14/07/2026
በምክክር ጉባኤው ትልቋን ኢትዮጵያ የሚገነቡ ሀሳቦችን ከማፍለቅ አኳያ ከተሳታፊዎች ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቅባቸዋል።
የርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ መልዕክት
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በነገው ዕለት የሚጀመረውን ታሪካዊ ሀገራዊ ምክክር በማስመልከት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ በአግባቡ ልንጠቀምበት በሚገባ፤ በታሪካዊውና ሁሉን አሸናፊ በሚያደርግ ታላቁ ሀገራዊ ምክክር ዋዘማ ላይ እንገኛለን፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ በረዥሙ የሀገረ-መንግስት ታሪካችን ካለፍንበት ደካማ የፖለቲካ ባህል፤ በተለይም ከግጭት፤ ከርስ በርስ ጦርነትና የመጠፋፋት አዙሪት ሀገራችንን በማሻገር፤ ሁሉን አካታች በሆነ ምክክር ዘላቂ ሰላሟና ሁለንተናዊ ብልጽግናዋ የተረጋገጠ የተሻለች ጠንካራ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ወሳኝ የታሪካ ምዕራፍ ነው፡፡
እንደ ሀገር ያለፍንበት የፖለቲካ ታሪክ፤ የሃሳብና የፍላጎት ልዩነቶችንና ታሪካዊ ቅራኔዎችን በውይይትና በምክክር ሊፈቱ የማይችሉ ተቃርኖዎች አድርጎ የሚያይ፤ በከፋፋይ ትርክቶችና የጠላትነት ፍረጃዎች የታጀበ፤ በአፈሙዝ ኃይልና በጉልበት ለመፍታት በሚደረጉ አውዳሚ ጦርነቶች የተሞላ የአሸናፊና ተሸናፊ የኋልዮሽ አዙሪት ነው፡፡
በነገው ዕለት የሚጀመረው ታላቁ ሀገራዊ ምክክር፤ ይሄው ከደካማው የፖለቲካ ባህላችን የወረስነውን የፖለቲካ ስብራት በማከም የጀመርነውን ሀገራዊ የሰላም፤ የልማትና የብልጽግና ጉዞ ለማጽናት ዓይነተኛ መፍትሄ ከመሆኑም ባሻገር፤ መዳረሻው ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን አሸናፊ የሚያደርግ ብሔራዊ መግባባት፤ በእርስ በርስ መተማመን የፀና የሕዝቦች አንድነትና ጠንካራ ኅብረ-ብሔራዊ ሀገረ መንግስት ስለመሆኑ እምነቴ የጸና ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ ከየዞኑ የክልላችንን ሕዝቦች በመወከል በዚህ ታሪካዊ ሀገራዊ ምክክር የመሳተፍ ዕድል ያገኛችሁ የሕዝብ ተወካዮች፤ በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋ ለተረጋገጠ፤ ሉዓላዊነቷ በሙላት ለተከበረ ለጠንካራዋ ኢትዮጵያ ዕውን መሆን አሻራችሁን እንድታሳልፉ ጥሪ አቀርባለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!