02/09/2026
ኢትዮጵያ፡ የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የዘመናዊነት....!
ጥንታዊቷና ውቢቷ ኢትዮጵያ፤ በተፈጥሮ ጸጋዎቿ፣ በታሪኳና ማህበራዊ እሴቶቿ ታላቅ የቱሪዝም ገነት ስለመሆኗ ምስክር አያስፈልገውም።
ከተራሮች እስከ ዝቅተኛው የጨው ሜዳ፣ ከጥንታውያን የድንጋይ ውቅር ሕንጻዎች እስከ ዘመናዊ የከተማ መዝናኛዎች ድረስ ኢትዮዽያ ለዓለም ህዝብ የምታቀርበው አስደናቂ እይታና የማይረሳ ገጠመኝ እጅግ ብዙ ነው።
የኢትዮጵያን ተፈጥሮአዊ ውበት ልዩ ከሚያደርጉት መዳረሻዎች መካከል የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በአስደናቂ የተራራ ሰንሰለቶቹ የሚታወቀው ይህ ስፍራ እንደ ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ እና የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ ያሉ ብርቅዬ እንስሳት መኖሪያ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የአፍሮ-አልፓይን ሥነ ምህዳር መገለጫ በመሆን ለተፈጥሮ አፍቃሪያን ልዩ እርካታን ይሰጣል።
ወደ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል ስናቀና ደግሞ በአፋር ክልል የሚገኙት ኤርታአሌ እና ዳሎል የተፈጥሮ ተአምራትን ይገልጡልናል።
ኤርታአሌ በዓለም ላይ ካሉ ጥቂት ንቁ የእሳተ ገሞራ ሐይቆች አንዱ ሲሆን ዳሎል ደግሞ በተለያዩ ቀለማት ባበቡ የጨው ሜዳዎቹ የሚታወቅ ልዩ ተፈጥሮ ነው።
በተጨማሪም የዓባይ ምንጭ የሆነው ጣና ሐይቅ በዙሪያው ከሚገኙት ደሴት ገዳማትና ከታላቁ የዓባይ ፏፏቴ ጋር ተደምሮ ጎብኚዎችን በምትሐታዊ ውበቱ ያፈዝዛል።
የሰው ልጅ መገኛ ብቻ ሳትሆን የጥንታዊ ሥልጣኔዎች ባለቤትም የሆነችው ኢትዮጵያ ከድንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት እና የአክሱም ሐውልቶች የኢትዮዽያን የገዘፈ ጥንታዊ ሥልጣኔ ይመሰክራሉ።
እንዲሁም የጎንደር ፋሲል አብያተ መንግሥታት የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በቅርቡ የተከናወነው የቅርስ እድሳት ደግሞ ታሪክን ከውበት ጋር በማጣመር ለጎብኚዎች ተመራጭ መዳረሻ አድርጎታል።
በዩኔስኮ የተመዘገበችው የሐረር ከተማ በኮሪደር ልማት በተዋቡ ጎዳናዎቿ፣ በቀለም ባሸበረቁ ባህላዊ ቤቶቿ እና እንግዳ ተቀባይ ባህሏ ልዩ ውበትን ትፈነጥቃለች።
ከዚህ በተጨማሪ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ እየተቀየረ ይገኛል።
የከተማ ቱሪዝምን በአዲስ መልክ ያደሱት ብሔራዊ ቤተ መንግሥት፣ አንድነት ፓርክ እና ወዳጅነት ፓርክ ታሪካዊ እሴቶችን ከዘመናዊ የመዝናኛ ስፍራዎች ጋር አጣምረው ለህዝብ ክፍት ሆነዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የታሪክ ታላቅነት የሚያወሳው የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ ከተፈጥሮ ጋር ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያጣመረው እንጦጦ ፓርክ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከቱሪዝም ጋር የሚያገናኘው የሳይንስ ሙዚየም የመዲናዋን የወደፊት ራዕይ እና የፈጠራ አቅም ለዓለም የሚያሳይ ድንቅ እይታዎች ሆነዋል።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባህል እና የዘመናዊነት ውህደት የሆነች፣ እያንዳንዱ እርምጃ አዲስ ታሪክና ውበት የሚተርክባት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደር የሌላት እውነተኛ የቱሪዝም ገነት ናት።