20/08/2026
በየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር “6400 A” የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ
ነሐሴ 14/2018 ዓ/ም የካ ወረዳ 12 ኮሙኒኬሽን
በየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎንና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ “6400 A” የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት የማስተዋወቂያና በክፍለ ከተማ ደረጃ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ያስጀመረው ይህ የዲጂታል በጎነት ፕላትፎርም፣ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከተረጅነት በዘላቂነት ለማቃለል የሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በቀላሉ በበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ ለማሳተፍ ያለመ ነው።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የየካ ክፍለ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ መገርሳ ገላና በክፍለ ከተማው በርካታ ሰው ተኮር የሆኑ የበጎ ፈቃድ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀው ሁሉም ሰው የበኩሉን አስተዋፅኦ ሲያደርግ የሰው ሰራሽና ተፈጥሮዊ አደጋን በእራሳችን አቅም ለመፍታት በጋራ መስራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ መሰለች አቡዬ በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ ተግባር ለበርካታ አቅመ ደካማ ወገኖች፣ ለሀገር ባለውለታዎችና ለዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረስ መቻሉን ያስረዱ ሲሆን የ“6400 A” ዲጂታል በጎነት ፕሮጀክትም በተለይ አቅመ ደካማና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመድረስ የሚያግዝ በመሆኑ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በፕላትፎርሙ ላይ በመሳተፍ የበጎነት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የ“6400 A” ፕላትፎርም የበጎነት ባህልን በበለጠ ለማስፋፋት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ዘላቂ ጠቀሜታ ለመፍጠር አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ወደ 6400 “A” የጽሑፍ መልዕክት (SMS) በመላክና በቀን 1 ብር በመለገስ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን በመደገፍ በጎነትን ማስፋፋትና ፕሮጀክቱ የተቀመጠለትን ዓላማ እንዲያሳካ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ ቀርቧል።