03/09/2026
አካዳሚው የአንደኛ ዙር ምልመላውን ገመገመ
ነሀሴ 28/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ለ2019 ዓ.ም የስልጠና ዘመን ለአዲስ አበባ እና አሰላ (ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል) ካምፓሶች በ10 ስፖርት አይነቶች የፀጥታ ችግር ከሌለባቸው ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በአጠቃላይ በሁለቱም ካምፓሶቹ 158 ወንድ እና 200 ሴት በድምሩ 358 ተተኪ ስፖርተኞችን አስገብቶ ለተከታታይ አራት አመታት ለማሰልጠን በመላው ሀገሪቱ 19 የጉዞ መስመሮችን እና በ65 የምልመላ ጣቢያዎችን በማዘጋጀት በሁለት ዙር ከነሀሴ 4-25 /2018 ዓ.ም ሲያካሂድ የቆየውን የመጀመሪያ ዙር የእጩ ተተኪ ስፖርተኞች ምልመላን ዛሬ ነሀሴ 28/2018 ዓ.ም በአካዳሚው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ገምግሟል።
በግምገማ መድረኩ በተዘጋጀዉ ፍኖተ ካርታ መሰረት ሁሉም የመልማይ ኮሚቴ የቡድን ሰብሳቢዎች (ፀኃፊዎች) እንደየስፖርት አይነቱ በተዘጋጀው የመመልመያ መስፈርት መሰረት በምልመላው የሰሩትን ስራ እና ያጋጠሟቸውን ችግሮች እንዲሁም ለቀጣይ ይጠቅማሉ ያሏቸውን ምክረ_ሀሳቦችን አጠር ያለ ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ከሪፖርቱ እና በውይይቶች በተገኘው መረጃ በየምልመላ ጣቢያው ከፍተኛ የእጩ ሰልጣኞች መኖር፣ የቡድን አባላት ስራዎችን በቅንጅት መስራታቸው ፣ የእድሜ ተገቢነት ችግር ከፍ እና ዝቅ ብሎ መኖሩ፣ ደረጃውን የጠበቀ የማዘውተሪያ ስፍራ ችግር፣ በአንዳንድ ስፖርት አይነቶች የሴት እጩ ተመልማዮች ቁጥር አናሳ መሆኑ፣ የፓራለምፒክ ተመልማዮች አናሳ መሆን፣ የአየር ንብረት ችግር (ዝናብማ) መሆን፣ ለምልመላ የሚያገለግሉ የቁሳቁስ እጥረት መኖሩ፣ በአንዳንድ ክልሎች የአካዳሚው የምልመላ መረጃ ደርሷቸው ወደ ዞኖች እና ወረዳዎች አለማውረድ በዋናነት በጥንካሬ እና በተግዳሮት ተገልጿል።
በመጨረሻም የአካዳሚው የአስተዳደርና ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፍቃዱ መኩሪያ እና የአካዳሚው አሰላ ካምፓስ ካምፓስ ዋና ዲን አቶ መሀመድ ጃርሶ የግምገማ መድረኩን ሲያጠቃልሉ ባስተላለፉት መልዕክት እና በሰጡት የስራ አቅጣጫ በምልመላው የተሳተፉትን አጠቃላይ አባላት ለስራው መሳካት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ካመሰገኑ በኃላ የዘንድሮው ምልመላ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተደራሽነቱ ሁሉንም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮችን በማማከል ከወትሮው የተሻለ የምልመላ አደረጃጀት እና ስምሪት ተሰጥቶ ሰራው በአግባቡ መሰራቱን እና ለተነሱ ጥያቄዎች ቴክኒካዊ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
አያይዘውም አካዳሚው በቀጣይ በጊዚያዊነት በያዘው ፕሮግራም ከመስከረም 05-12/2019 ዓ.ም ለሁለተኛ ዙር (የማጠቃለያ) ምልመላ የሚጠሩ እጩ ሰልጣኞችን በቴክኒክ ኮሚቴው ተለይተው በአስቸኳይ ጥሪ እንዲደረግላቸው አቅጣጫ በማስቀመጥ የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል።
ማሳሰቢያ
አካዳሚው ለሁለተኛ (ለማጠቃለያ) ምልመላ የምትጠሩ እጩ ስፖርተኞችን በተንቀሳቃሽ ስልካችሁ የሚያሳውቅ ስለሆነ ስልካችሁን ክፍት እንድታደርጉ እያሳሰበ በተጨማሪም ለክልል እና ከተማ አስተዳደሮች ስፖርት ቢሮዎች አካዳሚው በህጋዊ ደብዳቤ የምናሳውቅ መሆኑን እየገለፅን በተጨማሪም በማህበራዊ ድህረ_ገፃችንም ከምልመላው ጋር የተያያዙ ተከታታይነት ያላቸው መረጃዎችን የምንሰጥ መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን።
ለበለጠ መረጃ
ፌስቡክ https://www.facebook.com/profile.php?id=100064708597717&mibextid=ZbWKwL
ቴሌግራም https://t.me/+0K6_bE7YFzU5YmY0
ድህረ ገፅ http://www.esacademy.gov.et/
ቲክቶክ www.tiktokcom@ethiopiansportsacademy" rel="ugc" target="_blank">https://www.tiktokcom@ethiopiansportsacademy
"ወርቃማ የትውልድ ቅብብሎሽን እናረጋግጣለን"
”We Ensure the Golden Generational Continuity”