25/08/2026
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ሦስት አመታት ከ5.1 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ መመለሱ ተገለጸ።
(ሆሳዕና፣ ነሐሴ 12/2018)፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት ከነበረበት 6.021 ቢሊዮን ብር ዕዳ ውስጥ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ መመለስ መቻሉን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ገለጸ።
የቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ዘይቱና ኢብራሂም ባለፉት ሦስት ዓመታት የክልሉን የዕዳ ቅነሳ ሂደት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ክልሉ ሲመሠረት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል።
በወቅቱም የደመወዝና የማኅበራዊ ዋስትና ክፍያዎችን ጨምሮ መደበኛ ወጪዎችን በወቅቱ መፈጸም አለመቻሉንና የካፒታል ፕሮጀክቶችም በክፍያ ችግር ምክንያት መስተጓጎላቸውን ገልጸዋል።
የዕዳ ጫናውን ካባባሱ ምክንያቶች መካከል ከቀድሞው ክልል የተላለፈ የጥሬ ገንዘብ ብድር፣ የማኅበራዊ ዋስትና ውዝፍ ክፍያዎች፣ በተጠናቀቁና በሂደት ላይ ባሉ ፕሮጀክቶች ላይ የቀረቡ የክፍያ ሰርተፊኬቶች በወቅቱ አለመከፈላቸው እና ከአፈር ማዳበሪያ ግዢ ጋር የተያያዙ የብድር ዕዳዎች እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
የዕዳውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የችግሩን መንስኤና መፍትሔ በጥናት በመለየት “ከዕዳ ነፃ የሆነ ክልል መፍጠር” የሚል ራዕይ ተይዞ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ ሥራ መሠራቱን ወይዘሮ ዘይቱና ገልጸዋል።
በዚህም የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ አስተዳደራዊ ወጪዎችን መቀነስ፣ የማዳበሪያ ግዢና የዕዳ አመላለስ ሥርዓትን ማዘመን እንዲሁም የወጪ ቅነሳ ስትራቴጂና መመሪያዎችን ማዘጋጀት ተችሏል።
በተጨማሪም የበጀትና የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር መመሪያዎችን በማዘጋጀትና በመተግበር፣ የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል በማድረግ እና የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓትን በማጠናከር የዕዳ ቅነሳ ሥራው እንዲጠናከር መደረጉን ጠቁመዋል።
ኃላፊዋ እንዳሉት፣ ቀሪ ዕዳውንም ለማጠናቀቅ በትኩረት በመሥራት ላይ ሲሆን፣ ወደፊት አዲስ ዕዳ እንዳይከማች ግልጽ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ነው።
በጁሲ ጥላሁን
ለተጨማሪ መረጃ ‼️
📌 በዌብሳይት https://www.cergcab.et/
📌በቴሌግራም https://t.me/CERGCAB
📌 በፌስቡክ https://www.facebook.com/profile.php?id=100070605291100&mibextid=ZbWKwL
📌 በቲውተር https://twitter.com/CabCerg2678
📌 በቲክቶክ tiktok.com/
📌 በዩቲዩብ https://youtube.com/?si=Ipdg3R3A3hpPQEUV
📌 በኢንስታግራም https://www.instagram.com/cergcab/profilecard/?igsh=MWNseXBlaW05dnM3MA==
ምርጫችሁ ስላደረጋችሁን እናመሰግናለን !!