03/09/2026
በስልጢ ወረዳ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የሶላር ሲስተም የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ!
በስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ በአሳኖ ዱግደሬራ ቀበሌ በ«ዳይሬክት ኤድ» (Direct Aid) የበጎ አድራጎት ድርጅት በ18.5 ሚሊዮን ወጪ የተገነባውና ከ4 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርገው የሶላር ሲስተም የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃና ማዕድን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር፤ በአሳኖ ዱግደሬራ ቀበሌ እውን የሆነው ይህ የውሃ ፕሮጀክት የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ በዘላቂነት የፈታ መሆኑን ተናግረዋል።
የዞኑ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ከክልልም ሆነ ከመዋቅር አንጻር አሁንም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያነሱት ወ/ሮ አለይካ፣ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በዞኑ እንዲንቀሳቀሱ የሚደረገው ይህንኑ የውሃ አቅርቦት ችግር ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ አብራርተዋል።
እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 47 ከመቶ የሚሆነው ማህበረሰብ አሁንም የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን እንዳላገኘ የጠቆሙት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ፤ መንግስት ከመንግስታዊ ካልሆኑ አጋር ድርጅቶችና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
አክለውም ህዝቡ ከብዙ ጥረትና ልፋት በኋላ እውን የሆነውን ይህን የልማት አውታር በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ መልእክት አስተላልፈዋል።
የስልጤ ዞን መንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነኢማ ሙኒር በበኩላቸው፤ ውሃ የህይወት፣ የጤና እና የልማት መሰረት በመሆኑ የመጠጥ ውሃ ሽፋንን ባጠረ ጊዜ ለማሻሻል ከልማት አጋሮች ጋር የተቀናጀ አሰራር መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።
ወ/ሮ ነኢማ አክለውም፤ በዞኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት 22 የውሃ ፕሮጀክቶችን በማስመረቅ ለህዝብ ክፍት ማድረግ መቻሉን አውስተው፤ በ2018 ዓ.ም ብቻ 14 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መበቃታቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት 48% የደረሰውን የዞኑን የመጠጥ ውሃ ሽፋን በ2019 ዓ.ም መጨረሻ ወደ 58% ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ዛሬ የተመረቀውና ከ18.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የአሳኖ ፕሮጀክት፤ 30 ሺህ ሊትር የመያዝ አቅም ያለው ማጠራቀሚያ፣ 5 የውሃ ቦኖዎች እና 3.5 ኪሎ ሜትር የቱቦ ዝርጋታ ያለው እንደሆነ ተገልጿል።
የስልጢ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሸምሴ ረዲ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ የአሳኖ ዱግደሬራ ቀበሌ ህዝብ ለረጅም ዓመታት ሲያነሳው የነበረውን የመጠጥ ውሃና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በዘላቂነት እንደመከተው ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ልዩ ባህሪ በፀሐይ ኃይል (Solar Energy) የሚሰራ በመሆኑ ከነዳጅና ከመብራት ወጪ ነፃ የሆነና ዘመናዊ አሰራርን የተከተለ መሆኑን አስረድተዋል።
አያይዘውም በወረዳው በ2018 ዓመት ብቻ ከ66 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ የውሃ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፤ በዚህም ከ14,240 በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ የወረዳውን የመጠጥ ውሃ ሽፋን ወደ 37.7% ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል።
የ«ዳይሬክት ኤድ» የኢትዮጵያ ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ጠሃ ማህሙድ ለፕሮጀክቱ እውን ማህን ማህበረሰቡና አማራሩ ላድረገላው ሁለንተናው ድጋፍ አመስግነዋል።
ዛሬ በአሳኖ ዱግደሬራ የተመረቀ በዞኑ አራተኛው ፕሮጀት እንደሆነ ገልጸው በቀጣይም የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በምረቃ መርሃ-ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃና ማዕድን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር፣የስልጤ ዞን መንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነኢማ ሙኒር፣ የ«ዳይሬክት ኤድ» የኢትዮጵያ ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ጠሃ ማህሙድ፣
የስልጤ ዞን መንግስት ረዳት ተጠሪና የፖለቲካና ሪዖት አለም ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሁሴን ሱነሞ፣ የስልጤ ዞን ውሃ መምሪያ ሀላፊ አቶ ጨፋ ከድር የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን፤ አመራሮቹ ለልማት አጋር ድርጅቱ «ዳይሬክት ኤድ» ላደረገው ሁለገብ ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።