01/10/2025
ኢትዮጵያ በብዝሃ ማንነት፣ ባህልና እሴቶች የደመቀች ፣ በህብረ ብሄራዊነት የተጋመደች፣ ወንድማማችነትን ከፍ አድርጋ ያፀናች ታላቅ ሀገር ናት።
የመስከረም ወር ለኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት ተስፋ የሚሰነቅበት እና በርካታ ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት የሚከበሩበት ልዩ ወር ነው።
ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ያሸጋገረዉን አምላኩን የሚያመሰግንበትና መጪዉን ዘመን የሰላምና የደስታ እንዲሆንለት የሚለምንበት በዓል ነዉ።
ኢሬቻ የአንድነት፣ የሰላም እና የወንድማማችነት ምልክት በመሆኑ ከኦሮሞ ህዝብ በተጨማሪ በርካታ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄሰቦች አብረው የሚያከብሩት፣ ለሰላምና ወንድማማችነት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ የተነሳ በአለም አቀፍ ደረጃ ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል በዩኔስኮ የተመዘገበ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን በዓል ነዉ ።
በኢሬቻ ቂም በይቅርታ ይሻራል፣ ጨለማ ለብርሀን እጁን ይሰጣል፣ የተለያየ ይገናኛል፣ የተጣላ ይታረቃል፣ ጥላቻ ቦታውን ያጣል ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት እና አብሮነት ይነግሳል።
ብልጽግና የአደባባይ በዓላት ለሀገር ገፅታ ያላቸውን ጉልህ ሚና በመረዳት ባማረና በደመቀ ድባብ በሰላም ይከበሩ ዘንድ በትብብር ይሰራል። ሰላም ለልማት፣ ለዜጎች ዘላቂ ተጠቃሚነትና አብሮነትና ለሁለንተናዊ ዕድገት መሰረት የሆነ ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ የሰላም አማራጮችን ቅድሚያ እየሰጠን የአደባባይ በዓላቱን ለሀገር ገፅታ ግንባታ ማዋል ወሳኝ ነው።