07/09/2026
የአፍሪካ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የአየር ንብረት እርምጃዎችን በምግብ ስርዓቶች እና በግብርና ላይ ለማጠናከር ያለመ አህጉራዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።
አዲስ አበባ ጳጉሜን 2 / 2018 ዓ.ም (የፕ.ል.ሚ)
በአፍሪካ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላቸውን ንቁ ተሳትፎ ለማጠናከር ያለመ አህጉራዊ መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።
በአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ትብብር (Alliance for Food Sovereignty in Africa) እና በተባባሪ ድርጅቶች አዘጋጅነት ለሶስት ቀናት የሚቆየው ይህ ታላቅ ጉባኤ በምግብ ስርዓቶችና በግብርና ላይ የአፍሪካን አቅም ለማጠናከር እና የተናበበ አህጉራዊ አቋም ለመገንባት ያለመ ነው።
በጉባኤው ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ 100 የሚጠጉ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች፣ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች እና የአየር ንብረት ተደራዳሪዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የያደም (YADAM) ፋዉንዴሽን መስራች እና የአፍሪካ የስነ-ምግብ አምባሳደር አቶ ደመቀ መኮንን በመርሃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ስነ-ምግብ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለአገርና ለአህጉር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንዲሁም ለተሻለ አእምሯዊና አካላዊ ልማት ወሳኝ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ስነ-ምግብ፣ ጤና እና የአየር ንብረት ለውጥ ተነጣጥለው የማይታዩና ለአጠቃላይ ስነ-ምህዳር ጤናማነት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው መሆናቸውን አብራርተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የፅህፈት ቤት ሃላፊ ሀና አበበ በበኩላቸው፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋን በመወከል ባደረጉት ንግግር፣ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ የምግብ ዋስትና እና በግብርና ምርታማነት ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ጠንካራ አህጉራዊ አቋም መያዝ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ የግብርና ዘዴዎችን፣ የስነ-ምህዳር ጥበቃን እና የስነ-ምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ አሰራሮችን መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ጉባኤዉ በአፍሪካ የምግብ ስርዓትና ግብርና ዘርፍ የሚታዩ ተደራራቢ ፈተናዎችን በመፍታት፣ ዘላቂ የግብርና አሰራሮችን በማጎልበት እና አፍሪካውያን በአለም አቀፍ መድረኮች አንድ ወጥ አቋም እንዲይዙ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል።