25/12/2025
(ዘ-ሐበሻ ዜና) በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ ተርፋም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ታኅሣሥ 15 ቀን 2018 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 24/2025) በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 47 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ምንጮች ገለጹ። በዚሁ ዕለት በክልሉ የተቀሰቀሰውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከትሎ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን (MSF) ከመቶ በላይ በጦር መሣሪያ የቆሰሉ ሰዎችን ማከሙን አስታውቋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በተርፋም ንዑስ ከተማ የመኖሪያ መንደር ውስጥ ሲሆን፣ ሰለባዎቹም ሴቶች፣ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞችን ያካተቱ መሆናቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል። በጥቃቱ የመኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውና ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውም ተመልክቷል። ድርጊቱ ድንበር ተሻግረው ከመጡ ግለሰቦች ጋር በተቀናጀ ሁኔታ የተፈጸመ መሆኑን ምንጮች ቢጠቁሙም፣ የሟቾች ቁጥር ከመጀመሪያ ደረጃ መረጃ የተገኘ በመሆኑ ወደፊት ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።
የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ታኅሣሥ 15 ቀን ባወጣው እና ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መግለጫ፣ በክልሉ ያለው ግጭት ከጠዋት ጀምሮ መጠናከሩንና ድርጅቱ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከ100 በላይ በጦር መሣሪያ የቆሰሉ ሰዎችን መቀበሉን አረጋግጧል። ግጭቱ የሚቀጥል ከሆነ በቀጣይ ቀናት ተጨማሪ ቁስለኞች ሊመጡ እንደሚችሉም ድርጅቱ አስጠንቅቋል።
ይህንን እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ የጋምቤላ ክልል መንግሥት ታኅሣሥ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚተገበር ያልተገደበ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሏል። ገደቡ የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ አለመረጋጋት የሚታይባቸውን ሌሎች አካባቢዎችን የሚሸፍን መሆኑ ተገልጿል።