21/08/2026
የኢንተርፕራይዞች አዲሱ የእድገት መንገድ፡ ከባህላዊ ገበያ ወደ ዲጂታል ምህዳር
ዲጂታል ቴክኖሎጂ የንግድ አሠራርን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀየረ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ምርትን ከመሸጥ ይልቅ ገበያ ማግኘት ትልቁ ፈተና ሆኗል። ይህንን መዋቅራዊ ለውጥ ተከትሎ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢንተርፕራይዞችን የገበያ ትስስር ከማስፋት ባሻገር ዲጂታል ገበያን እንደ አዲስ የንግድ መድረክ ለማስፋፋት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ለአንድ ኢንተርፕራይዝ እድገትና ዘላቂነት ምርት ማምረት ብቻውን በቂ አይደለም። ምርቱን ተደራሽ የሚያደርግበት ሰፊ ገበያ፣ ገዢ እና ሁለቱን የሚያገናኝ ቀልጣፋ የግብይት ሥርዓት ካልተዘረጋ፣ የምርት አቅም ብቻውን ወደ ተሻለ ንግድ ሊያሸጋግር አይችልም።
ይህንን እውነታ በመገንዘብ ሚኒስቴሩ ባለፉት አምስት ዓመታት የገበያ ትስስርን ማጠናከር ከትኩረት መስኮቹ አንዱ አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም በ5 ዓመቱ ዕቅድ 252 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ፣ 295 ቢሊዮን ብር (116%) ማስመዝገብ ተችሏል። በዚሁ ሂደትም ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ኢንተርፕራይዞችን የዕድሉ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ከዚህም በላይ ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ ለማድረግ ወደ ዲጂታል የገበያ አማራጮች መግባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡
በባህላዊ የገበያ አሠራር አንድ ኢንተርፕራይዝ ምርቱን ለማስተዋወቅ አካላዊ ቦታ፣ የገበያ መድረክ ወይም በቀጥታ ገዢ መፈለግ ይጠይቅ ነበር። ዲጂታል ገበያ ግን ይህንን ሂደት በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ምርትን ከገዢ ጋር በፍጥነትና በሰፊ የገበያ ክልል ማገናኘት ያስችላል።
ኢንተርፕራይዞች በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (LMIS) በኩል ያበለጸገው «ሉሲ» (Lucy) ዲጂታል ገበያ ሁነኛ ማሳያ ነው። ሉሲ ዲጂታል ገበያ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን በዲጂታል መድረክ ላይ እንዲያስገቡ፣ እንዲያስተዋውቁና ለተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡ የሚያስችል ዘመናዊ መድረክ ነው።
እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ ከ3,000 በላይ ኢንተርፕራይዞች ፕላትፎርሙን ተቀላቅለዋል። ይህ ቁጥር በቁጥር ብቻ የሚለካ ሳይሆን፣ ከአሮጌው አሠራር ወደ ዘመናዊው የዲጂታል ንግድ ሥነ-ምህዳር እየተደረገ ያለውን መዋቅራዊ ሽግግር ያመላክታል። ፕላትፎርሙ በአካባቢው ብቻ ተወስኖ ይሸጥ የነበረን ምርት በዲጂታል መድረክ በማስተዋወቅ ከመላው ዓለም ጋር ለማገናኘት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።
ዲጂታል ገበያ የሚሰጠው ዕድል የምርት ማስተዋወቂያ ብቻ አይደለም፤ የገዢና ሻጭ መረጃን ማሰባሰብ፣ የገበያ ፍላጎትን መረዳት፣ የምርት ጥራትን ማሻሻል እና የንግድ ውሳኔዎችን በመረጃ ላይ መመስረትም የሥርዓቱ አካል ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ይህ አዲስ አሠራር በአዲስ አበባ ከተማ በልዩ ንቅናቄ እየተመራ ይገኛል። አሠራሩ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በስፋት እንዲጠቀሙበት የዲጂታል ክህሎት ግንባታ፡ የጥራት እና አቀራረብ ማሻሻያ፡ የምርት ጥራትና የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ድጋፎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡