኩል የመሳተፍ መብት ተወያዩባሕር ዳር፣ ሰኔ 20/2018  ...
27/06/2026

የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች አካል ጉዳተኞች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባ እኩል የመሳተፍ መብት ተወያዩ

ባሕር ዳር፣ ሰኔ 20/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

በዳኝነትና በፍትህ ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ የለዉጥ ሥራዎች እና የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ዉጤታማነት ለማሳደግ የሚወሰዱ ተሞክሮዎች በሚል ርዕስ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዘጋጅነት በተካሄደው ወርክሾፕ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎችና የውይይት መነሻ ጽሁፎች ሲቀርቡ ውለዋል።

በወርክሾፑ የከሰዓት ውሎም፣ የፍትህ ተደራሽነትን ለማሳደግ ሊወሰዱ የሚገባቸው ስትራቴጅክ እርምጃዎች እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ሀሳብ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር በሆኑት ሞላልኝ በላይ (ዶ/ር)፣ አማካኝነት ቀርቧል።

ትኩረቱን የፍትሕ ስርዓቱ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ መሆኑን ማረጋገጥ ላይ ያደረገ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን፤ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሆነ የፍትሕ ሥርዓት አለ ለማለት የፍትሕ ተቋማት ህንጻዎች ለአካል ጉዳተኞችን ምቹ መሆንን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በፍትሕ ሂደቶች ውስጥ እኩል ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥንም የሚጨምር ስለመሆኑ ተነስቷል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ያልሆኑ የፍትሕ ተቋማት ሕንጻዎች፣ በፍትሕ ተቋማት የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ አለመኖር፣ በብሬል የተዘጋጁ የሕግ ሰነዶች እጥረት እና ለዳኞች፣ ዐ/ህጎች ፣ለፖሊሶች፣ እና ሌሎች የፍትሕ ሥርዓት ተሳታፊዎች አካል ጉዳተኝነትን አስመልክቶ በቂ የግንዛቤ ስልጠና አለመሰጠቱ በዘርፉ የሚነሱ ችግሮች መሆናቸው ተነስቷል፡፡

ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አካላዊ መሰረተ ልማት ማሻሻያዎች እና የሥርዓት ማሻሻያዎች ሊደረጉ የሚገባ ስለመሆኑ ጽሁፍ አቅራቢው ዶክተር ሞላልኝ አንስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ በወንጀል ምርመራ ሂደት የፖሊስ እና ዐ/ህግ ሚና በሚል ርዕስ ሌላ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ሀሳብና አስተያየት ተሰጦበታል።

ጥናታዊ ጽሁፉን ያቀረቡት፣ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሰቲ የፒ.ኤች .ዲ ፕሮግራም አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር መዳረሻዉ ታፈሰ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሰቲ የህግ ትምህርት ክፍል ሀላፊ ዋና ኢንስፔክተር ትንሳኤ ገብረክርስቶስ
ሲሆኑ፣ በወንጀል ምርመራ ሂደት ውስጥ የዘርፉ ተቋማት ሊኖራቸው የሚገባውን ኃላፊነት የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በቀረቡት የውይይት መነሻ ሀሳቦች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በውይይቱ ማጠቃለያ የሰጡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘደንት ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው፣ የዲጂታል ፍትሕ አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሚሆንበትን አግባብ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚሰራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉ ጊዜ ህግና ስርዓት በማጽናት የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ሚና በሚል ርእስ ለአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተሰጠባህርዳር...
27/06/2026

ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉ ጊዜ ህግና ስርዓት በማጽናት የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ሚና በሚል ርእስ ለአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ

ባህርዳር፣ ሰኔ 20/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት በዘላቂነት በማሻሻል ህብረተሰቡ እምነት የሚጥልባቸው፣ በክልሉ የልማት እና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና መወጣት የሚችሉ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማትን ለመገንባት ከሌሎች የፍትሕ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እና በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይዞት የተነሳውን ርዕይ እውን ማድረግ በሚያስችለው የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ትግበራ የእስካሁን አፈጻጸም እና ቀጣይ የትብብር አቅጣጫ ላይ ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እና ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር የተወያየ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉ ጊዜ ህግና ስርዓት በማጽናት የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ሚና በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጧል።

ስልጠናውን የሰጡት በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት የሕግ አማካሪ እና ተመራማሪው ዮናስ ተስፋ (ዶ/ር) ናቸው።

ዶክተር ዮናስ፣ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉበት ወቅት በአስቻይ ሁኔታዎች ከሚያስፈልጉበት በላይ እንደሚያስፈልጉ ገልጸው፣ በችግር ወቅት እና ከችግሩ ማግስት ህግና ስርዓትን የማስፈን ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በተለያየ ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጽናት ለማለፍ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ጥንካሬ ወሳኝ ነው ያሉት ዶክተር ዮናስ፣ ተቋማቱ አንዱ ባንዱ ላይ ሳይነሳ፣ ከውድድር በነጻ መንፈስ እና በላቀ ትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ጠንካራ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ያላቸው ሀገራት የከፋ ችግር እንደማይገጥማቸው በገለጻቸው ያብራሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ እነዚህ ተቋማት በችግር ጊዜ የመረጋጋት መልህቅ ናቸው ብለዋል።

የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉበት ወቅትም በሙሉ አቅማቸው ስራ ላይ ሊሆኑ እንደሚገባ ያስረዱት ዶክተር ዮናስ፣ ህገወጥነት እንዳይባባስ፣ ህግ እና ስርዓት በግለሰቦች እጅ ላይ እንዳይወድቅ እና ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ የሌሎች ንጹሀን መብት እንዳይጣስ የማድረግ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ጠንካራ ለማድረግ እና አሰራራቸውን ለማዘመን በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ማየታቸውን የተናገሩት ዶክተሩ፣ እየተተገበሩ ያሉ ዘመናዊ የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች፣ እንዲሁም የዳኞችን እና ሌሎች የፍትሕ አካላትን አቅም ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

ከዳኝነት እና የፍትሕ አካላት መሪዎችና ባለሙያዎች የሚጠበቅ ሙያዊ ስነ-ምግባር በሚል ርዕስ ለአማራ ክልል ዳኞች እና ሌሎች የፍትሕ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተሰጠባህርዳር ፣ ሰኔ ...
27/06/2026

ከዳኝነት እና የፍትሕ አካላት መሪዎችና ባለሙያዎች የሚጠበቅ ሙያዊ ስነ-ምግባር በሚል ርዕስ ለአማራ ክልል ዳኞች እና ሌሎች የፍትሕ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ

ባህርዳር ፣ ሰኔ 20/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እየወሰዳቸው ካሉ ስር-ነቀል የለውጥ ስራዎች አንዱ የዳኞችን፣ የጉባኤ ተሿሚዎችን እና የሰራተኞችን ሙያዊ እና ስነ-ምግባራዊ አቅም ማሳደግ ነው።

በክልሉ የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ካስፈለገ ሁሉም የዘርፉ ተዋናዮች በጋራ ትብብር መስራት አለባቸው የሚለው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ጨምሮ፣ ከክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ፣ ፍትሕ ቢሮ እና ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከተወጣጡ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር ዘርፉ ለክልሉ ማህበረሰብ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በላቀ ደረጃ ለማቅረብ እስካሁን በተሰሩ የጋራ ስራዎች እና በቀጣይ የትብብር መስኮች ላይ የሚመክር ወርክሾፕ አዘጋጅቷል።

በወርክሾፑ ላይ ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ የሕግ ምሁራን ስልጠናዎችን የሰጡ እና የውይይት መነሻ ጽሁፎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም በቀረቡ ጽሁፎች መነሻነት ውይይቶችን አካሂደዋል።

ለዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ከሰጡት የህግ ምሁራን መካከልም፣ የወንጀል ፍትሕ ፕሮፌሰሩ ፔትሮ ቶጃ አንዱ ናቸው።

በፔንስልቫንያ (ዩናይትድ ስቴትስ) በሚገኘው የኩተዝታውን ዩኒቨርሲቲ የወንጀል ፍትህ ትምህርት ክፍል ለ27 ዓመታት ያስተማሩት ፕሮፌሰር ፔትሮ ቶጃ፣ከዳኝነት እና የፍትሕ አካላት መሪዎችና ባለሙያዎች የሚጠበቅ ሙያዊ ስነ-ምግባር በሚል ርዕስ ስልጠና ሰጠዋል።

ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች በተጨማሪ በጣሊያን እና ሌሎች ሀገሮች በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርስቲዎች ያስተማሩት ፕሮፌሰሩ፣ ያገኙትን ልምድ እና እውቀት ለክልሉ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች አጋርተዋል።

የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ካለባቸው ህዝባዊ አደራ የሚመነጭ ከፍተኛ የሆነ የሙያዊ ስነ-ምግባር ባለቤት መሆን ይጠበቅባቸዋል ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይህንን ሕዝባዊ አመኔታ ለማስጠበቅ ሁሉም የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ማህበረሰባቸውን በላቀ የሙያ ስነ-ምግባር ማገልገል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የዳኝነት እና የፍትሕ አካላትን ሙያዊ ስነምግባር ምንነት እና አስፈላጊነት የአሜሪካን ጨምሮ የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮ እያነሱ ለተሳታፊዎች ገለጻ ያደረጉት ፕሮፌሰሩ፣ የተለያዩ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ፍልስፍናዊ አተያይም ለውይይት ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም በጉዳዩ ላይ ያሏቸውን ጥያቄዎች እና አስተያይቶች አንስተውላቸዋል።

ፕሮፌሰር ፔትሮ፣ ከዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በተጨማሪ፣ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች በዳኝነት ሙያዊ ስነ-ምግባር ላይ ስልጠናዎችን ሰጠዋል።

ህብረተሰቡ በህይወቱ፣ በንብረቱ እና በነጻነቱ ላይ ወሳኝ አድርጎ የሾማቸው ዳኞች በላቀ የስነ-ምግባር ደረጃ ላይ መገኘት አለባቸው ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይሄንን በማረጋገጥ ለሙያቸው ክብር የመቆም ታሪካዊ ሸክም ተጥሎባቸዋል ብለዋል።

ዳኞች በእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው እና በማህበራዊ መስተጋብራቸው ጭምር ህብረተሰቡ ከእነሱ የሚጠብቀው የስነ ምግባር ልእልና አለ ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይሄንን አስጠብቆ መዝለቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቅምን ጨምሮ አንዳንድ ገደቦች የዳኝነት ሙያን ክብር ለመጠበቅ እና የዳኞችን ገለልተኛነት በማረጋገጥ ህብረተሰቡ የሚሰጡ ውሳኔዎች ከወገንተኝነት ነጻ ሆነው የተሰጡ በመሆናቸው በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት እንዲያድርበት የሚቀመጡ ገደቦች መሆናቸውን በስልጠናቸው ያነሱት ፕሮፌሰር ፔትሮ፣ ገደቦቹ አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት ዳኞች ላይም የሚተገበሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ስልጠናውን የተከታተሉ ዳኞችና የጉባኤ ተሿሚዎች ከዳኝነት ሙያዊ ስነ-ምግባር ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን፣ በዘርፉ በንባብ ፣ በስራ እና በህይወት ልምድ የካበተ እውቀት ያላቸው ፕሮፌሰር ፔትሮ ቶጃ ምላሽና ማብራሪያ ሰጠዋል።

Address

Bahir Dar
Kebele 13
P.BOX901

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት/ Supreme Court of Amhara Region posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share