ስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት/Werabie Town Adminstration Justice Office

  • Home
  • Ethiopia
  • Werabie
  • ስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት/Werabie Town Adminstration Justice Office

ስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት/Werabie Town Adminstration Justice Office ፍትህ የሰላም መሠረት ነው !

የወራቤ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለላቀ አፈጻጸም ያሳዩ ባለሙያዎች የማበረታቻ እውቅና ሰጠ!~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~ነሃሴ 1፣ 2018 ዓ/ም          [...
07/08/2026

የወራቤ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለላቀ አፈጻጸም ያሳዩ ባለሙያዎች የማበረታቻ እውቅና ሰጠ!
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ነሃሴ 1፣ 2018 ዓ/ም
[ወራቤ ]
የወራቤ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በ2018 በጀት ዓመት የላቀ የሥራ አፈጻጸም ላሳዩ ዳኞች፣ ረዳት ዳኞችና ሌሎች ሠራተኞች የማበረታቻ እውቅናና ሽልማት የመስጠት መርሃ ግብር አካሂዷል።

በመር-ሃግብሩ ንግግር ያደረጉት የወራቤ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ካሚል ኤገኖ እንዳሉት በሥራቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ሠራተኞችን ማበረታታትና እውቅና መስጠት የሌሎች ሠራተኞችንም የሥራ መነሳሳት በማጎልበት በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።

የእውቅና አሰጣጡ በፐብሊክ ሰርቪስ መመሪያዎችና በተቀመጡ የምዘና መስፈርቶች መሠረት በተቋሙ በተቋቋመ ኮሚቴ ፍትሃዊና ግልጽ በሆነ ሂደት እንደተከናወነ ተጠቁሟል።

በዳኞች፣ በረዳት ዳኞች፣ በሴት ሠራተኞች እና በአጠቃላይ ሠራተኞች ምድብ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ላስመዘገቡ ተሸላሚዎች የእውቅና ሰርተፍኬትና የገንዘብ ማበረታቻ በመስጠት መርሃ-ግብሩ ተጠናቋል።

የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የግንባር ቀደም ፈፃሚዎች ማትጊያ መርሃ ግብር አካሄደ!  ~~~~~~~~~~~~~~~~~~~ሐምሌ 29፣2018 ዓ/ም [ወራቤ] የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍት...
05/08/2026

የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የግንባር ቀደም ፈፃሚዎች ማትጊያ መርሃ ግብር አካሄደ!
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ሐምሌ 29፣2018 ዓ/ም
[ወራቤ]

የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት በ2018 ዓ.ም በሴክተሩ የዕቅድ አፈፃፀም ላይ ለግንባር ቀደም ፈፃሚዎች እና ባለሙያዎች የዕውቅናና የማትጊያ መርሃ ግብር አካሄዷል።

በዕውቅና መርሃ ግብሩ እንደተነሳው ማትጊያ እና እውቅና ዓላማው በቀጣይ ሁሉም ባለሙያ ተቀራራቢ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ ለማድረስ የውድድር መንፈስ ለመፍጠር ነዉ።

በሌላ በኩል ግንባር ቀደም ፈፃሚዎች ደግሞ ዕውቅናው የሞራል ስንቅ እንዲሆናቸው በማሰብ ይበልጥ እንዲተጉ መሆኑ ተመላክቷል።

አጠቃላይ የተቋም ውጤት ሊመጣ የሚችለው በሁሉም ባለሙያ ድምር አስተዋፅኦ በመሆኑ መርሃ ግብሩ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት ሁሉም ባለሙያ ላይ መነሳሳትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን የጽ/ቤቱ ሃላፊ አሳስበዋል ።

መረጃው የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ነው!

የወንጀል ክስ ይርጋ በኢትዮጵያ************************                መግቢያወንጀል ፈፃሚዎች ለፈፀሙት ጥፋት  በሕግ ፊት መጠየቃቸውና ተገቢውን ቅጣት መቀበላቸው  ተገ...
29/07/2026

የወንጀል ክስ ይርጋ በኢትዮጵያ
************************
መግቢያ
ወንጀል ፈፃሚዎች ለፈፀሙት ጥፋት በሕግ ፊት መጠየቃቸውና ተገቢውን ቅጣት መቀበላቸው ተገቢና አስፈላጊም ነው፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ አንድ እንደተመለከተው በወንጀል ሕጉ መሰረት ወንጀል የተደረጉ ድርጊቶች እና የሚያስከትሉትን ቅጣት በመደንገግ ሰዎች ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡ አሰቀድሞ ቅድመ-ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ቢሆንም ቅድመ-ማስጠንቀቂዎች በቂ ባልሆኑ ጊዜ ወንጀል ፈፃሚዎች ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲታቀቡና ለሌሎችም ማስተማሪያ እንዲሆኑ ማድረግን ግቡ ያደረገ ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ግን በወንጀል ሕጉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ ውስጥ ክስ ሊመሠረት እና አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ የሚገባ ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ክሱ በይርጋ የሚታገድ ይሆናል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የወንጀል ክስ ይርጋን ምንነት፣ በሕግ የተመለከተውን የክስ ይርጋ ዘመን እናአቆጣጠር እንዲሁም የክስ ይርጋ ዘመን መቋረጥና መታገድ በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የወንጀል ክስ ይርጋ ምንነት
የወንጀል ሕጉ የወንጀል ክስ ይርጋን ምንነት በተመለከተ ቀጥተኛ ትርጓሜ ባይሰጥም ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 217 በመነሳት የወንጀል ክስ ይርጋ ማለት በማናቸውም ወንጀል ጉዳይ በግል አቤቱታ ወይም በወንጀል ክስ አቅራቢነት ጉዳዩ በዳኝነት ከመታየት የሚታገድበት በሕግ የተመለከተ ጊዜ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

የመደበኛ ክስ ይርጋ
የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 217 መደበኛ የክስ ማቅረቢያ ጊዜን የደነገገ ሲሆን
• የሞት ፍርድ ወይም የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል በሃያ አምስት ዓመት
• ከአስር ዓመት በላይ እስከ ሃያ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችሉ ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል በሃያ አመት
• ከአምስት ዓመት በላይ እስከ አስር ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል በአስራ አምስት አመት
• ከአምስት አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል በአስር ዓመት
• ከአንድ ዓመት በላይ በቀላል እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል በአምስት ዓመት
• እስከ አንድ ዓመት ቀላል እስራት ለሚያስቀጣ ወይም በመቀጮ ብቻ ለሚያስቀጣ ወንጀል በሦስት ዓመት ውስጥ ክስ ካልቀረበ ክሱ በይርጋ ይታገዳል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመው ሲገኙ የወንጀሎቹ ከፍተኛ ቅጣቶች ተመሳሳይ በሚሆኑበት ጊዜ የአንዱ ወንጀል የክስ ማቅረብያ የይርጋ ዘመን በሁለቱም ወንጀሎች ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆንና የወንጀሎቹ ከፍተኛ ቅጣቶች የተለያዩ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ከሁሉም ከባድ የሆነው ወንጀል የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን በሌሎች ወንጀሎች ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 217(2) ይደነግጋል፡፡

በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስቀጡ ወንጀሎች ይርጋ
በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል ወይም በሌላ ማሟያ የወንጀል ሕግ በግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ እንደሚያስቀጡ የተደነገጉ ወንጀሎች የግል ተበዳዩ ወይም ሕጋዊ ወኪሉ የግል አቤቱታ ካላቀረበ በስተቀር ክስ እንደማይመሰረት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 212 ተደንግጓል ፡፡ ለአንብነትም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 560 የእጅ እልፊት ወንጀል በግል አቤቱታ ሲቀርብ የሚስቀጣ ወንጀል መሆኑ ተደንግጓል፡፡ መሰል በግል አቤቱታ የሚቀርቡ ወንጀሎች የተፈፀመበት የግል ተበዳይ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 213 መሠረት አቤቱታውን ማቅረብ የሚጠበቅበት ሲሆን የእነዚህ በግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎች የክስ ይርጋ ዘመን ሁለት አመት እንደሆነ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 218 ተደንግጓል፡፡

ፍፁም የሆነ የይርጋ ዘመን
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 222 ፍፁም የሆነ የይርጋ ዘመን የተደነገገ ሲሆን በማናቸውም ምክንያት ከላይ የተመለከትነው መደበኛ የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን እጥፍ ጊዜ ካለፈ ወይም በግል አቤቱታ የሚያስቀጡ ወንጀሎች ሲሆኑ ደግሞ ከላይ ከተመለከትነው በግል አቤቱታ የሚያስቀጡ ወንጀሎችን የይርጋ ዘመን በግማሽ የሚበልጥ ጊዜ ካለፈ በወንጀሎቹ ላይ የሚቀርብ ክስ በይርጋ ቀሪ ይሆናል፡፡

የክስ ይርጋ አቆጣጠር
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 219 መሠረት የክስ የይርጋ ዘመን የሚታሰበው የቅጣት ማክበጃ ወይም ማቅለያ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ሳይገቡ በወንጀል ሕግ ልዩ ክፍል የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት መሠረት በማድረግ ሲሆን የተፈፀመው ወንጀል በተለዋጭ ወይም በተደራራቢ ተፈፃሚነት በሚኖራቸውም ቅጣቶች የሚያስቀጣ ሲሆን የይርጋ ዘመኑ የሚታሰበው ከሁሉም ከባድ ለሆነው ወንጀል በወንጀል ሕግ ልዩ ክፍል የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት መሠረት በማድረግ ይሆናል፡፡

የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረውም ጥፋተኛው የወንጀል ድርጊቱን ከፈጸመበት ቀን አንስቶ ሲሆን የወንጀል ድርጊቱ እየተደጋገመ የተፈፀመ ከሆነም የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው የመጨረሻው የወንጀል ድርጊት ከተፈፀመበት ቀን አንስቶ ነው፡፡ የወንጀል ድርጊቱ ለረጅም ጊዜ ሲፈፀም የቆየ ከሆነ ደግሞ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው የወንጀል ድርጊቱ ካቆመበት ቀን ጀምሮ ይሆናል፡፡

የክስ ይርጋ መታገድ
የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 220 የወንጀል ክስ ይርጋ የሚታገድበትን ሁኔታ የደነገገ ሲሆን ይኸውም
በሕግ ወይም በፍሬ ነገር ክሱ እንዳይጀመር ወይም እንዳይቀጥል የሚያግድ መሰናክል ካለ መሰናክሉ እስካለ ድረስ
ክስ ቀርቦ ነገሩ በዳኝነት በመታየት ላይ ከሆነ ወይም በሌላ ችሎት የቀረበ ክስ ሳይፈፀም ተከሳሹ በተከሰሰበት የወንጀል ክስ ላይ ውሳኔ ሊሰጥ የማይገባ በሆነ ጊዜ
የይርጋ ዘመኑ ታግዶ ይቆያል፡፡ መታገዱን ያስከተለው መሰናክል ሲወገድ ግን የይርጋ ዘመኑ ወዲያውኑ መቆጠር ይጀምራል፡፡

የይርጋ ዘመን መቋረጥ
የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 221 እንደሚያመለክተው ከወንጀሉ ወይም ከወንጀለኞቹ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ምርመራ እንዲካሄድ፣ ብርበራ እንዲደረግ፣ መጥሪያ እንዲሰጥ ወይም ክስ እንዲቀርብ የሚሰጥ ትዕዛዝ፣ የሚፈፀም ድርጊት ወይም የሚሰጥ ውሳኔ የይርጋ ዘመኑን መቆጠር ያቋርጣል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ የይርጋ ዘመን እንደገና እንደ አዲስ መቆጠር ይጀምራል፡፡ በድንጋጌው መሠረት የይርጋ ዘመኑ መቋረጥ ፍፁም የሆነ ውጤት የሚኖረው ሲሆን በወንጀሉ ተካፋይ መሆናቸው ለታወቀውም ሆነ ላልታወቀው ሁሉ መቋረጡ ይፀናባቸዋል፡፡ ይህ ማለት የወንጀል ተካፋይ መሆናቸው ወንጀሉ በተከሰተበት ጊዜ ያልታወቁ ሰዎች ያኔ ባለመታወቃቸው ምክንያት የይረጋ መቋረጥ አስመልክቶ ሊኖር የሚችል ልዩነት እንደሌለ መረዳት ይቻላል፡፡

በይርጋ የማይታገዱ ጉዳዮች
በመርህ ደረጃ የወንጀል ድርጊቶች ከተፈፀሙ በኋላ ክስ ለማቅረብ የሚቻልበት የጊዜ ገደብ በግልፅ ሰፍሮ ያለ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ በሌላ ሕግ ከተደነገገ በይርጋ የማይታገዱ ወንጀሎች እንዳሉ ከወንጀል ሕጉ እንቀጽ 216(1) መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ መንግሥት ቀዳሚው ሲሆን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28(1) መሠረት ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች የአገራችን ሕጎች የሰው ልጅ ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑ ወንጀሎች፣ የሰው ዘር የማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር ወይም የኢሰብዓዊ ድብደባ ድርጊቶችን በፈፀሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም።

ማጠቃለያ
የወንጀል ክስ በአንድ በኩል ተጎጂዎች ፍትሕ የሚያገኙበት የሕግ ሂደት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በወንጀል የተጠረጠሩ ወይንም የተከሰሱ ግለሰቦች ነፃነት በሕግ የሚገደብበት ነው። በዚሁ መሠረት የወንጀል ክስ መመስረቻ ጊዜ ገደብ በሕግ ወስኖ ማስቀመት በሁለቱ ተፃራሪ መብቶች መካከል ሚዛን ለመጠበቅ የሚያስችል ነው። ስለሆነም ማንኛውም ክስ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ሊቀርብ ይገባል፡፡

የፍትህ ፎረም የሴቶችን እና ህፃናትን ሁለንተናዊ የመብት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑ ተጠቆመ ።የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የሴቶች እና የፍትህ አካላት የጋራ ፎ...
16/07/2026

የፍትህ ፎረም የሴቶችን እና ህፃናትን ሁለንተናዊ የመብት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑ ተጠቆመ ።

የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የሴቶች እና የፍትህ አካላት የጋራ ፎረም ውይይት አካሄደ ።
ጽ/ቤቱ የ2018 ዓ/ም የ12 ወር የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ከባለድርሻ አካላት በጋራ ግምገማ አደረገ ።

ዛሬ ሐምሌ 09/2018 ዓ/ም
[ ወራቤ ]

የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት በሴቶች እና ህፃናት ዙሪያ በበጀት አመቱ በ 12 ወራቶች የተከናወኑ ተግባራት የዕቅድ የአፈፃፀም ሪፖርት በሴቶች እና ህፃናት ዓቃቤ ህግ በኩል ቀርቦ ከባለድርሻ አካላት ሰፋ ያለ ውይይት ማድረግ የተቻለ ሲሆን ባለድርሻ አካላት በቀረበው የአፈፃፀም ሪፖርት መነሻ በበጀት አመቱ የነበሩ ደካማ እና ጠንካራ ጎኖችን የተመለከተ ሀሳብ፤አስተያየት እንዲሁም ጥያቄ አንስተዋል ። በተነሱ ጥያቄዎች እና ሀሳቦች ላይ የፎረሙ ሰብሳቢ እና የከተማው ፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል አስከትለውም በበጀት አመቱ ከ 30 በላይ አቅመ ደካማ ለሆኑ ሴቶች እና ህፃናት በጠበቃ እና በዓ/ህግ ነፃ የህግ ድጋፍና የጥብቅና አገልግሎት ተጠቃሚ መድረግ መቻሉ ጠቁመዋል ።ከባለድርሻ ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ከግዜ ወደ ግዜ እየተሻሻ የመጣ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ ያልደረሰ በመሆኑ በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ በመጀመርያ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ የተጠቆመ ሲሆን በቅንጅት ሊሰሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በቀጣይ ሊሰራ የሚገባ መሆኑን የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ መድረኩ ተጠናቋል ።

#መረጃው የወራቤ ከተማ አሰተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ነው ።

‎የስልጤ ዞን ፍትህ መምሪያ የ2018 የ12 ወራት እቅድ አፈጻጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር በወራቤ ከተማ ገመገመ!‎‎​ወራቤ (ሀምሌ 2 /2018 ዓ.ም) — ስልጤ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ‎መ...
09/07/2026

‎የስልጤ ዞን ፍትህ መምሪያ የ2018 የ12 ወራት እቅድ አፈጻጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር በወራቤ ከተማ ገመገመ!

‎​ወራቤ (ሀምሌ 2 /2018 ዓ.ም) — ስልጤ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን
‎መምሪያው የዜጎችን መብት ከማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተቋማዊ እምርታዎችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ከታችኛው መዋቅር ከተገኙ ባለድርሻ አካላትና የህዝብ ክንፍ አባላት ጋር በወራቤ ከተማ በጋራ ገምግሟል።

‎​በግምገማ መድረኩ ላይ እንደተገለጸው፤ መምሪያው በተሻሻለው የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ መሰረት የሪፎርም መሳሪያዎችን ወደ ተግባር በማስገባት፣ ተቋማዊ የቲም አደረጃጀቶችን በመፍጠርና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን በየሳምንቱ በመፈተሽ ተገልጋይ ተኮር እና ፈጣን ምላሽ ሰጪ አሰራርን ማስፈን ችሏል።

‎​በበጀት ዓመቱ የወንጀል ፍትህ አስተዳደሩን ውጤታማ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተለይም ከፖሊስ ጋር የሦስትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም የተቀናጀ ስራ መሰራቱ ተገልጿል።

‎በዚህም መሠረት በልዩ ልዩ ወንጀሎች በበጀት ዓመቱ በቀረቡ 1,033 የምርመራ መዛግብት ላይ ዐቃቤ ህግ 100% ውሳኔ በመስጠት የዕቅዱን (99%) በላይ አሳክቷል።

‎​ ወደ ፖሊስ ተመላሽ የሚሆኑ መዛግብትን ከ1% በታች ለማድረግ ታቅዶ ወደ 0% ዝቅ በማድረግ አመርቂ ውጤት መመዝገቡም ተገልጿል።

‎​ በፍርድ ቤት ክርክር ከተደረገባቸው መዛግብት ውስጥ በመዝገብ 98.03%፣ በተከሳሽ ደግሞ 98.37% የማስቀጣት ስኬት የተመዘገበ ሲሆን፤ በከባድ ወንጀሎች ዘርፍ የማስቀጣት ምጣኔው 100% ደርሷል።

‎​ በዓቃቤ ህግ የተጠየቁ የይግባኝ መዛግብት የማሻር ወይም የማሻሻል ምጣኔ በመዝገብም ሆነ በተከሳሽ 100% ሙሉ ስኬት እንደተመዘገበ በሪፖርቱ ቀርቧል።

‎በበጀት​ ዓመቱ የፍትህ ሴክተሩ የሙስና እና የታክስ ማጭበርበር ወንጀሎችን በመታገል ረገድ ታሪካዊ የተባለ የሃብት የማስመለስ ስራ ማከነወኑ ተገልጿል።
‎ለአብነትም:-
‎-​በሙስና ወንጀል፦ በድርድር በተዘጉ 07 መዛግብት ብቻ 9,016,693 (ዘጠኝ ሚሊዮን አስራ ስክስት ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና ሦስት) ብር የመንግስትና የህዝብ ሃብት ማዳን ተችሏል።

‎-​በታክስ ማጭበርበር ወንጀል፦ ባልተከፈለ የሰራተኞች የስራ ግብር እና የኦዲት ጉድለት ሳቢያ ተመዝብሮ የነበረ 26,680,011 (ሃያ ስድስት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሰማንያ ሺህ አስራ አንድ) ብር 100% ለመንግስት ገቢ ተደርጓል።

‎-​በፍትሃብሔር ዘርፍ፦ በበጀት ዓመቱ ውስጥ በድርድር፣ በክስ ሂደት እና በአፈጻጸም በድምሩ 43,859,145.9 ብር ለመንግስት ገቢ የተደረገ ሲሆን፤ ከከተማና ገጠር መሬት ማስመለስ አንጻርም ከፍተኛ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

‎​የሴቶች፣ የህጻናት እና ተጋላጭ ወገኖች መብት ጥበቃ
‎​በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል።

‎በተጨማሪም አቅም ለሌላቸው አረጋውያን፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ዐቃቤ ህግ የህግ ድጋፍ በመስጠት በፍርድ ቤት 99% የመርታት ምጣኔ አስመዝግቧል።

‎​የመድረኩን ማጠቃለያ የሰጡት የስልጤ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሪድዋን ኑሪ፤ በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡት ስኬቶች የሪፎርም መሳሪያዎችን በቁርጠኝነት የመተግበርና የህዝብና የመንግስት ክንፎችን በንቅናቄ የማሳተፍ ውጤት መሆናቸውን ገልጸዋል።

‎​"በበጀት ዓመቱ የተለዩ 11 የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መነሻ በማድረግ 81.8% የሚሆኑትን መፍታት መቻሉንም አንስተዋል።

‎በተለይም የተመዘበረ የመንግስትና የህዝብ ሃብት ማስመለስ፣ በፍትህ ዘርፉ ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከርና የወንጀል መዛግብት ደረጃን ለይቶ በማጥራት 100% የስኬት ምጣኔ ማስመዝገብ መቻሉ ትልቅ እምርታ ነው" ያሉት አቶ ሪድዋን፤ ይሁን እንጂ አሁንም ያልተፈቱ የውስጥ ችግሮች መኖራቸውን አልሸሸጉም።

‎እንደ ተግባርን ያገናዘበ የበጀት ምደባ ማነስ፣ የተሽከርካሪ እጥረት እና እስከ ስር መዋቅር ያሉ ሰራተኞችን አቅም በስልጠና የማሳደግ ውስንነቶች በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚሹ ናቸው ተብሏ።

‎እነዚህን ክፍተቶች በቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመት የውጤት ተኮር (BSC) ዕቅዳችን ውስጥ በማካተት፣ በቁጭትና ከምን ጊዜውም በላቀ ዝግጅት የምንፈታቸው ይሆናል" ብለዋል።

‎​በመጨረሻም፣ በ10 ወረዳዎችና 5 ከተማ አስተዳደሮች የተካሄደውን የድጋፍና ክትትል ቼክ-ሊስት መሠረት በማድረግ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው መዋቅሮች መለየታቸውንና ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን በመጠቆም፤ በቀጣይም የዜጎች ቻርተር ስታንዳርድን የጠበቀ ወጥ የፍትህ አገልግሎት በየደረጃው ለማስፈን ሁሉም ባለሙያ በስራ ገበታው ላይ በቁርጠኝነት ሊተጋ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ያለመያዝ እና ያለመታሰር መብት!*********ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር ምንነትና ይዘት፤ ዋና ዋና አንጓዎች(መገለጫዎች)እንዲሁም እንዲህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራትን የምንከላከልበት የመፍት...
09/07/2026

ያለመያዝ እና ያለመታሰር መብት!
*********
ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር ምንነትና ይዘት፤ ዋና ዋና አንጓዎች(መገለጫዎች)እንዲሁም እንዲህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራትን የምንከላከልበት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተገቢነት ካላቸው የተለያዩ ህጎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ከህግ ውጭ ማሰር (Arbitrariness)

ከህግ ውጭ ማሰር ማለት የህግ የበላይነትን በመጣስ ወይም ህግን እና ስርአትን ባልተከተለ መልኩ ሰዎችን መያዝ እና ማሰር ማለት ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚቴ ደግሞ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አለምአቀፍ መግለጫ በአንቀጽ 9(1) ላይ የተደነገገውን ይዘት ሰፋ ባለ መልኩ እንደሚከተለው ያብራራዋል፡፡
“Arbitrariness is not to be equated with against the law; but must be interpreted more broadly to include elements of inappropriateness, injustice, lack of predictability and the due process of law.”
ይህ የእንግሊዘኛ አነጋገር ወደ አማርኛ ሲመለስ “ከህግ ውጭ ማሰር ማለት በህግ የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ ወይም ህግን በጣሰ መልኩ ሰዎችን ማሰር ብቻ ሳይሆን አግባብነት በሌለው ፣ፍትሃዊነት በጎደለው ፣ሊተነበይ ወይም ሊገመት በማይችል ምክንያት ሰውን መያዝ እንዲሁም ህግን ባልተከተለ አሰራር ማሰርን” በሚያካትት መልኩ በሰፊው መተርጎም እንዳለበት ገልል (ትርጉም የራሴ)፡፡
በተጨማሪም አንድ ሰው በህግ አግባብ የተያዘ ቢሆንም የተያዘበትን ጉዳይ በህግ መሰረት የዋስትና መብት የማያስነፍግ ሆኖ እያለ ፖሊስ ምክንያታዊነት በጎደለው እና አስፈላጊነቱን ወይም ወቅታዊነቱን ሳያገናዝብ ተጠርጣሪው በፍርድቤት እያስቀረበ ተጨማሪ የቀጠሮ ጊዜ በመጠየቅ በእስር እንዲቆይ ማድረግ ከህግ ውጭ ማሰር ነው ሲል ኮሚቴው ይገልጻል፡፡ሆኖም ግን ተጠርጣሪው ከህግ ተጠያቂነት እንዳይሸሽ ለመከላከል የሚደረግ የእስር ተግባር ህገ-ወጥ የእስር ተግባር ልንለው አንችልም፡፡ ለምሳሌ፡- ተጠርጣሪው ከሃገር ለመውጣት ሙከራ ሲያደርግ ከተነቃበት፤መረጃ እና ማስረጃ እንደሚያጠፋ አመላካች ሁኔታዎች ስለመኖራቸው ከተረጋገጠበት ወይም ሀገራት በራሳቸው የወንጀል ስነስርአት ህጎች መሰረት ዋስትናን የሚያስከለክሉ ጉዳዮች ናቸው ተብለው የተዘረዘሩትን ሁኔታዎች ተሟልተው ስለመገኘታቸውን ፍርድቤቱ በማስረጃ አረጋግጦ ተጠርጣሪውን በእስር እንዲቆይ ከታዘዘ ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር ነው ሊባል አይችልም፡፡
ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር መጠኑ ይብዛም ይነስም በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ መኖሩ የማይቀር ነው፤ በተለያዩ ሁኔታዎች እና ዘዴዎችም ሊከናወን ይችላል፡፡ለምሳሌ የተጣሰ የወንጀል ህግ ሳይኖር፣ የህጋዊነት መርህን ችላ በማለት ሰውን መያዝ እና ማሰር፣ምክንያታዊነት እና አግባብነት የሌለው የእስር ተግባር ማከናወን እንዲሁም በአድልዎ እና በገደብ አልባ እስር ሰዎችን ካለ ፍርድቤት ትእዛዝ እና የቅጣት ውሳኔ ለረዥም ጊዜ ማሰርን ሊያካትት ይችላል፡፡እነዚህን ከህግ ውጭ የመያዝ እና የማሰር መገለጫዎች አንድ በአንድ እንደሚከተለው ይብራራሉ፡፡

ኢ- ህጋዊነት (Unlawful Detention)

ሀገራት በህጎቻቸው ላይ በግልጽ ባላካተቱት ምክንያት ሰዎችን የሚያስሩ እና የሚያግቱ ከሆነ ይህ ተግባር የህጋዊነትን መርህን የሚጥስ የአምባገነን መንግሰት ባህርያዊ መገለጫ ነው፡፡ ፖሊስ ወይም ሌላ የህግ አስከባሪ አካል አንድን ግለሰብ ሲያስር እና በቁጥጥር ስር ሥያውል በግለሰቡ የተፈጸመው ድርጊት አስቀድሞ በወንጀል እንደሚያስጠይቅ በህግ ተደንግጎ መሆን አለበት፡፡በህግ በግልጽ ያልተከለከለን “ተግባር”(”ግድፈት”) ሰውን ለመያዝ ሆነ ለማሰር ምክንያት ሊሆን አይችልም ፤ፖሊስ ወይም ሌላ አካል ወንጀል ስለመሆኑ በህግ ባልተደነገገ ጉዳይ አይነ ውሃው ስላልወደደው ወይም ከተለያዩ ምክንያቶች ከሚመነጩ የጥላቻ መነሻዎች መሰረት በማድረግ ብቻ ሰዎችን የሚይዝ ከሆነ ከህግ ውጭ የእስር ተግባር ተከናውኗል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ከላይ ለመግለጽ እንደሞኮርኩት “ኢ-ህጋዊነት” ይባላል፡፡

ኢ-ምክንያታዊነት(Unreasonable Detention)

በህግ የሚያስጠይቁ ተግባራት ተፈፅመው ሲገኙም መያዝ እና ማሰር ግዴታ ላይሆን ይችላል፡፡በተጨማሪም በአንድ ወይም በተለያዩ የወንጀል ተግባራት ተጠርጥሮ የተያዘ ሰውን በግዜ ቀጠሮ ፍርድቤት ማቅረብ ኢ-ህጋዊ ባይሆንም ምክንያታዊ ላይሆን ግን ይችላል፡፡ለምሳሌ አንድ ተጠርጣሪ የእጅ እልፊት ወይም የስድብ እና ማዋረድ ወንጀል መፈጸሙን በተጎጂው አማካኝነት የግል አቤቱታ ቀርቦበት በፖሊስ ከተያዘ በኃላ ወደ ፍርድ ቤት “ጊዜ ቀጠሮ” ማቅረብ አግባብነት አይኖሮውም፤ጠቃሚም ምክንያታዊም አይሆንም፡፡ በመርህ ደረጃ አንድ ተጠርጣሪን ጊዜ ቀጠሮ በማቅረብ እና በዳኛ ፈቃድ በእስር በማቆየት ምርመራን ለማከናወን (Remand in Custody) ፍርድቤትን መጠየቅ የሚያስፈልገው ለመካከለኛ እና ከባድ ወንጀሎች ብቻ ነው፡፡ይህ እንዲሆን የተፈለገበት ዋና ምክንያትም ፖሊስ በከባድ እና በመካከለኛ ወንጀሎች የተጠረጠረን ግለሰብ በዋስትና እንዲለቅ የሚፈቅድለት ህግ ባለመኖሩ እንጂ ሁሉም ተጠርጣሪ ዋስትና ይከለከላል ማለት አይደለም፡፡በህግ መሰረት ዋስትና በሚያስከለክሉ ወንጀሎች ተጠርጥሮ በችሎት የቀረበ ተጠርጣሪን ፍርድቤቱም በህግ መሰረት ብቻ መከልከል ይኖርበታል፡፡የተፈጸመ ወንጀል ስለመኖሩ አጠራጣሪ ከሆነ ወይም ወንጀሉን በተጠርጣሪ ስለመፈጸሙ ፖሊስ መነሻ ማስረጃዎች ማቅረብ ካልቻለም ዋስትናን መፍቀድ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪው የተያዘበት ጉዳይ በህግ መሰረት ዋስትና እንደሚያስከለክል ባይደነገግም የተያዘው ሰው ከሃገር እንዳይወጣ ለመጠበቅ፤ በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የተጠርጣሪው ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ለመከላከል እና ማስረጃዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማደረግ እንዲሁም በሌላ አስፈላጊ እና ህጋዊ ምክንያት ተጠርጣሪውን በእስር ለማቆየት ጠቃሚ እና ምክንያታዊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ዋስትናን ለማስከልከል(ሊፈቀድለትም ላይፈቀድለትም ይችላል) ፍርድቤት ማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡ስለሆነም ጊዜ ቀጠሮን መሰረት በማድረግ የሚከናወን የእስር ተግባር በህግ ምክንያት የሚከናወን መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ምክንያታዊ፣ጠቃሚ እና አግባብነት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡በሌላ አገላለጽ አንድ ግለሰብ በቀላል ወንጀል ተጠርጥሮ ከተያዘ ወይም የተጠረጠረበት የወንጀል ተግባር ቀላል ባይሆንም እንኳን አንድ የወንጀል ተግባር ስለመፈጸሙ እንዲሁም በተጠርጣሪው ስለመፈጸሙ አማላካች መረጃ ከሌለ ግለሰቡን በመያዝ እና በማሰር እንዲሁም በስመ “ጊዜ ቀጠሮ” ወደ ፍርድቤት በማመላለስ እና በማንገላታት የነፃነት መብት ጥያቄ ውስጥ መክተት ትክክል ስለማይሆን መርማሪ ፖሊስ በራሱ መንገድ ህጋዊ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል ፡፡

አድልዎዊነት (Discriminatory Detention)

ከህግ ውጭ ማሰር የተፈፀመውን የወንጀል ተግባር መሰረት በማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህ ተግባር እንደ ሽፋን በመጠቀም በአንጻሩ ሌሎች የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ በአድልዎ ሰዎችን ማሰር ሊያካትት ይችላል፡፡ለምሳሌ ሁለት ግለሰቦች ተመሳሳይ የወንጀል ተግባር መፈጸማቸው በበቂ ማስረጃ ተረጋግጦ እያለ አንዱን በማሰር እና ነጻነቱን እንዲያጣ በማድረግ ሌላኛውን ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሳይታሰር ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ በነፃነት እንደፈለገ መኖር የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡”አድልዎ” በየትኛውም የአለም ክፍል ማስቀረት የማይቻል የሰዎች “አመለካከታዊ በሽታ” ነው፡፡ ሰዎች በዘራቸው/ በብሄራቸው፣በቋንቋቸው፣በፖሊቲካዊ አቋማቸው፣ በሀይማኖታዊ እምነታቸው እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን መድልዎ ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ተግባር የእኩልነት መርህን ጥሰት የሚያስከትል፣መሰረታዊ መብቶችን እና ነጻነቶችን አደጋ ላይ የሚጥል ህግን የሚቃረን አሰራር ነው፡፡ለምሳሌ፡- በኢፌድሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 25 ላይ የተደነገገውን የእኩልነት መብትን በመጣስ የሚከናወን ማንኛውም የመያዝና የማሰር ተግባር አድልዎ መሰረት በማድረግ የተከናወነ ከህግ ውጭ እስር ነው ልንለው እንችላለን፡፡ማንኛውም ግለሰብ በህግ ክልከላ ያልተደረገበትን ተግባር(ግድፈት) በወንጀል ተጠርጥረኃል በሚል ሽፋን በዘሩ፣ በብሄሩ፣ በቀለሙ፣ በጾታው፣ በቋንቋው፣ በሃይማኖቱ፣ በማህበራዊ አመጣጡ፣ በድህነቱ/በሃብቱ፣በትውልድ ቦታው ፣በፖለቲካዊ አመለካከቱ ወይም በሌላ ግላዊ አቋሙ ምክንያት ብቻ ሊያዝ ወይም ሊታሰር አይገባም፡፡

ገደብ አልባ እስር (Indefinite Detention)

ካለምንም የፍርድ ቤት ውሳኔ በውል ተለይቶ ላልታወቀ ጊዜ ሰዎችን መያዝ እና ማሰር ከህግ ውጭ የማሰር ተግባሮች አንዱ ገፅታ ነው ፡፡ከዚህ በተጨማሪም ክስ ሳይቀርብ ወይም በዋስትና ጉዳይ ፍርድቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥ ሳይደረግ በፖሊስ ወይም በሌላ ባለስልጣን ትእዛዝ ብቻ ለረዥም ጊዜ ሰውን ማሰር(Detaining people with out the possibility of Charge and Bail) ገደብ አልባ እስር ሊባል ይችላል፡፡ ፍርድቤቱ ከህግ ውጭ የታሰረን ግለሰብ ከእስር እንዲለቀቅ ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም ላልታወቀ ጊዜ የእስር ሂደቱ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ይህ ማለት በመንግስት ባለስልጣናት የሚፈጸሙ የእስር ተግባራት ብዙ ጊዜ ከፍርድቤት ትእዛዝ እና የቅጣት ውሳኔ ውጪ ስለሚከናወኑ ታሳሪዎች ከእስር የሚፈቱበት ጊዜ ሊያውቁ አይችሉም ፤ምክንያቱም ሁሉም ነገር በአንድ ባለስልጣን(ፖሊስ፣አቃቤ ህግ፡የፖለቲካ ሹመኛ ወዘተ…) ፈላጭ ቆራጭነት እና አምባገነናዊ ትእዛዝ ብቻ ስለሚከናወን ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንድ ወቅት በሀገረ ሩዋንዳ “በዘራቸው ምክንያት ኢ-ሰብአዊ አያያዝና ስቅያትን የሚያስከትል የድብደባ ወንጀል (Torture) የተፈጸመባቸው ዜጎች(በቱሲ እና በሁቱ መካካል በነበረው የእርስበርስ ጦርነት ምክንያት ቱሲዎች የደረሰባቸውን በደል በማስመልከት) መንግሰትን በመቃወማቸው ምክንያት ካለምንም የፍርድቤት ውሳኔ በሀገሪቷ መንግስት ትእዛዝ ለረዢም ጊዜ መታሰራቸው የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 6 ን የሚጥስ ከህግ ውጭ የተከናወነ ተግባር ነው” ሲል የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች አጠቃላይ የአንድ ሀገር ደካማ ስርአት እና ተቋማዊ አወቃቀር የፈጠሩት ችግር ሊሆን ይችላል፤ወይም ደግሞ ለሙያው ታማኝ የሆነ፣ነጻ እና ገለልተኛ ፖሊስ ፣አቃቤ ህግ፣ዳኛ ወይም ጠበቃ ያለመኖር ችግር የፈጠራቸው ሊሆንም ይችላል፡፡ቁርጠኛ የፖለቲካ አመራር ያለመኖር ወይም የአንድ መንግስት አምባገነናዊ ባህሪ የወለዳቸው ችግሮችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ስለሆነም በአለምአቀፍ ህጎች ሆነ በሀገራት ብሄራዊ ህጎች የሰዎች መሰረታዊ መብቶች እና ነፃነቶችን የሚያከብር እና የሚያስከብር የሰለጠነ የህግ ባለሙያ መገንባት ፤የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሲያጋጥምም የህግ ተጠያቂነትን የሚዘረጉ የህግ ማእቀፎችና ጠንካራ ተቋማት እንዲኖሩ ማድረግ፤የመብቶቹ አከባበር እና አፈፃጸም የሚከታተል ወይም የሰብኣዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትም የሚጠየቁበት ሁኔታ በህግ መሰረት በአግባቡ የሚከታተል ፣የሚያስፈጽም ፣የሚተረጉም እና ተገቢውን ቅጣት እና የእርምት እርምጃ የሚወስድ ተቋማዊ እና ግለሰባዊ ነጻነቱን የጠበቀ የፍትህ አካል መኖር የግድ ይላል፡፡
በዚሁ መሰረት ሁሉም የአለም ሀገራት የሁሉም ሰዎች የነጻነት እና የአካል ደህንነት መብት በእኩል እንዲያከብሩ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኙ መብቶችን ጥሰው የተገኙ ሀገራት አለም አቀፍ ህጋዊ ሃላፊነት(Universal Legal Responsibility) ያስከትልባቸዋል፡፡ የነጻነት መብት ማለት ማንኛውም ሰው የእለት ተእለት የሂወት እንቅስቃሴው ውስጥ ካለምንም መሸማቀቅ እና ጣልቃ ገብነት ሙሉ የመንቀሳቀስ እና የመኖር መብት የሚጎናፀፍበት የተፈጥሮ መብት ሲሆን የደህንነት መብት ማለት ደግሞ ማንኛውም ሰው በሂወቱ ላይ ሊደርስበት የሚችል አደጋ ወይም ስጋት/ፍርሀትን መከላከል እና በነጻነት እንዲንቀሳቀስ መንግስታዊ ጥበቃ ወይም ዋስትና የሚያገኝበት ሆኖ የተያዘ ሰውም ቢሆን የአካል ደህንነቱን እንዲጠበቅ መንግስት እና የመንግስት አካላትን ግዴታ ውስጥ ማስገባትን የሚጨምር ተፈጥሮኣዊ መብት ነው፡፡በዚሁ መሰረት ሀገራት የማንኛውም ሰው የነፃነት እና የደህንነት መብት ለማክበር እና ለማስከበር ምክንያታዊ እና ተገቢ እርምጃ እንዲወስዱ አለም አቀፍ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡የነፃነት እና የደህንነት መብቶች በአጠቃላይ እንዲሁም እነዚህ መብቶችን የሚገደብባቸው ህጋዊ ምክንያቶችንና ልዩ ሁኔታዎችን ከአለም አቀፍ ህጎች፣ ከኢፌድሪ ህገ መንግስት እና ከወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ አንፃር እንደሚከተለው ይቃኛሉ፡፡

አለም አቀፍ እና ብሄራዊ የህግ ማእቀፎች

ሀ) የሰብአዊ መብቶች ሁሉ-አቀፍ መግለጫ
ይህ ሁሉ አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ በአንቀጽ 3 ላይ እያንዳንዱ ሰው የሕይወት ፣የነጻነት እና የተሟላ የድህንነት መብት እንዳለው ያሰፈረ ሲሆን በአንቀፅ 9 ደግሞ ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ ፣ሊታሰር ወይም ሊያዝ አይችልም በማለት በግልፅ ደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ይህ ድንጋጌ በሌላ መልኩ ስናነበው-- ማንኛውም ሰው በዘፈቀደ ነፃነቱን ማጣት አይችልም የሚል አጠቃላይ መርህ ደነገገ እንጂ ሀገራት በህጎቻቸው ላይ በግልጽ ተለይተው በተቀመጡ ምክንያቶች እና በተዘረጉ የአያያዝ ስርአቶች መሰረት መያዝ ወይም ማሰር ክልክል ነው ማለት ግን አይደለም፡፡
ለ) የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አለምአቀፍ ቃልኪዳን ፡-
በዚህ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 9(1) ላይ በግልፅ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው የግል ነጻነቱ እና ደህንነቱ እንዲረጋገጥለት መብት አለው፡፡ማንኛውም ሰው ከህግ ውጭ አይያዝም ፣አይታሰርም ፡፡ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ምክንያት እና ስርአት ውጭ የግል ነፃነቱ አይገፈፍም፡፡ የተባበሩት የአለም ሃገራት ደርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ይህን አንቀጽ መሰረት በማድረግ የሰጣቸውን ትርጉሞችና አስተያየቶችን በጥቂቱ እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡
ምሳሌ አንድ፡-አንድ ግለሰብ በከባድ የወንጀል ተግባር ተጠርጥሮ የተሰወረ ወንድሙን ፈልጎና መርቶ እንዲያስዝ ቢገደድም መፈጸም ባለመቻሉ ምክንያት ብቻ ለአንድ ወር ቢታሰር ከህግ ውጭ መያዝና ማሰር በመሆኑ አግባብነት የሌለው ተግባርና የህጋዊነት መርህን የሚጥስ ነው ብሏል፡፡
ምሳሌ ሁለት፡-አንድ ግለሰብ የመያዣ ትእዛዝ ሳይቆረጥበት ወይም መጥርያ ሳይደርሰው ከተያዘ በኃላ ወደ ፍርድቤት ሳይቀርብ ለረዥም ጊዜ ማሰር የግለሰቡን የነፃነት መብትን ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ህገ-ወጥ የመያዝና የማሰር ተግባር ነው ብሏል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንድ ግለሰብ በህጋዊ መልኩ ከተያዘ ወይም ከታሰረ በኃላም ቢሆን ፍርድቤቱ መለቀቅ አለበት ብሎ ካዘዘ በኃላ በፖለቲካ ባለስልጣናት ወይም በሌላ አካላት ትእዛዝ ምክንያት በእስር ላይ እንዲቆይ ማድረግ ኢ-ህጋዊ ተግባር ነው ብሏል፡፡
ሐ) የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ቻርተር (አንቀጽ 6)
ማንኛውም ሰው ነፃነቱ እና አካላዊ ደህንነቱ ተጠብቆለት የመኖር መብት አለው፡፡ቀድሞ በህግ በተደነገጉት ሁኔታዎች እና ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ነፃነቱን እንዲያጣ ሊደረግ አይችልም፡፡ በተለይም ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊታሰር ወይም ሊያዝ አይችልም፡፡
የአውሮፓ ሰብአዊ መብቶች መግለጫ እና የአሜሪካ ሃገራት ሰብኣዊ መብቶች መግለጫም ከላይ ከተጠቀሱት የህግ ማእቀፎች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ማንኛውም ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ ሆነ ሊታሰር እንደማይችል ደንግገዋል፡፡
መ) የኢፌድሪ ህገ መንግስት
የኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 17(1) ስር እንደተመለከተው በህግ ከተደነገገው ስርአት ውጭ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን /ቷን አያጣም /አታጣም በማለት ደንግጓል ፤በተጠቃሹ አንቀጽ ንኡስ ቁጥር ሁለት ላይም ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ስርአት ውጭ ሊያዝ ፣ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሣይፈረድበት ሊታሰር አይችልም በማለት ደንግጓል፡፡
ሠ)የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአት
ማንኛውም ሰው በህግ መሰረት ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው አንደኛ ሊያስይዘው ወይም ሊያስጠይቀው የሚችል የወንጀል ተግባር መፈጸሙ ሲረጋገጥ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የተጠረጠረበትን/የተከሰሰበትን የወንጀል ተግባር በህግ መሰረት የሚያስይዘው/የሚያሳስረው መሆኑን ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ አንቀጽ 25፣ 26 እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው የስነስርአት ህጉ ድንጋጌዎች ይዘት እና መንፈስ ያስረዳሉ፡፡
በረቂቅ ደረጃ ያለው የወንጀል ስነስርአት እና የማስረጃ ህግ በአንቀጽ 8 ላይ ስለመያዝና ማሰር በሚል ርእስ ስር እንደተመለከተውም “ማንኛውም ሰው ወንጀል ስለመፈፀሙ በቂ ጥርጣሬ ሳይኖር ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረደበት ሊታሰር አይችልም” በማለት ደንግጓል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት አጠቃላይ መንግስታዊ ግዴታዎች የሚያስገነዝቡን፤ በመርህ ደረጃ ማንኛውም ሰው ካለ ምንም ህጋዊ ምክንያት ሊያዝ ወይም ሊታሰር እንደማይችል የሚያስረዱና የተፈጥሮ ችሮታ የሆኑ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች እንዲከበሩ እውቅና የሚሰጡ አለም አቀፍ ግዴታዎችና ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ህገ-መንግስቱን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህጎችም ከአለም አቀፍ ህጎችጋር ተመሳሳይ አላማ በመያዝ የተቀረፁ ናቸው፡፡
በዚሁ መሰረት የነጻነት መብት ህገ መንግስታዊ መብት ከመሆኑ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው አለም አቀፍ ህጎች እና በሌሎች ዝርዝር የስነ ስርአት ህጎቿ ላይ በግልጽ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ይህ መርህ በኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 17፣ በአለም አቀፍ ፖሊቲካ እና ሲቪል ስምምነት ሰነድ አንቀጽ 9፤በሰብአዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ አንቀጽ 3 እና 9፣በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ አንቀጽ 25 እና 26 እንዲሁም በረቂቁ የወንጀል ስነ ስርአት እና የማስረጃ ህግ አንቀጽ 8 ላይ እና ሌሎች ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ህጎች ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ግን አንድ ግለሰብ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ የሚፈለግ ከሆነ አጠቃላይ የህብረተሰቡ ሰላም እና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል በህግ ተለይተው በተቀመጡ ስነስርአታዊ አካሄዶች መሰረት መያዝ ወይም ማሰር ይቻላል፡፡
ይህ ማለት አንድ ግለሰብ ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው በአንድ ፖሊስ የግል ፍላጎት ወይም በባለስልጣን ፈላጭ ቆራጭነት ወይም በማንኛውም ግለሰብ ጥላቻዊ ጥቆማ ወይም ቂም በቀልነት ሳይሆን ጉዳዩ በአንድ ምክንያታዊ ታዛቢ ሰው ሲለካ እንዲሁም በግልጽ እና በሚያሳምን ሁኔታ እውነታዎቹ ሲታዩ እና ማስረጃዎቹ ሲመዘኑ ወይም ሲመረመሩ ለማስያዝ እና ለማሳሰር በቂ ሆኖው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ዝቅተኛ የህግ ግንዛቤ እና እውቀት ባለበት እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ሃገራት ማሰር እና መያዝ ካለምንም ገደብ እና ቅድመ ሁኔታ በዘፈቀደ ለፖሊስ የተሰጠ ስድ እና ያልተገራ ስልጣን የሚመስለው የህብረተሰብ ክፍል ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ ብዙዎቻችን ደንብ ልብስ ለብሶ ካቴና ይዞ የመጣ ፖሊስ ሁሉ ህግን እያስከበረ ነው የሚል የተሳሳተ ህብረተሰባዊ እምነት እና ልማዳዊ አሰራር ስለምናራምድ እና ለዚሁ ጸረ-ነጻነት የሆነውን አሰራር ተገዢ ስለምንሆን ለመብታችን ስንታግል አይታይም፡፡ ይህ ስል ግን ራሳችንን ከህግ ውጭ በማድረግ ለሚደርስብን ኢ-ፍትሀዊ ተግባር ኢ-ፍትሀዊ ግብረመልስ እየሰጠን ወደአላስፈላጊ እሰጣ እገባ እና ንትርክ ውስጥ በመግባት በህግ አስከባሪ አካላት ላይ ችግር የመፍጠር መብት አለን ለማለት ሳይሆን ብያንስ ግን በህግ እና በመብታችን ላይ የተሟላ እውቀትና ግንዛቤ ኖሮን ህግን መሰረት በማድረግ መጓች እና ንቁ ዜጋን በመፍጠር አምባገነን መንግስትን እና ፈላጭ ቆራጭ ባለስልጣንን የምንከላከልበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ መንግስት ጠንካራ ስርአት እና ተቋም እንዲመሰርት፤ተጠያቂነት እና ሃላፊነት መሰረት በማድረግ ስራውን የሚያከናውን ባለሙያ(ባለስልጣን) እንዲኖር መንግስት በአንክሮና በቁርጠኝነት እንዲሰራ በር ለመክፈት ያስችላል፡፡
ስለሆነም አንድ ግለሰብ ሊታሰር የሚችለው በልዩ ሁኔታ በህግ መሰረት በግልጽ ተለይተው በተቀመጡ ዝርዝር ምክንያቶችና አካሄዶችን በጥብቅ በመከተል ብቻ ሲሆን ኢትዮጵያም ከአለም አቀፍ ህጎች ጋር ተመሳሳይ አቋም እና ይዘት ያላቸው ድንጋጌዎች በብሄራዊ ህጎቿ ላይ አስፍራለች፡፡ በዚሁ መሰረት አንድ ግለሰብ ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው በሚከተሉት ምክንያቶች ብቻ ነው፡፡

ሀ) በወንጀል ተግባር ሲጠረጠር፡-

ማንኛውም ሰው ወንጀል ሊመፈጸም በሙከራ ላይ እያለ ፣ወንጀል ስለመፈፀሙ በቂ ጥርጣሬ መኖሩ ወይም የወንጀል ተግባርን ሲፈፅም እጅ ተፍንጅ ከተያዘ፣ወይም በህግ መሰረት ወንጀልን ለመፈጸም የመሰናዳት ተግባራት ያስቀጣሉ ተብለው በተደነገጉ ጉዳዮችን እንዳይፈጸሙ ለማስቆም/ለመከላከል በማሰብ እና ለዚሁም በቂ በሚባል ሁኔታ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖር በህግ ተለይተው በተቀመጡ ስነስርአታዊ አካሄዶችን በጥብቅ በመከተል መያዝ ወይም ማሰር ይቻላል፡፡በኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 17 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰው ካለ ፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ሊታሰር ወይም ሊያዝ አይችልም ፡፡ሆኖም በህጉ መሰረት ተለይተው በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት አንድ በወንጀል የሚፈለግ ሰው ካለ፤ በፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ በቁጥጥር ስር ሊውል እንደሚችል፡ በዚሁ የህገ-መንግስት ድንጋጌ ንኡስ አንቀጽ 2 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ አንድ በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረ ሰው የሚያዝበት ስርአትስ እንዴት ነው የሚል ጥያቄ መመለሱ የሚያስፈልግበት ዋና ምክንያት በአንድ በኩል የተገራ የፖሊስ ተግባር እንዲኖር እና ህግን የማስከበር ሃላፊነት በአግባቡ እንዲሰፍን የሚያደርግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የልተገራና እና ልቅ የሆነ ነፃነትን ከመገደብ አንጻር የሚፈጥረው ሚዛናዊ አካሄድ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ስለሚኖሮው በህግ የሚፈለግ ሰው የሚያዝበት አግባብ አጠር አጠር ባለ መልኩ እንደሚከተለው ማየቱ ይጠቅማል፡፡

1. መጥርያ

በየትኛውም የወንጀል ተግባር የተጠረጠረ ግለሰብን በመጀመርያ ደረጃ ፖሊስ በመጥርያ እንዲያቀርብ ማድረግ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ለምሳሌ ፖሊስ ፍርድቤት ድረስ በመሄድ ፍቃድ ለማግኘት የሚያባክነው ጊዜ እና ጉልበት ይቀንስለታል፤ተጠርጣሪው በመጥርያ የሚቀርብ ከሆነ በፖሊስ ላይ ሊያደርሰው የሚችል ተቃውሞ ሆነ ለህግ አልታዘዝም ባይነት አይኖርም፤በሌላ አገላለጽ ተጠርጣሪው በፍላጎቱ እስከ ቀረበ ድረስ በህግ አስፈጻሚ አካላት ላይ ሊያደርሰው የሚችል ጥቃት ወይም ተቋውሞ አይኖርም…. ወዘተ፡፡ እንደ እነ እንግሊዝ የመሳሰሉ የኮመን ሎው የህግ ስርአት የሚከተሉ ሃገራት በየትኛውም የወንጀል ተግባር የተጠረጠረ ግለሰብ በፖሊስ መጥርያ ከቀረበ ፍርድቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ አይታሰርም፡በሙሉ ነፃነት እና ካለምንም ገደብ በውጭ ሁኖ ወደ ፍርድቤት እየተመላለስ ጉዳዩን እንዲከታተል ፍርድቤቱ ይፈቅድለታል፡፡ በኢትዮጵያ የህግ ስርአት ግን ለቀላል ወንጀሎች ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥሮ በፖሊስ መጥርያ መሰረት ቢቀርብም ሊታሰር ወይም በገደብ-ለምሳሌ በዋስትና -ሊለቀቅ ይችላል እንጂ በፖሊስ መጥርያ በመቅረቡ ብቻ ላለመታሰሩ ዋስትና ሊሆነው አይችልም ፡፡መርማሪ ፖሊስ በየትኛውም የወንጀል ተግባር የተጠረጠረን ግለሰብ በመጥርያ ይቀርባል ብሎ ግምት ከወሰደ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአት አንቀጽ 25 መሰረት መጥርያ ማድረስ ይችላል፡፡በዚሁ መሰረት የቀረበ ተጠርጣሪ የተጠረጠረበትን የወንጀል ተግባር ክብደቱ እና ቅለቱ ታሳቢ በማድረግ ፖሊስ በራሱ ህጋዊ ስልጣን ተጠርጣሪውን በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአት አንቀጽ 28 መሰረት በዋስትና መልቀቅ ወይም ተጠርጣሪውን ከተያዘበት ሰአት ጀምሮ በሚቆጠር በ 48 ስአታት ውስጥ ወደ ፍርድቤት በማቅረብ በዋስትና ላይ እልባት እንዲያገኝ ከልብ የመነጨ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡

2. የመያዣ ትእዛዝ

ፖሊስ የመያዣ ትእዛዝ በማውጣት ተጠርጣሪን መያዝ የሚችለው ተጠርጣሪው በመጥርያ ለመቅረብ ፍቃደኛ ሣይሆን ሲቀር ወይም እንደማይቀርብ እርግጠኛ ሲሆን ብቻ መሆን አለበት፡፡የመያዣ ትእዛዝ የሚፈቀድበት መደበኛ ስነ ስርአት በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ቁጥር 53 እና 54 ላይ በግልጽ የተደነገገ ሲሆን በዚሁ መሰረትም ማንኛውም ፍርድቤት ትእዛዙን የመስጠት ስልጣን ቢኖሮውም በመርማሪ ፖሊስ የቀረበ ጥያቄ ሳይኖር ግን መስጠት አይችልም፡፡መርማሪ ፖሊስ የመያዣ ትእዛዝ መጠየቅ የሚችለውም አንደኛ ተጠርጣሪው በፍርድቤት መቅረቡ ፍጹም አስፈላጊ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ተጠርጣሪው ወደ ፍርድቤት የሚቀርብበት ሌላ አማራጭ አለመኖሩን መረጋገጥ ሲቻል ብቻ ነው፡፡የተጠርጣሪው መቅረብ ፍጹም አስፈላጊነት(The criterion of Absolute Necessity) እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠበት ዋና ምክንያት ተጠርጣሪው የወንጀል ድርጊቱን ስለመፈጸሙ የሚያሳዩ መነሻ ማስረጃዎች (Minimum standards of evidences) ስለመኖራቸው በገለልተኛ ፍርድቤት እንዲረጋገጥ በማሰብ ነው፡፡በሌላ አነጋገር ማንኛውም ሰው በስስ ማስረጃ ወይም ካለምንም ማስረጃ እንዳይያዝ /እንዳይታሰር ለመከላከል ፍርድቤቱ በመርማሪ ፖሊስ በኩል የሚቀርብ የእስር መያዣ ማመልከቻን በአግባቡ እንዲመረምር ስለሚፈለግ ነው፡፡ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ማረጋገጡ ያስፈለገበት ዋና አላማ ደግሞ ተጠርጣሪው መርማሪ ፖሊስ የሚያደርስለትን መጥርያ ሣይቋወም ህግን አክብሮ የሚቀርብበት ሁኔታ ካለ እድሉን ለመጠቀም ሲሆን ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የመጥርያ ጠቀሜታ ከአዘገጃጀቱ፣ አደራረሱና ውጤቱ አንፃር ሲለካ በፍትህ ዘርፉ ላይ የላቀ አስተዋፅኦ ስላለው የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ከመውጣቱ በፊት መጥርያ የመጀመርያ አማራጭ እንዲሆን ስለተፈለገ ነው፡፡

3. ያለመያዣ ትእዛዝ

ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ ካለ ፍርድቤት ትእዛዝ ሊያዝ እንደሚችል በህገ መንግስቱ አንቀፅ 17 እና በተለያዩ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ድንጋገጌዎች ላይ በግልፅ ሰፍረው እናገኛቸዋለን፡፡ከእነዚህ መካከል ሊጠቀሱ የሚችሉት የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች (Flagrant Offences) ናቸው፡፡የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች በትርጉም ደረጃ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ቁጥር 19 እና 20 ላይ የተቀመጡ ሲሆን ስነስርአታዊ ውጤታቸው ደግሞ በአንቀጽ 20 እና 50 ላይ በግልጽ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡በተጨማሪም ተጠርጣሪው ወንጀሉን ሲፈጽም እጅ ተፍንጅ ባይያዝም እንኳ የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ እስከሚወጣበት ድረስ ሊሰወር ወይም ሊያመልጥ ይችላል ተብሎ ለመገመት የሚያስችሉ አመላካች(ጠቋሚ) መረጃዎች ካሉ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ባገኘበት ቦታ መያዝ ይችላል፡፡ለምሳሌ ከሃገር ለመሸሽ ሙከራ ሲያደርግ ከተያዘ ፖሊስ ለጊዜው የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ማውጣት ሳይጠበቅበት ሌሎች በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ ላይ የተቀመጡትን ህጋዊ ጥንቃቄዎችና እርምጃዎችን በመከተል ከፍትህና ህግ ለማምለጥ የሚሞክር ማንኛውም ተጠርጣሪን መያዝ ይችላል፡፡
ለ) ስልጣን ባለው ፣ ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ ፍርድቤት ሲፈረድበት ወይም ሲወሰንበት
አንድ ተጠርጣሪ በአንድ የወንጀል ተግባር ተጠርጥሮ ህጉና ስነ ስርአቱ በሚፈቅደው መሰረት በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉ በፍርድቤት የመጨረሻ ውሳኔ ተወስኖበታል ማለት አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው በከባድ የወንጀል ድርጊት እንኳ ቢጠረጠር ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠርና ወደ ፍርድቤት ለማድረስ የሚፈጀው ጊዜ ሣይታሰብ በ48 ስአታት ውስጥ ፖሊሰ ተጠርጣሪን ወደ ፍርድቤት የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡አንድን ተጠርጣሪ ወደ ማረሚያቤት እንዲላክ ፣በነፃ እንዲለቀቅ፣ በገደብ እንዲፈታ ወይም በዋስትና እንዲወጣ ማዘዝ የሚችለው ስልጣን ያለው፣ነፃና ገለልተኛ የሆነ ፍርድቤት ሲወስን ብቻ ነው፡፡በሌላ አነጋገር የፖሊስ መጥርያ ደርሶት በፍላጎቱ የቀረበ ተጠርጣሪ ይሁን በፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ወይም ካለምንም የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ለፖሊስ እጁን የሰጠ ተጠርጣሪ ነፃነቱን ተገፎ ወደ ማረሚያ ቤት የሚላከው ፍርድቤቱ እንዲታሰር ሲወስንበት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የሚከናወን የእስር ተግባር ህጋዊ አይደለም፡፡

የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የህዝብ ክንፍ የሐይማኖት አባቶች ፤ከተቋሙ ማኔጅመንት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ አካሄደ ።~~~~~~~~~~~~~~~~~...
02/07/2026

የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የህዝብ ክንፍ የሐይማኖት አባቶች ፤ከተቋሙ ማኔጅመንት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ አካሄደ ።
~~~~~~~~~~~~~~~~~~------------------
ሰኔ 25/2018 ዓ/ም
[ወራቤ]
የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት የ2018 ዓ/ም የተቋሙን የ12 ( አስራ ሁለት ) ወር ዕቅድ አፈጻጸም ከባለድርሻ አካላት በጋራ ገመገመ ።
ተቋሙ ከሐይማኖት አባቶች፤ከአካል ጉዳተኛ ማህበራት ተወካይ፤ከወጣቶች ፌዴሬሽን ተወካዮች፤የሴቶች ፌዴሬሽን እና ማህበራት ተወካዮች ከህዝብ ክንፍ፣ከጠበቆች ማህበር ተወካይ እንዲሁም ከተቋሙ ማኔጅመንት አባላት ጋር በተቋሙ በ2018 ዓ/ም በአስራ ሁለት ወራት የተከናወኑ ዋናዋና ተግባራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ከባለድርሻ አካላት፤ከተሳታፊዎች ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች ሀሳብ፤አስተያየት ተነስቶ በተነሱ ሀሳብ አሰተያያት እና ጥያቄዎች የተቋሙ ማኔጅመንት አባላት እና የጸ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አክመል ጀማል ማጠቃለያና ምላሽ ሰጥተዋል ።
በመጨረሻም የተቋሙን አፈፃፀም መነሻ በማድረግ ምዘና በህዝብ ክንፍ ተከናውኖ በቀጣይ ከሚመለከታቸው የፍትህ ባለድርሻ ተቋማት በቅንጅት የሚሰራውን ስራ በማጠናከር ፤ከማህበረሰቡ ከህዝብ ክንፍ ወቅቱን ጠብቆ መረጃ በመለዋወጥ ተቀናጅቶ በመስራት ተቋሙን ወደ ተሻለ የአፈፃፀም ደረጃ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ መድረኩ ተጠናቋል ።

መረጃው የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ነው ።

ህጻናትን ማዕከል ያደረጉ ክርክሮች የልጆችን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ መስተናገድ ያለባቸው ስለመሆኑ=====================ሕፃናቱ ከእድሜያቸው ለጋነት በተያያዘ ለአደጋ የተጋለጡ የሕብረ...
10/06/2026

ህጻናትን ማዕከል ያደረጉ ክርክሮች የልጆችን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ መስተናገድ ያለባቸው ስለመሆኑ
=====================
ሕፃናቱ ከእድሜያቸው ለጋነት በተያያዘ ለአደጋ የተጋለጡ የሕብረተሰብ አካላት /vulnerable groups/ የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ ይህንኑ አደጋ ለመከላከል እና የተለየ ድጋፍና እንክብካቤ የማድረጉ ሥራ የተሣካ ይሆን ዘንድም የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች መብትና ደህንነት በሚመለከት የተለዩ ስምምነቶች በአለምና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተፈርሞ እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡ ከስምምነቶቹ ውስጥም የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን እና የአፍሪካ ሕፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሐገራችን ኢትዮጵያ የሕፃናት መብቶች ኮንቬሽንን ህዳር 29 ቀን 1984 ዓ.ም፣ የአፍሪካ ሕፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር ደግሞ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 02 ቀን 2002 ዓ.ም አጽድቃለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሕፃናትን መብትንና ደህንነት በሚመለከት የፌዴራሉ ሕገ-መንግሥት፣ የክልል ሕግጋተ- መንግሥታት እና ሌሎች ሕጎች አሉ፡፡ በዓለም አቀፍ በአህጉርና በአገር ደረጃ ሕፃናትን አስመልክቶ በስራ ላይ ያሉ እነዚህ ሕጎች ደግሞ መሠረታዊ መርሆዎችን የያዙ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን መሠረታዊ ከሆኑት መርሆዎች ውስጥ አንዱ ሕፃናትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ለሕፃናት ጥቅምና ደህንነነት /the best interest of the child/ ቅድሚያ መስጠት የሚለው ስለመሆኑ የአንቀጽ 3.1 ድንጋጌ ሲያሣይ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተርም በአንቀጽ 4.1 ድንጋጌ ስር ይህንኑ አካትቶ ይዟል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥትም ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸውን የዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የአገሪቱ የሕግ አካል መሆናቸውን በአንቀጽ 9/4/ ስር ከመደንገጉና በሕገ-መንግሥቱ በስፋት ሽፋን የተሰጣቸው መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ሀገሪቱ ከተቀበለቻቸውና ዓለም አቀፍ የሠብአዊ መብቶች ሕግጋት፣ ስምምነቶች ወይም ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ መተርጎም የግድ ስለመሆኑ ከማስቀመጡም በተጨማሪ የሕፃናትን ልዩ ችግር ከግምት ያስገቡ የተለያዩ ንዑስ ድንጋጌዎችን የያዘ ድንጋጌ በአንቀጽ 36 በአንቀጽ 13/2/ አስፍሯል፡፡ በተለይም የአንቀፁ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ሕፃናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ ሁሉ የመንግሥታዊ ወይም የበጎ አድራጎት ተቋማት እንዲሁም ፍ/ቤቶችና የአስተዳደር ባለስልጣናት ወይም የሕግ አውጪው አካላት የሕፃናትን ደህንነት በቀድሞ ትጋት ሊያስቡበት የሚገባ ስለመሆኑ አጽንኦት ባለው መንፈስ፤ በአስገዳጅነት ደንግጓል፡፡ ሕገ-መንግሥቱንም ተከትለው የወጡ ፖሊሲዎችና ሕጎዎች አቀራረጽ ይዘትና መንፈስ ሲታይም የሕፃናትን መብትና ደህንነት የማስከበር ዓላማ ግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡
የሕፃናትን ጥቅምንና ደህንነት ቀደምትነት ከሚለው መርህ በተጨማሪ በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ ሠነዶችና ስምምነቶች ውስጥ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ሌላው መሠረታዊ መርህ የሕፃናት ተሣትፎ መርህ ነው፡፡ የዚህ መርህ ዓይነተኛ ይዘት በዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን በአንቀጽ 12 የተመለከተ ሲሆን የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተርም በአንቀጽ 4.2 ስር በግልጽ ሠፍሯል፡፡ አጠቃላይ የዚህ መብት አድማስ ሲታይም ሕፃናት ህይወታቸውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በውሣኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ተሣትፎ ማድረግ እንደሚችሉ፣ በተጨማሪም ጥቅማቸውን በሚመለከቱ ውሣኔዎች ላይ የራሣቸውን ተጽእኖ የማሣረፍ መብት ያላቸው መሆኑ፣ይህም ስፋት ባላቸው የፍርድ ጉዳዮች እንዲሁም መደበኛ የውሣኔ አሰጣጥ በሚመለከቱ በጤና፣ በትምህርትና በአከባቢ ጉዳዮች ሁሉ ሊካተት የሚገባ ስለመሆኑ ተጠቃሽ ድንጋጌዎች ያስገነዝባሉ፡፡ ድንጋጌዎቹ ሕፃናት በጉዲፍቻ ወቅት፣ በወላጆች መለያየትና ፍቺን ተከትሎ የትኛው ወላጅ ጋር ማደግ እንደአለባቸው ውሣኔ ሲሰጥ እና በመሣሠሉት ጉዳዮች ላይ አስተያየት መስጠትና ሊደመጡ እንደሚገባ እንዲሁም አስተያየታቸው ከመደመጡ ባሻገር ተገቢው አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የሕፃናቱ ሀሣብና አስተያየት ተገቢውን አፅንኦት የሚያገኘውም የሕፃኑን እድሜንና የአስተሣሠቡን የብስለት ደረጃ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሆኑንም የሚያጠያይቅ አይሆንም፡፡
እንግዲህ ሕፃንን የሚመለከት አንድ ጉዳይ ሲወሰን ሊታሰብባቸው የሚገባቸውን የተወሰኑ መሠረታዊ መርሆዎችን የሕግ ማቀፋቸውንና የድንጋጌዎችን ዝርዝር ይዘትና መንፈስ ምን እንደሆነ ከላይ ተመልክተናል፡፡ የተሻሻለው የፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ አካለ መጠን ያልደረሰን ልጅ የሚጠብቁትን ተቋሟትንና ቅደም ተከተሉን ከአንቀጽ 219-238 ድረስ ባሉት ድንጋጌዎች አስቀምጧል፡፡ በድንጋጌዎቹ መሠረት ወላጆች ከሌላው ሰው በቅድሚያ የአስተዳዳሪነትና የሞግዚትነት ሥልጣን ያላቸው መሆኑ፣ አሣዳሪ ወይም ሞግዚት በልጁ ወላጅ በኑዛዜ ቃል የሚመረጥ መሆኑ፣ ይህም በፍ/ቤት ሊሻር ወይም ሊሻሻል የሚችል መሆኑ፣ ወላጆች ወይም የወላጅ ኑዛዜ ከሌለ ሦስተኛው መንገድ ከዘመዶቹ መካከል በዝምድና ቅደም ተከተል የአሣዳሪነትና የሞግዚትነት ሥልጣን ሊሰጥ እንደሚገባ፣ በመጨረሻም በሕግ የሚመረጡ ዘመዶች ከሌሉ ይኸው ሥልጣን በፍ/ቤቱ በሚመረጥ ሰው ሊሰጥ የሚችል ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡ ሆኖም የእነዚህ ድንጋጌዎች ቅደም ተከተል ተግባራዊ ሲደረግ ሁልጊዜ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ቁልፉ ነጥብ በሕገ-መንግሥቱ የተመለከተው የሕፃኑ ደህንነት መብት ቀደምትነት ስለመሆኑ ሊረሣ የማይገባው ነው፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ የተመለከቱት ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎችም ሆነ በአንቀጽ 113/2/ ስር የተመለከተው ድንጋጌ አቀራረፅ፣ ይዘትና መንፈስ ሲታይ ፍ/ቤቶች አካለመጠን ያልደረሰን ልጅ አሣዳሪነትና ሞግዚትነት በተመለከተ ውሣኔ ሲሰጡ በሕጉ የተሰጣቸውን ሠፊ ሥልጣን መጠቀም ያለባቸው መሆኑንና የሕፃናትን መብትና ጥቅም የማስከበር ኃላፊነታቸውን መወጣት ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ያስረዳል፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 13/1/ ስር የተመለከተው ድንጋጌም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ የሕፃናትን ደህንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚችል ውሣኔ ይሰጥ ዘንድ ደግሞ የሕፃናቱ ሀሣብ ሊደመጥና ተገቢው ክብደት ሊሰጠው የሚገባ ነው ይህንኑ የሚቃረኑ ልማዳዊ አሠራሮችን ተቀባይነት የሌላቸው ስለመሆኑ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9/1/ ድንጋጌ በግልጽ ያሣያል፡፡ ቅጽ 8 የመ/ቁ. 35710

በሌሎች ሰዎች መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነት   መግቢያበኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕግ-መንግሥት ክፍል ሶስት ስር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተደነገጉ   ሲሆን...
05/06/2026

በሌሎች ሰዎች መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነት

መግቢያ
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕግ-መንግሥት ክፍል ሶስት ስር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተደነገጉ ሲሆን እንዚህ መብቶች ማንኛውም ሰው በእኩልነት የተጎናጸፏቸው ናቸው። በዚህም ማንኛውም ሰው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕግ-መንግሥትም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተደረጉ ስምምነቶች በተጎናጸፋቸው መብቶች የመጠቀም መብት ያለው ሲሆን በመብቱ የሚጠቀም ማንኛውም ሰው ደግሞ የሌላውን መብትና ነጻነት ባከበረ መንገድ መሆን አለበት። የአንድ ሰው መብት በማንኛወም አካል ከሕግ አግባብ ውጭ የተደፈረ እንደሆነ የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚስከትል በወንጀል ሕጉ እና በሌሎች ሕጎች ተመልክቶ ይገኛል። በዚህ ጽሑፍ በወንጀል ሕጉ የተደነገጉ በሌላ ሰው መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚያስከትሉትን ተጠያቂነት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

በሲቪል መብቶች በነጻ የመጠቀም መብትን መከልከል
በመርህ ደረጃ የሲቪል መብቶች ሰው በመሆን ብቻ የሚገኙ በመሆኑ ገደብ ሊጣልባቸው የማይቻል ከመሆኑም በላይ በነዚህ መብቶች ለመጠቀም ለማንም ምንም አይነት ክፍያም ሆነ ውለታ ማድረግ አይጠበቅም። በ1996 ዓ.ም በወጣው ወንጀል ሕግ አንቀጽ 601 ላይ እንደሰፈረው ማንም ሰው በዛቻ፣ በኃይል ድረጊት፣ በማታለል ወይም ሕግ ወጥ በሆነ በሌላ መንገድ፡-
• ሌላ ሰው በሕግ-መንግሥቱ ወይም በሌሎች ሕጎች ከተሰጡ የሲቪል መብቶች አንዱን በተለይም የወላጅነትን ወይም የሞግዚትነትን፣ የመክሰስን ወይም ፍርድ ቤት መብቱን እንዳይጠቀምበት የከለከለ ወይም
• ሌላው ሰው ከእነዚህ መብቶች በአንዱ በተወሰነ አኳኃን እንዲጠቀምበት ያስገደደ እንደሆነ
ድርጊቱ በሌላ ግልጽ ድንጋጌ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል በወንጀል ሕጉ ላይ ተደንግጎ ይገኛል። ሌላው ከሲቪል መብቶች በነጻ የመጠቀም መብት ክልከላ ጋር በተያያዘ የሚነሳው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 467 ላይ የመምረጥና የመመረጥ መብትን የመንካት ሲሆን ይህንን መብት የከለከለ ሰው ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጎ እናገኛለን።

የመዘዋወር ነጻነት መብትን መድፈር
የመዘዋወር ነጻነት መብት በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት ላይ ከተረጋገጡ መብቶች መካከል አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ሕግ-መንግሥት ተካተው ከሚገኙ መብቶች መካከልም አንዱ ነው። በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕግ-መንግሥት አንቀጽ 32 ላይ እንደተቀመተው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የሚገኛ የውጭ ዜጋ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት ነጻነት አለው። በመሆኑም ማንም ሰው በሕግ ሥልጣን ሳይኖረው ሌላው ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በነጻ እንዳይዘዋወር የከለከለ እንደሆነ በቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ እንደሚቀጣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 602(1) ስር ተመልከቷል።

በነጻነት የመዘዋወር መበትን የከለከለው ወይም የደፈረው የመንግሥት ሠራተኛ በሆነ ጊዜ ሥልጣን አላግባብ መገልገል በመሆኑ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1) መሠረት ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት እና ከሶስት ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት እና ከአስር ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ የሚቀጣ መሆኑ ተደንግጓል።

የሥራ ነጻነት መብትን መጣስ
በሌላ ሰው መብቶች ላይ ከሚፈጸሙ የወንጀል አይነቶች አንዱ የሥራ ነጻነት መብትን መጣስ ሲሆን ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በአገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኡኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራት እና ለመተዳደሪያ የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት እንዳለው በሕግ-መንግሥቱ አንቀጽ 41(1) ላይ በግልጽ ተደንግጓል። የሥራ ነጻነት መብት በሕገ-ገመንግሥቱ የተረጋገጠ በመሆኑ ማንም ሰው ሌላው ሰው በዚህ መብት እንዳይሠራብ ሊከለክለው አይችልም።
በዚህ መሠረትም ማንም ሰው በዛቻ፣ በኃይል ድረጊት፣ በማታለል ወይም በሌላ ሕግ-ወጥ መንገድ ሌላውን ሰው፡-
• አንድ የተወሰነ ሥራ ወይም የሥራ ሁኔታ እንዲቀበል ወይም አሰሪው የሥራ ሁኔታዎችን እንዲቀበል ወይም እንዲያሻሽል በማሰብ ሥራ አንቢ እንዲል ወይም እንዲያቆም ያስገደደ
• ከላይ የተመለከቱትን ለመፈጸም ዓላማው የሆነውን አንድ ቡድን ወይም ማኅበር እንዲቀላቀል ወይም የአንድ ቡድን አባል እንዲሆን ያስገደደ ወይም ከእንደዚህ አይነቱ ቡድን ወይም ማኅበር እንደፈለገው ወይም በፈለጋው ጊዜ እንዳይወጣ የከለከለ አንደሆነ የሥራ ነጻነት መብትን በመጣስ ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል።
ይህ የወንጀል ድርጊት በግል አቤቱታ የሚቀርብ ክስ ሲሆን ቅጣቱም ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ እንደሆነ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 603(1) ላይ ተመልክቷል።

የመጻጻፍ ወይም የግንኙነት ግላዊነት መብትን መድፈር
በኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕግ-መንግሥት በምዕራፍ ሶስት ስር ከተደነገጉ ሰብዓዊ መብቶች መካከል የመጻጻፍ ነጻነት እና የግላዊነት መብት ሲሆን ይህ መብት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጥበቃ ከተደረገላቸው መብቶች መካከልም አንዱ ነው። ይህ መብት በሕግ-መንግሥቱ ጥበቃ የተደረገለት በመሆኑ በዘፍቃድ ወይም ከሕግ አግባብ ውጭ ሊጣስ አይችልም፡፡ ጥሶ የተገኘ ማንም ሰው የወንጀል ተጠያቂነት እንዳለበት በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ ላይ ተመልከቷል።
በዚሁ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 606 ላይ እንደሰፈረው ማንም ሰው በሕግ ሳይፈቀድለት፡-
• የእርሱ ያለሆነውን የሥራ (የመስሪያ ቤት) የጉዳይ ማስፈጸሚያ ወይም የግል የሆነ ዝግ ወይም ግልጽ የደብዳቤ (የፖስታ) ወይም የመጻጻፍ፣ የቴለግራም፣ የስልክ፣ የኤሎክትሮኒክ ወይም የቴሌኮሚኒኬሽን ወይም የማናቸውም ሌላ ዘዴ የሚደረግ ግንኙነትን፤ የንግድ ወይም የግል የሆነ የተዘጋ ደብዳቤን ወይም አንድን ጥቅል፤ የታሸገን ጥቅል ዕቃን ወይም ማናቸውንም የተላከ ነገር አስቦ የከፈተ ወይም ውስጡ ያለውን ነገር ያወቀ እንደሆነ ወይም
• ለዕርሱ ያልተላከውን እንደዚህ አይነቱን ደብዳቤ ወይም የታሸገ ጥቅል በስሕተት ወይም በቸልተኝነት በመክፍት አንዳንድ ነገሮችን ከአወቀ በኋላ ለሌላ ሰው ያሳወቀ ወይም ጥቅም ያገኘበት እንደሆነ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከአንድ ሺ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ከሶስት ወር በማይበልጥ ቀላል እሥራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል።
በሌላ በኩል ማንም ሰው አስቦና ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ አንድን ደብዳቤ ወይም የሚላክ ዕቃ ወደ ተላከበት አድራሻ እንዳይደርስ ያቋረጠ ወይም ያስቀረ፣ ወደ ሌላ አድራሻ እንዲደርስ ያደረገ ወይም ያወደመ እንደሆነ የወንወጀል ተጠያቂነት ያለበት በመሆኑ ድርጊቱ የበለጠ ቅጣት በሚያስከትል ሌላ የሕግ ድንጋጌ የሚያስጠይቅ ካልሆነ በቀር በወንጀል ክስ አቅራቢነት ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እሥራት እንደሚቀጣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 606(2) ስር ተደንግጎ ይገኛል። በዚሁ የወንጀል ሕግ እንደተመለከተው በመንግሥት ሠራተኞች ስለሚፈጸሙ የሥራ ሚስጥርን ስለመግለጽ፣ በአደራ በተሰጠ ዕቃ ያለአግባብ ስለማዘዝ እና በሥራ ተግባር ስለሚፈጸም የመውሰድና የመሰወር ወንጀሎች በተመለከተ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 መሠረት በሙስና ወንጀል ተጠያቂ ይሆናሉ።

ማጠቃለያ
በአጠቃላይ በፌደራሉ ሕገ-መንግሥት የተረጋገጡና ጥበቃ የተደረገላቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሕግ አግባብ ካልሆነ በስተቀር ሰዎች በመብቶቹ እንዳይጠቀሙ ለማገድም ሆነ ለመከልከል የማይቻል ሲሆን ሰዎች እነዚህን መብቶች እንዳይጠቀሙ አድርጎ መገኘት የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ሊታወቅ ይገባል፡፡

Address

Werabie

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት/Werabie Town Adminstration Justice Office posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to ስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት/Werabie Town Adminstration Justice Office:

Shortcuts

Share