04/09/2026
በጷጉሜን እና በአዲሱ ዓመት የበዓላት ሰሞን የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ ለ11ዱም ክፍለ ከተማ የብሎክ አመራሮች የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።
AAFDRMC ነሐሴ 29/2018 አዲስ አበባ
የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ቅነሳ ዘርፍ የጷጉሜን ቀናት እና ከሚጠበቀው የ2019 አዲሱ ዓመት በዓላት ጋር ተያይዞ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ድንገተኛ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከ11ዱም ክፍለ ከተሞች ለተወጣጡ የብሎክ አመራሮች ስልጠና ሰጥቷል።
የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ምስክትል ኮሚሽነር አቶ ደሳለኝ ፉፋ በስልጠናው ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ በየክፍለ ከተማውና በየአካባቢው የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ተከስተው የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ ስጋቶችን አስቀድሞ የማወቅና የመከላከል አቅምን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም የብሎክ አመራሮች ከዚህ ስልጠና ያገኙትን እውቀትና ግንዛቤ ወደ ታች በማውረድ፣ የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ በማስተማርና በማሳተፍ በበዓላት ሰሞን የተቀናጀ የአደጋ ደህንነት ንቅናቄ እንዲፈጥሩ አሳስበዋል።
ስልጠናውን የሰጡት በዘርፉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ግንዛቤና ስርፀት ቡድን መሪ አቶ መኩሪያ መንግስቴ እንደ ገለጹት በመዲናችን በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚከሰቱ አደጋዎችን የመከላከል ስራ ውጤታማ የሚሆነው በህዝብ አደረጃጀቶች ንቁ ተሳትፎ መሆኑን ጠቅሰው፤ የብሎክ አመራሮች ማህበረሰቡን በቀጥታ የሚያገኙ እንደመሆናቸው መጠን ሚናቸው የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።በማብራሪያቸው ለብሎክ ለአመራሮቹ የተለያዩ የአደጋ መንስኤዎችንና ቅድመ ጥንቃቄዎችን የተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሰልጣኞች በበዓላት ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመግታት የሚያስችል ጠቃሚ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸው፣ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመወጣት አዲሱ ዓመት የሰላምና ከአደጋ የጸዳ እንዲሆን አካባቢያቸውን በመጠበቅና ህብረተሰቡን በማንቃት በተነሳሽነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
#አደጋስጋትቅነሳ #አዲስአበባ #ጷጉሜን #አዲስዓመት #የአደጋደህንነት