01/09/2026
የፀጥታ ኃይሉ የህዝብን ሰላም ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ ፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
አሰኮ፣ ነሐሴ 26 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢ.ፌ.ፖ.ሚ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ አዛዥ ኮማንደር ኢብራሂም መሀመድ በምስራቅ አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ከሕዝብ ጋር በተካሄደ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ እንደገለፁት የፀጥታ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ የህዝቡን ሰላም በጀግንነት ለማስከበር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
አዛዡ ልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እያካሄደ ባለው ኦፕሬሽን በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ለማፅዳት የጀመረውን ኦፕሬሽን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አያይዘውም የኢትዮጵያ ህዝብ የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነቶች ሳይገድቡት ከልዩነት ይልቅ በአንድነት፣ በፍቅር፣ እርስ በእርስ በመከባበርና በመተባበር ለሺህ ዓመታት አብሮ የኖረበት እሴት ያለው ሕዝብ በመሆኑ የትኛውም አካል ሰላሙንና ደህንነቱን ሊያናጋው እንደማይችል ገልፀዋል።
ማንኛውንም የልዩነት ጥያቄ በኃይል ሳይሆን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ ያሳሰቡት የልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ አዛዥ በፀረ-ሰላም ኃይሎች ተደልለውና ተገፋፍተው ወደ ጥፋት የገቡ ግለሰቦች ድርጊታቸው ሕዝብንና ሀገርን የሚጎዳ መሆኑን ተገንዝበው በፍጥነት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሰኮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጋቢ ጋልቹ በበኩላቸው የፀጥታ አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባከናወኑት የፀጥታ ማስከበር ተግባር በአካባቢው የነበረውን ስጋት በመቅረፍ አበረታች ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
በምርጫ ወቅት ጠላት በአሰኮ ወረዳ የምርጫውን ሂደት ለማስተጓጎልና አካባቢውን ለማወክ ያደረገውን ጥረት ህዝቡና የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ጠንካራ ቅንጅት በማክሸፋቸው ምርጫውም በሰላማዊ ሁኔታ በስኬት መጠናቀቁን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በተካሄደው የተቀናጀ ኦኘሬሽን በአሰኮ ወረዳ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑንና ይህም በዞንና በክልል ደረጃ ትልቅ ትኩረት ያገኘ ሥራ መሆኑን ያነሱት አስተዳዳሪው የወረዳው ሰላም ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት እስኪመለስ የህብረተሰቡ እና የፀጥታ ኃይሉ ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።