04/09/2026
“ኪነ-ጥበብ ለአካል ብቃት፤ ለአእምሮ ንቃት” በሚል መሪ ቃል ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረው ታላቅ የኪነ-ጥበብ የንቅናቄ መድረክ በታላቅ ድምቀት ተጠናቀቀ!
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
ባኪ በቢሮ | ነሃሴ 29/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ኪነ-ጥበብ ቢሮ በተፈሪ መኮንን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ባዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ ከ300 በላይ አማተር የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የከተማዋን የኪነ-ጥበብ እንቅስቃሴ ወደ አዲስ የፈጠራ ምዕራፍ ማሸጋገርና የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ነው። ኪነ-ጥበብ የማኅበረሰብን ማንነት ከማንጸባረቅ ባለፈ አማተሩን ከእውቅ አርቲስቱ ጋር የሚያቀራርብ፣ ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክርና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው በመሆኑ፣ ቢሮው ይህንን እምቅ አቅም ለመጠቀምና ባለሙያዎችን ወደ ተሻለ የሙያ ደረጃ ለማሸጋገር ይህንን አዲስ የሥልጠና፣ የንቅናቄና የልምምድ እድል አመቻችቷል።
በማጠቃለያ መድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ባህል እና ኪነ-ጥበብ ቢሮ አመራሮች የስራ መመሪያና አደራ ያስተላለፉ ሲሆን፣ የቢሮው ም/ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አዲሱ ሻንቆ ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየርና ሙያዊ ስነ-ምግባርን በመላበስ የሀገራቸውን ስም እንዲያስጠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የቢሮው የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሉባባ ጀማል የሀገርን ባህልና እሴት ጠብቆ ኪነ-ጥበብን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ኃላፊነት የወጣቶችና የባለሙያዎች ድርሻ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም የኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪ ማበልፀግና ማስፋፋት ዳይሬክተር አቶ ፀጋ ተመም ባስተላለፉት መልዕክት፣ መዲናችን አዲስ አበባ ለዘርፉ በሰጠችው ልዩ ትኩረት ውብ የማሳያ መድረኮች መገንባታቸውን ጠቅሰው፣ የኪነ-ጥበብ ማህበረሰቡም ይህንን የሚመጥን ጥራት ያለው ስራ ማቅረብ አለበት ካሉ በኋላ ቢሮው ዘርፉን የበለጠ ለማጠናከር ለተለያዩ ባለድርሻ አካላትና መምህራን የሚሰጠውን ድጋፍና ስልጠና አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ንቅናቄው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ አስዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት በቢሮው ከፍተኛ አመራሮች ተበርክቶላቸዋል።