02/09/2026
"ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር የአብሮነትና የትብብር እሴቶችን አጠናክሯል" የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ኮሚሽን
ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም
በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም አከባቢዎች የተውጣጡ በጎ ወጣቶች በሲዳማ፣ ኦሮሚያና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ተዘዋዉረው የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን አከናውነዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ኮሚሽን ኮሚሽነር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በ3ቱ ክልሎች ተንቀሳቅሰው ያከናወኑት ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ወጣቶቹ በተንቀሳቀሱባቸው ክልሎች የደም ልገሳ፣ ችግኝ ተከላ፣ አረጋውያንን የመመገብ፣ የከተማ ጽዳት እንዲሁም የተማሪዎችን የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩ ከበጎ ተግባር ባሻገር ወጣቶችን በአንድ ዓላማ በማሰባሰብ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የትብብር እሴቶችን አጠናክሯል ሲሉም አቶ ማርቆስ ጠቅሰዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚካኤል ዋዳ በበኩላቸው መርሃ ግብሩ በሕዝቦች መካከል ያለውን የተሳሰረ ማንነትና አብሮነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣቶች ደም በመለገስ ለሕይወት መዳን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የሕዝቦችን በደም የተሳሰረ አብሮነት እንደሚያሳይ አቶ ሚካኤል ገልፀዋል።
በቀጣይም ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከሲዳማ እና ከአዲስ አበባ የሚመጡ ወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች በተመሳሳይ በክልሉ የበጎ ተግባር መርሃ ግብር ላይ እንደሚሳተፉም አመላክተዋል።
በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ ወጣቶችም በቆይታቸው በርካታ ልምድ መቅሰማቸውን ተናግረዋል።
በየኔዓሐም ሳሙኤል