Major Mamo Loma

Major Mamo Loma Military & Security matters

10/29/2024
10/26/2024

ኢትዮጵያ እና የጦር ኃይሏ
ከቶ እንደ ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ስም ሲሾፍበትና ሲቀለድበት የኖረ ሃገርና ሕዝብ በዓለም ላይ ይገኝ ይሆን?
እነሆ ኢትዮጵያ ከለየለት ዘውዳዊ አገዛዝ ከተላቀቀች 50 ዓመታትን አስቆጠረች፡፡ በዚህ የግማሽ ምዕተ ዓመታት ዕድሜ የሃገሪቱን የመንግሥትነት በትረ ሥልጣንን የጨበጡ አገዛዞች ሁሉ በሃገሪቱ ላይ አንዲት ጠብታ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ቀዳዳ ሰጥተው አያውቁም፡፡ ከዚህ ይልቅ የተቀያየሩት አገዛዞቹ ሁሉ ፍትሕን እና የሰው ልጅን ነፃነት እረግጠው በጭካኔና አንባ ገነናዊ አገዛዛቸው ተተኪው ካለፈው እየከፋ ከመሄድ ውጪ አንዱ ከሌላው ተምሮ ለሃገርና ለሕዝብ የተሻለ ሆኖ አያውቅም፡፡ ይባስ ተብሎም በወያኔ/ኢህአዲግ ዘመን ዓለም አንቅሮ የተፋውና የጣለው የብሔር ፖለቲካን በማራመድ በሃገርና በሕዝብ ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰት፤ መከራና ሰቆቃ አንድም መሻሻል ሳያሳይ ኖሮ ጊዜውን ሁሉ በበደል ፈጽሞ አልፏል፡፡
በዚህ ሁኔታ ሁሉም አገዛዞች ፀረ ዲሞክራሲ ሆነው እያሉ በአስገራሚ ሁኔታ ሁሉም አገዛዞች በሃገርና በሕዝብ ላይ ሲያሾፉና ሲያላግጡ የኖሩትና የሚኖሩት መጠሪያቸውን ዲሞክራሲዊ መንግሥት በማለት ነበር፡፡
በዚህ መሠረት ደርግ ለድፍን አስራ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን በአረመኔያዊ አንባ ገነን አገዛዝ ለዘለቀበት አገዛዙ መጠሪያው አድርጎት የነበረው ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሚለውን ነበር፡፡ ቀጥሎ ደርግ ተገርስሶ የኤትኒክ አፓርታይድ አራማጅ የሆነው ዘረኛው የወያኔ/ኢህዲግ አገዛዝ ሲተካ በመጀመሪያ ምንም ዓይነት ጠብ የምትል ዲሞክራሲ ጠብታ በሌለበትና በማይታወቅበት እራሱን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር በማለት ሲጠራ ቆይቶ በመቀጠል ሥልጣኑን ሲያደላድል “መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ“ እንዲሉ የአገዛዙ መጠሪያ ያደረገው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት በማለት ነበር፡፡ አ-ይ-ገ-ር-ም-ም?
ከ7 ዓመት በፊት ደግሞ ከወያኔ/ኢህአዲግ ውስጥ ወጥቶ ኢትዮጵያን ከኋላ ቀር የዘር ፖለቲካ አላቅቄ ፍትሕ፤ ነፃነትን እና እኩልነትን አስፍናለሁ በሚለው የቃል ስብከቱ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ድጋፍ የተቸረው የብልጽግና አገዛዝ፤ የአሁኑ ይባስ በሚያሰኝ ሁኔታ ዘርን እና የዘር ጥላቻና መጠፋፋትን ይበልጥ በማክረርና በማጦዝ ሃገሪቱን ዲሞክራሲ ሳይሆን ከአውቶክራሲም የከፋ አደጋና ምስቅልቅል ውስጥ እያስገባ ሌላ የሚያውቀውና የሚፈጥረው ባለመኖሩ ሊሆን ይችላል ያንኑ ወያኔ/ኢህአዲግ ሲያላግጥበት የኖረውን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት የሚለውን መጠሪያ በመያዝ የ50 ዓመቱን በሕዝብና በሃገር ላይ የሚካሄደውን በዲሞክራሲ ስም የማሾፍና የማላገጥ ተግባር በከፋ ሁኔታ አስቀጥሎት ይገኛል፡፡
ዲሞክራሲ የሚለው ቃል ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ባዕድ ቃል ስለሆነ ይመስላል አንዳንዴ ቁንጽል ትርጉም እየተሰጠው ወይም ፈረንጅ የፈጠረውና ለፈረንጅ ብቻ የሚሰራ በሚመስላቸው ሰዎች ሲተችና አንዳንዴም መረዳት በተሳናቸው ሰዎች ለኢትዮጵያ አይሆንም ሲባል ይሰማል፡፡
ለምን ዲሞክራሲ የሚለውን ቃሉን ትተን ትርጉሙን ወስደን ለሃገራችን በሚመጥንና በሚስማም ሁኔታ አንረዳውም፡፡ ለምሳሌ ዲሞክራሲ ማለት፡
1) ሕዝብ የሃገሩ የሥልጣን ባለቤት መሆን፤ (Power of the people) የሚለውን
2) የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርጎ የሚመራና የሚያስተዳድር መንግሥታዊ ሥርዓት (a way of governing which depends on the will of the people) የሚለውን
3) ፍትሕ፤ ነፃነት፤ እኩልነት፤ የሕግ የበላይነት፤ ተጠያቂነት የሰፈነበት መንግሥታዊ ሥርዓት የሚለውን ትርጉሙን በስራ ላይ አናውለውም?
ከቶ የሰው ልጅ ከላይ የተዘረዘሩትን በሃገሩ ላይ ማስፈን ከቻለ ከዚህ ሌላ ምን ሊፈልግ ይችላል?
ከቶ ለሰው ልጅ ፍትሕ፤ ነፃነት፤ እኩልነት፤ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የማይመለስለት ምን ዓይነት ጥያቄ ሊኖር ይችላል እና ነው ዛሬ በሃገራችን ኢትዮጵያ ይኸ ሁሉ የዘርና የሃይማኖት ዘባተሎ እየተመዘዘ እርስ በእርስ የጥላቻ መርዝ መርጨትና የመርዝን ሰብል ማጨድ የተስፋፋው? ከቶ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም ሁሉ ትቶት በሄደውና ወርውሮ በጣለው ከዘመኑ ጋር ጨርሶ በማይሄድ እጅግ ኋላ ቀር በሕግ መታገድና መገደብ የሚገባው መጠፋፊያ የዘር ፖለቲካን መንግሥታዊ ሥርዓት ሆኖ ሃገርና ሕዝብ እንዲመራበትና እንዲተዳደርበት ማድረግ ምን ይሉታል?
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህንን ርዕስ መርጬ ለማቅረብ ገፊ ምክንያት የሆነኝ በአንድ ሃገር ላይ ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈንና አለመስፈን ጋር ስለተያያዘውና ሃገራችን ኢትዮጵያ አልዋጣላት ብሏት ስለኖረው ሕዝባዊ ወይም ዲሞክራሲያዊ የጦር ኃይልን በተመለከተ ምልከታዬን ለማቅረብ ነው፡፡
ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ሃገራችን ኢትዮጵያ በእምነትም ሆነ በመንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ ዘመናትን ያስቆጠረች ታላቅና ድንቅ ሃገር የመሆኗን ያህል ካላት ጂኦ ፖለቲካ አስፈላጊነት በተጓዳኝ ዙሪያዋን በጎዋን በማይመኙላት ሃገሮች የተከበበች በመሆኗ ነፃነቷን እና ሉዓላዊነቷን ጠብቃና አስከበራ ለመኖር ሁል ጊዜም እና ምን ጊዜም ጠንካራና ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮፌሽናል የጦር ኃይል ያስፈልጋታል፡፡
ይህ ዓይነቱ ዘለቄታነት ያለውና ትውልድ ተሻጋሪ ፕሪፌሽናል የጦር ኃይል ሊኖር የሚችለው ደግሞ የጦር ኃይሉ ሕዝባዊና ዲሞክራቲክ መሆን የቻለ እንደሆነ ብቻ በመሆኑ ሃገሪቱ ያለፈችበት ታሪክ በራሱ አስረጂና መስካሪ ነው፡፡ የሕዝቧም የዘወትር ምኞትና ፀሎት የሚመጣው አገዛዝ ሁሉ በሃገርና በሕዝብ ንዋይ የቆመና የሚኖርን የጦር ኃይልና የፀጥታ ኃይል ተጠቅሞ ፍትሕን መጨፍለቂያና ሕዝብን ረግጦና አስፈራርቶ መግዣ መሣሪያ አድርጎ የመቀጠሉ አዙሪት እንዲቆምና እንዲያበቃ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ሕዝባዊ ወይም ዲሞክራቲክ የጦር ኃይል ሊኖር እንዲችል በመጀመሪያ ሃገር በዲሞክራቲክ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ሥርዓት መመራትና መተዳደር አለባት፡፡ ዲሞክራቲክ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ሥርዓት ማለት ደግሞ በሕዝብ ሥልጣን የበላይነትና የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማለት ነው፡፡
ይህንን በመሰለ ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ መንግሥታዊ ሥርዓት ስር ያልተገነባ የጦር ኃይል አሸዋ ላይ እንደቆመ ቤት ሲወድቅና ሲፈርስ፤ እንደገና በዛው አሸዋ ላይ ሲገነባ የሚኖር ስለሆነ ኢትዮጵያም ላለፉት 50 ዓመታት ገጥሟት የኖረው ይኸው መሆኑን ሕዝቡም ሆነ በይበልጥ ደግሞ አሁን ያለው የጦር ኃይል በሚገባ ሊያውቀውና ሊረዳው ይገባል፡፡
የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረገ መንግሥታዊ ሥርዓት ስለመኖር፡፡
1) መጀመሪያ ሕዝብ የሃገሩ ሥልጣን ባለቤት መሆኑ መረጋገጥ አለበት
2) ሕዝብ የሃገሩ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን የሕዝብ ውክልና የሚረጋገጥበት ማስመሰያውና ማታለያው ሳይሆን እውነተኛውና ሕዝብን በትክክል ወክለው የሚገኙበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መኖር ወይም parliamentary democracy በስራ ላይ መዋል ይኖርበታል፡፡
3) የጦር ኃይሉ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የሕዝብ ተመራጭ ሲቪል የጦር ኃይል ጠቅላይ አዛዥና የመከላከያ ሚኒስቴር (Defence Secretary) የበላይነት መመራት ይኖርበታል፤
4) የጦር ኃይል በሕዝብ ተወካይ ሲቪል የበላይ መሪነትና ቁጥጥር ስር ሲሆን ከፓርላማው እና ከሕዝቡ ጋር የሚያቆራኘው ሲስተም ተዘርግቶ የጦር ኃይሉ በመንግሥት ወይም በወታደራዊ አዛዦች ብቻ የሚታዘዝ ሳይሆን ሕዝባዊ ወይም ዲሞክራቲክ ኮንትሮል(Democratic Control) ያለው ይሆናል፡፡
5) ይህ ባለበት ሁኔታ የጦር ኃይል ሲገነባም ሆነ ሲዘምት ከጦርነቱ ሕጋዊነት አንስቶ ስለ ዝግጁነት፤ ብቃት፤ ስለ ጦርነቱ አዋጪነት፤ ሁሉ አይቶ ፓርላማው ሲፈቅድና ይሁንታ ሲሰጥ ብቻ ይሆናል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም በመንግሥትም ሆነ በጦር አዛዦች ስህተትም ይሁን ድክመት በጦር ኃይሉ ላይ ያልተገባ ተግባር ቢፈፀምም ሆነ አንዳች ጉዳትና በደል ቢደርስ ፓርላማው ለጦር ኃይሉ ቆሞ ይከራከራል ወይም መንግሥትን እና ወታደራዊ አዛዦችን በሕግ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡
ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ የመንግሥት ሥርዓት ባለበት ሃገር የጦር ኃይል ባለቤት፤ አሳቢ ተቆርቋሪና ተከራካሪ ወገን ያለው ሲሆን እሱም መንግሥት ሳይሆን የሃገሪቱ ሕዝብ ነው፡፡ ምክንያቱም ቋሚና የማይለወጥ ዘለዓለማዊ ሃገርና ሕዝብ እንጂ መንግሥት አይደለምና፡፡
ይህ ዓይነቱ ፍትሕ፤ ነፃነት፤ እኩልነትና የሕግ የበላይነት በሰፈነበት ሃገር ለምሳሌ public inquiry (የሕዝብ ጥያቄ) የሚባል ግዙፍ፤ የሚፈራ፤ የሚከበርና የሚታመን የምርመራ ዘዴ አለ፡፡ ይህ inquiry ብዙ ዘርፎችን የሚያካትት ሲሆን ለምሳሌ በጦር ኃይሉ ተቋምም ሆነ በተያያዘ አንዳች ነገር ቢደርስና ሕዝብን የሚያጠያይቅና የሚያሳስብ ሆኖ ቢገኝ የሕዝብ ተወካዮች፤ የሕግ ባለሙያዎችና የዲሞክራሲ ተቋማት መንግሥት public inquiry እንዲከፍት ያስደርጋሉ፡፡ ጉዳዩ ነፃና ገለልተኛ በሆኑና በታወቁ የሕግ ባለሙያዎች ሁሉንም ነገር የመመርመርና የመፈተሽ ሥልጣን ተሰጥቶት ያጣራና ውጤቱን ለሕዝብና ለመንግሥት ይፋ ያደርጋል፡፡
ለምሳሌ ከ4 ዓመት በፊት የሃገር ዳር ድንበር ለማስከበር በግንባር ላይ ተሰልፎ በሚገኝ የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ሰሜን ዕዝ ላይ በማን ጥፋትና ስህተት፤ እንዴት እና በምን ሁኔታ፤ ጥቃቱ እንደደረሰ? ምን ያህል ወታደር፤ ሲቪል፤ ሴት፤ ወንድ፤ ህፃን እና አዛውንት እንደሞተ፤ እንደቆሰለና አካለ ጎደሎ እንደሆነ? ይህንን ጥፋትና ውድመት ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ በመንግሥት በኩል መደረግ ሲገባው ስላልተደረጉ ጉዳይ፤ ወ.ዘ.ተ ስለሚለው የሚታወቅ ነገር ስለሌለ የሕዝብ ጥያቄ በመሆኑ public inquiry ተከፍቶ መጣራት ነበረበት፡፡ ይህ ሳይሆን ዝም ብሎ ተዳፍኖ የታለፈውና ቀጥሎም ቀጥሎም ዝም ብሎ መተላለቁ የቀጠለበት በኢትዮጵያ ውስጥ የጦር ኃይልን ከሕዝብ ባለቤትነት አላቀው በሥልጣን ላይ ያሉ የአገዛዝ ባለሥልጣናትና ከነሱ ጋር በተቆራኙ የሠራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች እንደ ኪስ ገንዘብ የሚያዙበት በመሆኑ ነው፡፡ አ-ያ-ስ--ቆ-ጭ-ም?
በዚህ መሠረት ሕዝብ የሃገሩ የሥልጣን ባለቤት ባልሆነበትና የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርጎ እንዲመራ ሕዝባዊ ወይም ዲሞከራሲያዊ ቁጥጥርና ተጠያቂነት ባልተበጀለት መንግሥታዊ ሥርዓት ስር የሚገኝ የጦር ኃይል ሕዝባዊ ወይም Democratic Control ስለማይኖረው በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ታዛዥና ጉዳይ አስፈጻሚ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
ይህም ስለሆነ በቀደመው ጊዜም ሆነ አሁን ለአገዛዞች ሠራዊቱን እንደ ኪስ ገንዘባቸው በመቁጠር ያለምንም ተጠያቂነት ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ለሥልጣናቸው መጠበቅ ሲሉ ብቻ የጦር ኃይሉን ወዳሻቸው ቀጠና በማዝመት ሠራዊቱ እየሞተና አካለ ጎዶሎ እየሆነ ምን ያህሉ እንደሞተ፤ እንደ ቆሰለና አካለ ጎዶሎ እንደሆነ ቁጥሩን እንኳ ለማወቅ የሚያስገድድ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ የዛሬ 50 ዓመትም አሁን የለም፡፡ ይህም ስለሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ክቡሩ የሰው ልጅ ህይወት ከዝንብ እኩል እንኳ እንዳይቆጠር ሆኗል፡፡
የዚግ ዓይነቱ አገዛዝ መጨረሻው በሕዝብ ኃይል መገርሰስ ሲሆን ያ ቀን ሲመጣ አገዛዙ በዘመኑ በሃገርና በሕዝብ ላይ ለፈፀመው ተነግሮ የማያልቅ ግፍና በደል ሁሉ ዋጋ ከፋዩ የጦር ኃይሉ ይሆናል፡፡ ይህንን ለመረዳት የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ላለፉት 50 ዓመታት ያለፉበትን እውነተኛ ታሪክ ማየት በቂ ነው፡፡
ይህ ሁሉ እየታየና ይህ ሁሉ እየታወቀ ዛሬ ያለው የአገዛዝ ሥርዓትም ሆነ ጦር ኃይሉ እየተከተሉትና እየሄዱበት የሚገኙት መንገድ መጨረሻው ቁልጭ ብሎ የማይታየው ካለ የአዕምሮውን ጤነኛነቱን ሊፈትሽ ይገባዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የጦር አዛዦች በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትን ነው የምንከላከለው እያሉ ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ይህ ግን በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ካለማወቅ እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ የተመረጠ ዲሞክራቲክ መንግሥት በታሪክ ኖሮ አያውቅም፤ የለም፡፡
በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ማለት ፍትሕ፤ ነፃነት፤ እኩልነትና የሕግ የበላይነት በሰፈነበት ሃገር መራጭም ተመራጭም በሕግ ፊት እኩል የሚታይ ሆኖ የሕዝብ ውክልናን ማግኘት ብቻ ሳይሆን በወከለው ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ቁጥጥር ስር ሆኖ የሚሰራበት የዲሞክራቲክ ተቋማት (democratic institutions) ኖረው የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርጎ ብቻ የሚሰራ መንግሥታዊ ሥርዓት ሲኖር ብቻ ነው፡፡
በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እና የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርጎ የሚሠራ መንግሥት በኢትዮጵያ ቢኖር እኮ የኦሮሞም ሆነ የአማራ ክልል ሕዝብ መንግሥት ሆይ የጦር ኃይል በክልሌ አዝምትና እኔንም ልጆቼንም እየገደለ እኔም መከላከያ የሆነውን ወገኔን እየገደልኩና እየተገዳደልን እንኑር ብሎ የሚፈቅድና የሚስማማ ይመስልሃል?
በንጉሡ ዘመን የእንደራሲዎች ምክር ቤት የሚባል ፓርላማ ነበር፤ በደርግ ጊዜ ደግሞ የሸንጎ ምክር ቤት ይባል የነበረ ሲሆን ላለፉት 35 ዓመታትና አሁንም ድረስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚባል አለ፡፡ እውነታው ከታየ ግን ሁሉም የአገዛዞቹ ጉዳይ ማስፈፀሚያና ዲሞክራሲ አለ በማለት የዲሞክራሲ ማላገጫዎች እንጂ የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርጎ የሚመራና የሚያስተዳድር መንግሥታዊ ሥርዓትን (a way of governing which depends on the will of the people) የሚለውን የዲሞክራቲክ መርህ የሚያራምዱ አይደሉም፡፡ በንፅፅር ከታየ እንደውም በንጉሡ አገዛዝ ዘመን የእንደራሴዎች ምክር ቤት እንደራሴዎቹ የተወከሉበትን ሕብረተ ሰብና አካባቢ ጥቅምና ፍላጎት ለማስከበር ሲሉ ብዙ ክርክር የሚካሄድበት ስለነበር የተሻለ የሚባል ነው፡፡
ይህንን ሁሉ ካልኩ በኋላ በመጨረሻ ዛሬ በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ለተነሳው የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊና የመሳሰሉት የሕዝብ ጥያቄዎችም ሆኑ ችግሮች አገዛዙ ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ የፀጥታ ኃይል ልኮ ግለሰቦችን እና ተቋማትን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሕገ ወጥ መንገድ ያሳፍናል፤ ያስራል፤ ይገርፋል፤ ያሰቃያል፡፡
ይህ ፍትሕ አልባነት አስመርሮትና ስጋት አድሮብት ትጥቅ ያነሳውን ደግሞ ሃገር በእውነተኛ የሃገር፤ የሕዝብና የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር በጥበብ፤ በትዕሥትና አርቆ አስተዋይነት መምራት እንዳለባት ጨርሶ የማያውቀውና የማይገባው አገዛዝ በፖለቲካዊ መፍትሔ ሰጪነት ሊፈታ የሚችለውን በጦር ኃይል ብቻ እጨፈልቃለሁ በሚል እብሪት ጥናትና ምርምር፤ ወይም ተገቢው ሁኔታ ማረጋገጥ ባልተሰራበት በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ የጦር ኃይሉን በገዛ ሕዝቡ ላይ ያዘምታል፡፡
በሚዋጋበትና ህይወቱን አሳልፎ በሚሰጥበት ዓላማና በወታደራዊ ሞራል ያልደረጀን፤ በስንቅና ትጥቅ፤ በሥልጠናና ልምምድ እንዲሁም በአመራርና በዲስፕሊን መታነጽ ለውጊያ ቀርቶ ለውትድርና ያልበቃን ሠራዊት በሕዝብ ላይ በማዝመት የሠራዊትና የሕዝብ እልቂትን በማምጣት ሠራዊቱን ከሕዝብ ጋር ደም እያቃባ ለውርደትና ለክስረት ይዳርጋል፡፡ የኢትዮጵያ ወላጆች በተለይ ደግሞ የደሃ ልጆች በዚህ አላስፈላጊ በሆነ አገዛዝ ወለድ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብተው እንደ ቅጠል እየረገፉ ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ እየቀረ ይገኛል፡፡
አሁንም የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርጎ የሚመራና የሚያስተዳድር ዲሞክራቲክ መንግሥታዊ ሥርዓት እስካልተመሠረተ ድረስ ይህ መተላለቅ ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻም ኢትዮጵያ የእምነትና የአማኞች ሃገር በመሆኗ በእግዚአብሔር ተራዳዒነት ከጥፉት መትረፏና መቀጠሏ ባይቀርም የጦር ኃይሉ የመጨረሻ እጣ ፋንታ ግን ከቀደመው ዘመንም ለከፋ ውድቀት እንደሚዳረግ የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡ ይህም ስለሆነ“ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል” ነውና ከዚህ ጥፋት ለመዳን የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ያለህ አማራጭ ጊዜ ሳይቀድምህ ከሕዝብህ ጎን መቆምና ለሃገርህም ሆነ ለራስህ ህልውና የሚበጅ ስራ መስራት ይጠበቅብሃል፡፡
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!!
ሻለቃ ማሞ ለማ

08/07/2024

ፍትሕ በሌለበት ሰላም ሊኖር አይችልም!
(Without justice, there can be no peace)
የእርስ በእርስ ጦርነትና የመጠፋፋት ሃገር ኢትዮጵያ
የወጣትነት ዘመኔን ባገባደደው የውትድርና አገልግሎቴ ኢትዮጵያ ውስጥ ለ30 ዓመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ወደ 20 ዓመት የሚጠጋውን ጊዜ በውስጡ ያለፍኩ በመሆኔ ዛሬ ላይ ሆኜ በየጦር ቀጠናው በሰው ልጅ ላይ ላይ ሲደርስ የነበረው አሰቃቂና ዘግናኝ የጦር ሜዳ እልቂትና ውድመት፤ እንዲሁም ይደርስብን የነበረውን ስቃይና መከራ፤ ወደ ኋላ ሄጄ በዓይነ ሂሊናዬ ስቃኘው ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ ቁጭትና ጥልቅ የሆነ የሃዘን ስሜት ያሳድርብኛል፡፡
ጦርነቱ ይካሄድ የነበረው በአንዲት ሉዓላዊ ሃገር ኢትዮጵያ ስር ካሉ 14 ክፍለ ሃገራት ውስጥ በኤርትራ እና ቀጥሎም ከ14 ዓመት በኋላ እንዲሁ በትግራይ ከኢትዮጵያ ተገንጥለን የራሳችንን ነፃ ሀገር እንመሠርታለን በሚል መሣሪያ አንስተው በሚዋጉ እና የሃገሪቱን ሉዓላዊነት እና አንድነት በሚያስከብር የሃገሪቱ የፀጥታ ኃይል መካከል ነበር፡፡
ከነጻ አውጪዎቹ በተጓዳኝ ሌሎች የፖለቲካም ሆነ የፍትሕና የመብት ጥያቄ በማንሳት ነፍጥ አንስተው የሚዋጉትን ጨምሮ በድምሩ 30 ዓመታትን ያስቆጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ሲካሄድ በመካከሉ ደግሞ ከውጪ ወራሪ ኃይል ጋር የተደረገው መጠነ ሰፊና ከፍተኛ ጦርነት ጋር ተዳምሮ በሃገራችን በሰው ልጅ ላይ የደረሰውን እልቂት፤ የአካል መጉደልና የሃብትና የንብረት መውደም ሁሉ ሲታሰብ ሃገሪቷም ሆነች ሕዝቧ እስከ አሁን ህልው ሆነው መቀጠላቸው በእጅጉ ያስገርማል፡፡
ከቶ ይህ ሁሉ ለምን እና እንዴት ሆነ? በማለት ወደ ኋላ ሄደን ስንጠይቅ በሚገባ ልንረዳውና ልንገነዘበው የምንችለው ነገር ቢኖር ሃገራችን ላለፉት ዘመናት ብቻም ሳይሆን አሁንም ድረስ እርስ በእርስ በመጠፋፋትና በመገዳደል ከዛም ጋር ተያይዞ በሚመጣ ረሃብ፤ በሽታ፤ ድህነትና ኋላ ቀርነት ተጋላጭ ሆና ለመኖሯ ዋንኛው ምክንያት ለዚች ጥንታዊትና ታሪካዊት፤ የታላቅ ሕዝብ መገኛ ለሆነች ሃገር የሚመጥናት እና የሚበጃት ዘመኑን የዋጀ መንግሥታዊ ሥርዓት ኖሯት ባለማወቁ ፍትሕ፤ ነፃነት፤ ዲሞክራሲ፤ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት የሚባል ነገር ሰፍኖባት የማያውቅ በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ መሠረት ፍትሕ በሌለበት ሰላም ሊኖር አይችልም! (Without justice, there can be no peace) እንደተባለው የሃገራችንን ሰላም ለማረጋገጥ የፍትሕ፤ ነፃነትና ዲሞክራሲ መስፈን ዋናው መሠረት ስለሆነ ሃገራቸውን እና ሕዝባቸውን የሚወዱ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ይህ መሠረታዊ ጥያቄ እስካልተመለሰ ድረስ ከእርስ በእርስ ጦርነት፤ ከመከራ፤ ከሰቆቃ፤ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት መላቀቅ እንደማንችል ተረድተው ፍትሕ፤ ነፃነትና ዲሞክራሲን ለማስፈን በአንድነት ቆመው መታገል ብቸኛው አማራጫቸው አድርገው መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
በሃገራችን ኢትዮጵያ ከንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ ቀጥሎ የተቀያየሩት አገዛዞች ሁሉ አንዱ ከሌላው ይሻል ይሆናል የአሁኑ ካለፈው ስህተት ይማር ይሆናል ተብሎ ሲታሰብ ሁሌም ከነበረው በከፋ ሁኔታ የሥልጣን ጥመኝነት፤ አንባ ገነንነት፤ እብሪትና ጭካኔ መባባስ ካልሆነ የተሻለ የሚባል መንግሥታዊ ሥርዓት ሊፈጠር አልቻለም፡፡
ከዚህ ሁሉ የከፋው ሁኔታ ደግሞ ላለፉት 33 ዓመታት የተያዘው ከሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር መጠፋፊያ ካልሆነ በስተቀር አንዳችም ጥቅም የሌለውን ኋላ ቀር ዘር፤ ጎሳ፤ ብሔርና ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አካሄድ ነው፡፡
በዚህ የዘር ፖለቲካ ውስጥ እጅግ አስገራሚው ነገር ተማሩ፤ በዕድሜ ጎለመሱ የሚባሉት ፖለቲከኞች ሳይቀሩ ብሔርንም ሆነ ማህበረ ሰብን ከገዢ መደብ ባለመለየት አንዱን ብሔር የሌላው ታሪካዊ ጠላት ወይም የሌላው ገዢና ጨቋኝ፤ ሆኖ የኖረ በማስመስል ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ማጋጨትና ማናከስን፤ አንዱ የሌላው ስጋት አድርጎ በማቅረብ ሕዝብ እርስ በእርሱ በስጋትና በጥላቻ እንዲኖር ማድረግን የሃገር ፖለቲካ መዘውር አድርገው በልማት ፋንታ ጥፋትን በሰላም ፋንታ የእርስ በእርስ ጦርነትን ጠማቂዎች ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ትግራይ እና አማራ ክልል፤ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል አፋርና እና ደቡብ ክልል፤ ወ.ዘ.ተ ባሉ የትኛውም የኢትዮጵያ ምድር ላይ ቢኬድ ከ80% በላይ የሚሆነው በእርሻ እና በአርብቶ አደርነት የሚተዳደር ሕዝብ ነው፡፡
ይህ የሃገሪቱን አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘው የሕብረተ ሰብ ክፍል ደግሞ በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት፤ የህክምና እና የሆስፒታል አገልግሎት በበቂ ደረጃ የሌለው፤ ንጹህ ውሃና የመሳሰለው ያልተሟላለት፤ ከሁለት ሺህ ዓመት በላይ ባስቆጠረ እጅግ ኋላ ቀር በሆነ የአስተራረስና የአመራረት ዘዴን የሚጠቀምና ከዚህ ተላቆ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚወስደው መንግሥታዊ አስተዳደር አጥቶ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው፡፡
ይህም በመሆኑ አብዛኛውና ለም በተባለ አካባቢ የሚኖረው የኢትዮጵያ አርሶ አደር ሕዝብ ሳይቀር የሚያመርተው ምርት ከዓመት ዓመት አላደርስህ እያለው በክረምት ጎመን እና ቅጠል እየበላ ጭምር የሚያሳልፍና በድህነትና በጉስቁልና የሚኖር ነው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም በዓለም ላይ ባለው የአየር ንብረት መለዋወጥ ምክንያት በየ10 ዓመቱና አንዳንዴም ባልተጠበቀ ሁኔታ በዝናብ መታጣት እና በድርቅ በመመታት ይህችኑ ከእጅ ወደ አፍ የሆነችውን ኑሮውን በማጣት ለከፋ ሁኔታ የሚዳረገው ይኸው አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር የያዘው የአርሶ አደሩ ክፍል ነው፡፡
እንግዲህ ይህንን ዓይነቱን አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው የዘመኑ ፖለቲከኞችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ አንዱ የሌላው ጠላት፤ አንዱ የሌላው ጨቋኝ ወይም ገዢ መደብ አድርገው በማቅረብ ሕዝብ ኋላ ቀርነቱ፤ ድህነቱና ጉስቁልናው ሳይበቃው በማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በመግባት የመከራና የሰቆቃ ኑሮን እንዲገፋ የሚያደርጉት፡፡
ይህንን ስንመለከት ዛሬም ያለው አገዛዝ ሆነ ነገም የሚመጣው በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ፤ ነጻነትና ዲሞክራሲን እስካላሰፈነ ድረስ በምድሪቷ ላይ አንዳችም ሰላም እንደማይኖር መረዳት አለበት፡፡
ይህም ስለሆነ ለሃገሩና ለሕዝቡ የሚቆረቆር የትኛውም ኢትዮጵያዊ ዓላማና ግቡ አድርጎ መያዝ ያለበት የሁሉም ቁልፍ የሆነው በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሕ ነፃነት፤ ዲሞክራሲና ከዚህም ጋር የሕግ የበላይነትን እና ተጠያቂነትን ማስፈን በሚለው ላይ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሻለቃ ማሞ ለማ

08/07/2024

ፍትሕ በሌለበት ሰላም ሊኖር አይችልም!
(Without justice, there can be no peace)

https://www.youtube.com/live/trLYgB70plo?si=JyysAr9ppHVRNTxC
07/23/2024

https://www.youtube.com/live/trLYgB70plo?si=JyysAr9ppHVRNTxC

ፋኖ የጦር ጄነራሎቹን መሪ አድርጎ መምረጥ ለምን አልፈለገም? የወታደራዊ ሳይንስ ጠበብት ሻላቃ ማሞ ለማን ጋዜጠኛ ዘውዱ መንግስቴ አነጋግሯቸዋል ቀጥታ በዘውዱ ሾው Zewdu Show 20/07/24

https://www.youtube.com/
03/16/2024

https://www.youtube.com/

Military Matters Ethiopia & World is a channel dedicated to bringing you inside information about Military science, weaponry, as well as the latest military ...

03/16/2024

ይህ ቪዲዮ የተዘጋጀው ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ተተኩሰው በመክሽፉና፤ በየቦታው በመጣል የሚቀሩ የፈንጂ ቅሪቶች ሰው ሳያውቅ ነክቷቸው ጉዳት እንዳያርሱበት ለማስተማር ነው ሁሉም እያየ ሼር ያድርገው፡፡

03/15/2024

በዚህ Facebook ላይ ጓደኛ የሆናችሁኝ እና የGroup አባላት በሙሉ፡፡ በኔ በኩል ውትድርናን በተመለከተ የማቀርበውን ጽሑፍና ቪድዮ በማንበብና በማየት ትሳተፉ ዘንድ የአክብሮት ግብዣዬን አቀርባለሁ፡፡

Address

London
Central London, ON
LONDONW1

Telephone

+447904777999

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Major Mamo Loma posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to Major Mamo Loma:

Share

Category