Gezahegn Kabthyimer

Gezahegn Kabthyimer This is my page to share and deliver information when needed

21/03/2026
18/01/2025

[እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ]
✍ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ (በድጋሚ ፓስት የተደረገ)
💥 ጥምቀት ማለት ቃሉ የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውሃ ውስጥ ገብቶ መውጣት” ማለት ነው፡፡

💥 ምስጢረ ጥምቀትን የመሠረተልን ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ሲመሠርትም በማዘዝ ብቻ ሳይሆን በሥራ በማሳየት ጭምር ነው (ማቴ 3፡17፤ ማር 1፡9፤ ሉቃ 3፡21፤ ዮሐ 1፡31)፡፡

💥 ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እከብር አይል ክቡር የባሕርይ አምላክ ሆኖ ሳለ በዮርዳኖስ ወንዝ በአገልጋዩ (በፍጡሩ) በዮሐንስ የተጠመቀበት ምክንያት፦
1) አንድነቱን ሦስትነቱን ለመግለጽ
2) የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ (ቆላ 2:14)
3) በእርሱ ጥምቀት የእኛን ጥምቀት ለመቀደስ
4)ለጥምቀታችን ኀይልን ለመስጠት
5) ለአብነት ርሱ ተጠምቆ እናንተም ተጠመቁ ብሎ አርአያና ምሳሌ ለመሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በ30 ዘመኑ ጥር 11 ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት፤ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡

💥 ጌታችን በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅና የዮርዳኖስ ወንዝ ጌታን ስታይ እንደምትሸሽ ነቢዩ ዳዊት በመዝ 113፡3-5፦
✍️ “ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፤ ተራሮች እንደ ኮርማዎች፥ ኮረብቶችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ፤ አንቺ ባሕር የሸሸሽ፥ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለስሽ ምን ሆናችኋል?” በማለት ከ1000 ዓመት አስቀድሞ ትንቢት የተናገረ ሲሆን፤ ብዙ ምሳሌም አለውና ከትርጓሜ ወንጌል ይመልከቱ፨

💥 ዮሐንስ ወደ ጌታችን መምጣት ሲገባው ጌታችን ወደ ዮሐንስ የሄደበት ምክንያት የመጀመሪያው ትሕትናን ለማስተማር ነው።
✍️ ሁለተኛው ለአብነት ለምሳሌ ነው፤ ይኸውም ዮሐንስ ሄዶ አጥምቆት ቢሆን ዛሬ ባለሥልጣናቱ ካህናትን ቤታችን ድረስ መጥታችሁ አጥምቁን ይሏቸው ነበርና ሰማያዊ ንጉሥ እኔ ከሄድኩ እናንተም ሄዳችሁ ቤተ ክርስቲያን ተጠመቁ ለማለት ሄዷል።

💥 ዮሐንስ ግን ወደርሱ በትሕትና የመጣው አምላኩ ክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን?” ሲል ጌታችንም “ጽድቅን ልንፈጽም” ይገባናል ብሎ ትንቢተ ነቢያትን ሊፈጽም እንደመጣ ሲነግረው ዮሐንስ እሺ አለ።

💥 ከዚያም ተያይዘው ወደ ዮርዳኖስ ሲወርዱ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንደሚያስተምሩት የዮርዳኖስ ወንዝ ወደ ኋላዋ ሸሽታለች በዚህም ዳዊት በመዝ 77፡16 ላይ፦
✍️ “አቤቱ፥ ውሆች አዩህ ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውሆችም ጮኹ” ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ።

💥 ጌታችንም ተጠምቆ ከውሃው ከወጣ በኋላ ሰማይ ተከፈተ ይላል። መተርጉሙ ሲያመሰጥረው፦
1) "ከመ ተጠምቀ ሰማያዊ ናሁ ወረደ እምሰማይ ወሀለዎ ከመ ይዕርግ ውስተ ሰማይ" (ሰማያዊው እንደተጠመቀ ከሰማይ እንደወረደ ወደሰማይ እንደሚያርግ ለማስረዳት)

2) "ወዳግም እስመ አናቅጸ ሰማያት ተዐጽዉ በምክንያተ ዕልወተ አዳም ..." (በአዳምና በሰዎች በደል ምክንያት የሰማያት ደጆች ተዘግተው ነበር። ገነትም ተዘግታ በእሳት ጦር ትጠበቅ ነበር። ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ በጥምቀቱ ምክንያት የሰማይ ደጃፎች ተከፈቱ)።

3) "ሣልስ ያጠይቀነ ከመ እለ ይጠመቁ ይትረኃው ሎሙ አናቅጸ ሰማያት ..." (ለሚጠመቁ ሰዎች የሰማያት ደጃፎች እንደሚከፈቱላቸውና ከሞት ከተነሡ በኋላ ወደ ሰማይ እንደሚወጡ ያስረዳል)።

4) ሰማያት ተከፈቱ መባሉ ደጃፍ በተከፈተ ጊዜ በውስጥ ያለው ዐዲስ ነገር እንዲገለጥ በጥምቀትም ዐዲስ ምስጢር ይገለጣልና ነው።

💥 አብ በሰማይ ኹኖ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ” (በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይኽ ነው) ብሎ ሲመሰክር፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ፤ አካላዊ ቃል ክርስቶስም በጽንፈ ዮርዳኖስ ቁሞ ታየ፡፡

💥 መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ለምን ወረደ? ቢባል
✍️ ርግብ ኀዳጊተ በቀል (በቀልን የምትተው) ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ኀዳጌ በቀል፤ ቸር ነኝ ሲል፡፡
✍️ ርግብ ልጆቿን ተከባክባ እንድታሳድግ፤ መንፈስ ቅዱስም ለምእመናን ልሕቀት መንፈሳዊ እሰጣለኊ ሲል፡፡
✍️ ርግብ በኖኅ ጊዜ የጥፋት ውሃ መጒደሉን የወይራ ቅርንጫፍ ይዛ ብሥራተ ፍሥሐ የምሥራችን እንደገለጸች፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል በመውረድ ከርሱ ጋር የሥልጣን አንድነት ባለው በወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ በመቀመጥ የፍዳ ዘመን ማክተሙን ተስፋ መስቀልን አብሥሯል፡፡
✍️ ርግብ ክንፏን ቢመቷት፤ ዕንቊላሏን ቢሠብሩባትም ቤቷን ካላፈረሱባት በቀር አትኼድም፤ መንፈስ ቅዱስም ምንም ኀጢአትን ቢሠራም፤ ጨርሰው ካልካዱት በስተቀር አይለይምና፡፡

💥 ይኸውም በምስጢረ ሥላሴ ትምህርት እንደምንረዳው ከሰማይ ኾኖ የመሰከረው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ በቃልነት መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስነት ያሉበት (ሕልው የኾኑበት) አብ ነው።
✍️ ወርዶ በወልድ ራስ የተቀመጠው አብ በልቡናነት አካላዊ ቃል ክርስቶስ በቃልነት ሕልው የኾኑበት መንፈስ ቅዱስ ነው።
✍️ በጽንፈ ዮርዳኖስ ቆሞ የታየው አብ በልቡናነት መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስነት ሕልው የኾኑበት አካላዊ ቃል ክርስቶስ ነው፤ እንዲኽ አድርገው የአካል ሦስትነታቸውን የፈቃድ አንድነታቸውን ለማስረዳት አብ በደመና ኾኖ መሰከረ፤ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ታየ፤ አካላዊ ቃል ክርስቶስ በጽንፈ ዮርዳኖስ ቆሞ ታየ።

♥ በዚኽም የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በሚገባ ሲታወቅ በተጨማሪም “በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይኽ ነው” ብሎ እግዚአብሔር አብ በመመስከሩ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው በኋለኛው ዘመን ከእመቤታችን ያለ አባት በኅቱም ድንግልና የተወለደው እግዚአብሔር ወልድ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው አንድ ብቻ መኾኑ በሚገባ ተረጋግጧል፤ ዕለቱም በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋንያ ሲባል በግእዝ አስተርእዮ በዐማርኛም የመታየት የመገለጥ ጊዜ ተብሏል፡፡

♥ ኢትዮጵያ ሀገራችን ስለ ነገረ ጥምቀት የሰማችው ከሌላው ዓለም አስቀድማ ጌታችን ባረገ በጥቂት ወራት (በ34 ዓ.ም) በኢትዮጵያው ጀንደረባ አማካይነት ነው (የሐዋ 8፥26-39)፤ ይህም በዐል ከዘጠኙ ዐበይት በዐላት አንደኛው ሲሆን ጌታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ስላመራ ይህንን ለማሰብ ታቦታቱ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ያመራሉ።

♥ በዚህ መልኩ መከበር እንዴት ተጀመረ? የሚለውን ሊቀ ትጉኃን ኃይለ ጊዮርጊስ በጻፉት የነገረ ሃይማኖት መጽሐፍ ላይ የጻፉትን ለአንባብያን ለማካፈል ወደድኩ። ይኸውም ከ515-529 ዓ.ም ለ14 ዓመት ኢትዮጵያን በመሩት በአጼ ገብረ መስቀል ዘመን ሲሆን በጊዜው ቅዱስ ያሬድ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ ከዝማሬው በመነሣት ታቦታቱ ጥር 11 ጠዋት ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ አምርተው አመሻሹ ላይ ይመለሱ ነበር ብለዋል፡፡

♥ ጸሐፊው በመቀጠል ሲያብራሩ ከዚያም ከ1157-1197 ዓ.ም ድረስ ለ40 ዓመት ኢትዮጵያን በመራው በታላቱ ጻድቅ ንጉሥ በላሊበላ ዘመን በአንድ አካባቢ ያሉ አብያተ ክርስትያናት ታቦታቱ ባንድ ላይ እንዲያከብሩ ንጉሥ ላሊበላ ታላቅ መንፈሳዊ ዐዋጅን አሳውጆ በአንድ አካባቢ፣ ወረዳ፣ ያሉ በአንድ ላይ ማክበር ጀመሩ፤ በርሱ ዘመን የነበሩት ታላቁ ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በጎንደር፣ በሸዋ፣ በአንኮበር፣ በመርጡለ ማርያም እየሄዱ ባሕረ ጥምቀቱን እንደባረኩ ይጽፋሉ፡፡

♥ በመቀጠልም ከ1245-1268 ዓ.ም ለ23 ዓመት ኢትዮጵያን በመሩት በዐጼ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አሳሳቢነት ታቦታቱ በባሕረ ጥምቀት ሲውሉ ምእመናን በታላቅ ድምቀት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ እንዲውሉ መንፈሳዊ ዐዋጅ አሳወጁ በማለት ገልጸዋል፡፡

♥ በመቀጠል ከ1426-1460 ዓ.ም ለ34 ዓመት ኢትዮጵያን በመሩት በታላቁ ንጉሥ በዐጼ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥትም ንጉሡ ከሊቃውንት ጋር በመወያየት የበዐሉን ታሪክ ተከትሎ ታቦታቱ ጥር 10 ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት እንዲወርዱና ጥር 11 እንዲመለሱ መወሰኑን ሊቀ ትጉኃን ኀይለ ጊዮርጊስ በመጽሐፋቸው ላይ ይተነትናሉ።

💥 እንደሚታወቀው ታቦተ ጽዮን በሄደችበት ሁሉ በረከትን ትሰጥ እንደነበር የአቢዳራን ቤት በበረከት እንደሞላች፤ የዮርዳኖስን ባህር እንደከፈለች፣ የኢያሪኮን ቅጽር እንዳፈረሰች፣ የፍልስጤማውያን ጣዖት ዳጎንን ቀጥቅጣ እንዳጠፋች ሀገሪቱ ትባረክ ዘንድ ርኲሳን መናፍስት ይርቁ ዘንድ ምድሪቱ በቃል ኪዳኑ ታቦታት ትቀደስ ዘንድ ታቦታቱ በመጡበት መንገድ እንዳይመለሱ ታላቅ ዐዋጅ አሳውጀው በዐዋጁ መሠረት ዛሬ ድረስ በደመቀ መልኩ በዓሉ እየተከበረ ይገኛል ብለው ታሪካዊ ዳራውን ጽፈዋል፡፡

💥 ከባሕር ማዶ ጸሐፍያን ውስጥ ቼሩሊ በዐጼ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ቁመቱ 14 ወርዱ 8 ክንድ የኾነ ባሕረ ጥምቀት እንደተዘጋጀ ሲጽፍ፤ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዐጼ ልብነ ድንግል በተገኙበት እጅግ ታላቅ ድንኳን በባሕረ ጥምቀቱ ዙሪያ እንዴት ተተክሎ እንደተከበረ ፍራንቺስኮ አልቫሬዝ ገልጿል፤ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውን የበዓለ ጥምቀት አከባበር ደግሞ ፔድሮ ፔየዝ ዘግቦት ነበር።

💥 አሁን ባለንበት ጊዜም ዳዊት በመዝ 44፡16 ላይ “በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ” በማለት እንደተናገረ ከመቼውም በበለጠ እግዚአብሔር የወጣቱን ልብ በረድኤት ጎብኝቶት "አልፋ ወዖ ቤጣ የውጣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው ወወልደ ማርያም ሥግው" ተብሎ ሕይወት የሆነው የአምላካችን የኢየሱስ ስም ለተጻፈበት ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለሚሠዋበት ለቃል ኪዳኑ ታቦታት ክብር አካባቢውን እያስዋበ፣ ታቦታቱ የሚሄዱበትን መንገድ እየጠረገ፤ ታላላቅ ምንጣፎችን ታቦታቱ በሚሄዱበት መንገድ እያነጠፈ ለቃል ኪዳኑ ታቦት እንደ ነቢዩ ዳዊት ከፍተኛ ክብር በመስጠት እግዚአብሔርን እያገለገለ ይገኛል (1ኛ ነገሥት 6፡1-23)፡፡

“የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት” (ኢያ 3፡3)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
♥ ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ [በድጋሚ ፓስት የተደረገ]
የቴሌግራም ቻናል፦ https://t.me/Rodas9
የYoutube Channel:- https://youtube.com/channel/UCFKnpmDyWe3LQ_9Gx3TMnAg

Address

Addis Ababa

Telephone

0911487717

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Gezahegn Kabthyimer posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to Gezahegn Kabthyimer:

Share

Category