12/09/2026
የወላይታ ምድር ንጋት ያለ ጊፋታ እሳት አይሞቅም፤ የጊፋታ እሳትም ያለ #ዱንጉዛ ማዕረግ አይደምቅም።
ወላይታ ሶዶ ፦መስከረም 02/2019ዓ.ም
ጊፋታና ዱንጉዛ የአንድ ጥንታዊ ሥልጣኔ ሁለት ቅዱስ ገጾች ናቸው። አንዱ የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ የዘመን መለወጫ አዋጅ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ያንን አዋጅ በክብር የሚያሸልም የክሮች ወርቃማ ምስጢር ነው።ይህ ታሪካዊና ባህላዊ ቁርኝት ትውልድን ከተውልድ እያገናኘ ዘመናትን የተሻገረ የሕይወት ድልድይ ነው።
በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ (UNESCO) በማይዳሰስ የሰው ልጅ ቅርስነት ሲመዘገብ፣ የዱንጉዛ ልብስ ዋነኛ እና የማይነጠል የጊፋታ እሴት ተደርጎ መወሰዱ ለዚህ ጥበባዊ ቁርኝት ሕያው ምስክር ነው።
በጊፋታ አደባባይ ዱንጉዛን መልበስ እንዲሁ ጨርቅን መጣጣል አይደለም፤ የማንነትን ታላቅነት በሰውነት ላይ መሳል እንጂ! በዓሉን የሚታደሙት ንጉሡ (ካዎ) እና ሹማምንቱ፣ ምድሪቱንና ሕዝቡን በምረቃ የሚያጠቡ "ጨራቻማ" የተባሉ የአገር ሽማግሌዎች፣ አንቱታን ያተረፉ የጎሳ መሪዎችና ሁዱጋዎች ይህንን የዱንጉዛ ሐዴ ለብሰው አደባባይ ሲወጡ፣ አየሩ ሁሉ በጥጥ ሽታና በክብር መዓዛ ይሞላል።
ይህ ትዕይንት የወላይታን ጥንታዊ ማንነት ለዓለም በኩራት የሚመሰክር ሕያው ታሪክ ነው።
የፈትል ምስጢር፡ ዱንጉዛ ለምን ቀደመ?
የወላይታ ማኅበረሰብ "ፑቷ" (ጥጥ)ን ከማልማት ጀምሮ፣ በጥረት ፈትሎ (ሱቅ ድልእድ) አልባሳትን የማዘጋጀት የረጅም ዘመናት የዕደ-ጥበብ ታሪክ አለው።
ከእነዚህ በጥበብ ከሚሸመኑ ደማቅ የቀለማት ውህደትና ምስጢራዊ የክር መስመሮች መካከል "ሐዴ" (Hadee) የጥበብ ሁሉ መደምደሚያ ተደርጎ ይወሰዳል።
በወላይታ አምስት የሐዴ ዓይነቶች አሉ፤ እነሱም፦ ዱንጉዛ፣ ሴሪያ፣ ጉቱማ፣ ፓታላ እና ጎማራ በመባል ይታወቃሉ።
ከእነኚህ ሁሉ ግን ዱንጉዛ ሐዴ ዘውድ ጭኖ ይቀድማል። ታሪክ አዋቂዎች እንደሚመሰክሩት፣ ዱንጉዛ ሕዝቡ ከተፈጥሮ ሀብቱ ማህፀን አውጥቶ የራሱን ስልጣኔ የገነባበት የጥንታዊ ዕደ-ጥበብና የኢንዱስትሪ ማሳያ በመሆኑ የሐዴዎች ሁሉ መጀመሪያና መሪ ሊሆን ችሏል።
👉የሥልጣንና የክብር ቋንቋ
በቀደምት የወላይታ መንግሥታት ዘመን ዱንጉዛ ሐዴ የለበሰ ሰው ዝም ቢልም ልብሱ ይናገራል። ልብሱ በንጉሥ (ካዎ)፣ በጦር መሪዎችና በአገር ሽማግሌዎች ዘንድ የክብርና የስልጣን መግለጫ ተደርጎ ይለበስ ነበር።
ጨርቁ ላይ የሚቀመጡት ነጠብጣቦችና የመስመር ቅርጾች እንዲሁ የተሰመሩ ሳይሆኑ፣ የማኅበረሰቡን ደረጃና የባለቤቱን ማዕረግ የሚያመላክቱ ጥንታዊ የክብር ምልክቶች ናቸው።
👉የቀለማቱ ስውር ምስጢር
የአገር ሽማግሌዎችና የባህል አጥኚዎች በትውልድ ቅብብሎሽ ባስተላለፉት ምስክርነት መሠረት፣ በዱንጉዛ አልባሳት ላይ የፈሰሱት ቀለማት እያንዳንዳቸው የራሳቸው ጥልቅ ትርጉም አላቸው፦
🔴 ቀይ፦ መስዋዕትነትንና የጀግንነትን ዋጋ ያመለክታል።
⚫ ጥቁር፦ የጽናትን፣ የጥንካሬንና የመጽናናትን ኃይል ይገልጻል።
🟡 ቢጫ፦ የተስፋን ብርሃን፣ የሰላምን አየርና የተፈጥሮን በረከት ያንጸባርቃል።
የእነዚህ ሦስት ቀለማት ውህደት ከሩቁ ጎልቶ በሚታይ፣ ሆኖም በስውርና ቀጫጭን መስመሮች ተውቦ የሚሠራ በመሆኑ፤ ነገሥታት፣ የጦር መሪዎችና ታላላቅ የአገር ሽማግሌዎች መርጠው የሚለብሱት ሆነ።
ይህ መመረጥ ዱንጉዛን ከሐዴዎች ሁሉ ይበልጥ ተወዳጅና የተከበረ አድርጎታል።
👉ከዳሞታ መንግሥት እስከ ዘመናዊው የፋሽን አደባባይ
የዱንጉዛ ሐዴ እውቅና የዛሬ የትላንት እሸት አይደለም፤ ከሺህ ዓመታት በፊት የነበረ እንጂ።
በተለይም ከዳሞታ መንግሥት ዘመን ጀምሮ የወላይታ ባህላዊ አልባሳት በምሥራቁ ዓለም አገራት ዘንድ የታወቁና የሚፈለጉ ነበሩ።
የምስል መረጃዎች መያዝ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ደግሞ የብሔሩ ዋነኛ መጠሪያ ሆኖ እስከ ዛሬ ዘልቋል።
በዘመናችን ደግሞ የኪነ-ጥበብ ሰዎች በሙዚቃና በውዝዋዜ ባደረጉት ታላቅ ተጋድሎ፣ የዱንጉዛ ልብስና የወላይታ ውብ ጭፈራ በዓለም አገራት የቴሌቪዥን መስኮቶች ላይ የውበት ማዕበል ፈጥረዋል።
ከዚህም ባለፈ፣ የዱንጉዛን የልብስ ጥበብና የሕብር ቀለማት ከዘመናዊ አልባሳት ጋር በማቀናጀት በዓለም አቀፍ የፋሽን ትርዒቶች (Fashion Shows) ላይ የሚያቀርቡ የብሔሩ ተወላጅ ዲዛይነሮች፣ ዱንጉዛን በኩራት መርጠው በማቅረብ ልብሱ የወላይታ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ አርማ እንዲሆን አስችለውታል።
ዱንጉዛ ሐዴ የራሱ የሆነ ልዩ የሕብር ቀለማት ውህደት፣ የቀይ፣ ጥቁር፣ ቢጫ መስመሮችና የነጠብጣብ ጥበብ አሠራር ያለው በመሆኑ፤ በሌሎች የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም አገራት ከሚሠሩ ባህላዊ ጨርቆች ሙሉ በሙሉ የተለየና በሩቅ የሚለይ የውበት ማኅተም ነው።