14/07/2026
የኮምቦልቻ ከተማ የጸጥታ ተቋማት የክረምት ወራት ተግባር አፈፃፀም የእቅድ ኦረንቴሽን ውይይት አካሄደ።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኮሙኒኬሽን ሀምሌ/7/2018ዓ.ም
የኮምቦልቻ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ እና የኮምቦልቻ ከተማ ሚሊሻ መምሪያ 3ቱም ተቋማት በጋራ ከክረምት ወራት ጋር ተያይዞ የህግ ማስከበር ተግባራት እንዲሁም የፀጥታ ተቋማት አቅም ግንባታ ዝርዝር የተግባር አፈፃፀም ማስፈፀሚያ እቅድ ኦረንቴሽንና የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አስመልክቶ በየ ደረጃው ከሚገኙ አጋርና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከከተማው የፀጥታ መዋቅር ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ እንዳሉት የፀጥታ ተቋም ዋነኛ ግባቸው የህዝቡን በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት ማረጋገጥና የህግ የበላይነት አንዲሰፍን ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው በክረምት ወራት ሊከናወኑ የሚገባ የፀጥታ ስራዎችን በጋራ እና በተናጠል የስራ ክንውን የሚገልፅ አጋርና ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የጋራ የእቅድ ኦረንቴሽን ነው ብለዋል።
ለውይይቱ መነሻ የክረምት ወራት /90/ ቀን ከክረምት ወራት ጋር የሰላም ግንባታ ትኩረት ያደረገ የፖሊስ ፣ የሰላምና ፀጥታ እና የሚሊሻ ተቋማት የሚከናወኑ ዝርዝር ማስፈፀሚያ እቅድና የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን የያዘ የመወያያ ሰነድ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ጌታቸው ሙህዬ በዝርዝር ለፀጥታ መዋቅሩ አቅርበዋል።
እንደ ኮማንደር ጌታቸው ሙህየ ገለፃ ሁሉም የፀጥታ መዋቅር አጋር አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር ከክረምት ወራት ጋር የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ህብረተሰቡን ለፀጥታ ስራ እያበረከተ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ በማጠናከር የህብረተሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ ወንጀል እና የወንጀል ስጋቶችን መቀነስ ፣ ከመከላከል አልፎ የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን ምርመራ ማጣራት እና የትራፊክ አደጋን መከላከል ምንም አይነት የወንጀል ችግር እንዳይከሰት በትኩረት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ አስረድተዋል ።
በኮምቦልቻ ከተማ የህግ የበላይነት አንዲረጋገጥ የፀጥታ መዋቅሩን የመፈፀም አቅም ለማሳደግ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናና የሰው ሀይል ግንባታ ማከናወን ሌላኛው አብይ ጉዳይ መሆኑን ኮማንደር ጌታቸው አውስተዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ ሚሊሻ መምሪያ ኅላፊ ኮሎኔል ጌታወይ ዘገየ በበኩላቸው ሁሉም የፀጥታ ተቋማት በግልፀኝነት እና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠንከር የጋራ ተልዕኮን በውጤታማነት ለማከናወን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የፀጥታ መዋቅሩ ህዝባዊ አገልጋይ መንፈስ በመላበስ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ኮሎኔል ጌታወይ ዘገየ ተናግረዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት የማህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች በሰላም እንዲከወኑ ማህበረሰቡን ያሳተፈ የፀጥታ ተግባራት እና ሁሉም አካላት ተቋማዊ ኅላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እና በታማኝነት መፈፀም ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በእቅድ ውይይት ላይ የየተቋማትን ጥንካሬና ድክመቶችን የለየና የቀጣይ አቅጣጫዎችን ያመላከተ በመሆኑ በውጤት የታጀበ ተግባር ለመፈፀም ያስችላል ሲሉ ተደምጠዋል።
።።ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም ።።