22/08/2026
"የበጎ አድራጎት ተግባራት ማኅበራዊ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ፣ የዜጎችን በልማት ሥራዎች የመሳተፍ ባህል እያሳደጉ ነው" ክቡር አቶ ደንጌ ቦሩ
በባህር ዳር ከተማ ለሦስት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ መሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ።
ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. (ትሎሚ) — በባህር ዳር ከተማ ለሚገኙ ወተት በር ፣ አየር ጤና እና ድል ችቦ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት መሠረተ ድንጋይ ተቀምጧል።
የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ፣ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ጎሹ አንዳለማሁ ፣የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፍራኦል ጣፋ እና ሌሎች የፌዴራል እና የአ/ብ/ክ/ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከናውኗል።
የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ትብብር የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ደንጌ ቦሩ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መሪነት ባለፉት ዓመታት የበጎ አድራጎትና የማኅበራዊ ተሳትፎ ሥራዎች እየተጠናከሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ደንጌ ገለጻ፣ እነዚህ ተግባራት የመደመርና የብልጽግና እሳቤዎች ውጤት ሲሆኑ፣ የደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት ግንባታ፣ የችግኝ ተከላ፣ የኢኮኖሚ ውስንነት ላለባቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የመማሪያ ክፍሎች ግንባታን ያካትታሉ።
እነዚህ የበጎ አድራጎት ተግባራት በማኅበረሰቡ ውስጥ ማኅበራዊ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ፣ የዜጎችን በልማት ሥራዎች የመሳተፍ ባህል እያሳደጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በባህር ዳር ከተማ በሦስቱ ትምህርት ቤቶች የሚከናወነው የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለተማሪዎች አገልግሎት እንዲውል አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ጎሹ አንዳለማሁ በበኩላቸው፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ወደ ከተማዋ በመምጣት ሰብዓዊና ሀገራዊ ተልዕኳቸውን ከመወጣት ባለፈ፣ በትምህርት ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት መሠረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸው የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባው አክለውም፣ የዛሬው የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው ትብብርና መስተጋብር እየጠናከረ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፌዴራል መንግሥት በክልሎች የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየትና ለመሙላት በሚያደርገው ጥረት የሚታየው ለውጥ ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ጎሹ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፍራኦል ጣፋ በበኩላቸው፣ ባለሥልጣኑ ለነገዋ የተሻለች ኢትዮጵያ የሚበቃ ትውልድ ለመፍጠር የትምህርት ዘርፉን ለመደገፍ ዕድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ፍራኦል የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ በፍጥነት እንደሚጠናቀቅ ቃል ገብተዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የችግኝ ተከላ የተከናወነ ሲሆን፣ በተጨማሪም ለ700 የሚጠጉ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
በሥነ-ሥርዓቱ መጨረሻም የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት መንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ቢሮ ከፌዴራል ተቋማት ለመጡ እንግዶች ክልሉን የሚያስተዋውቅና ባህላዊ እሴቶቹን የሚያንጸባርቅ ስጦታ አዘጋጅቶ አበርክቷል። ስጦታውም የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ዘውዱ ማለደ እና የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ጎሹ አንዳለምሁ በኩል ለእንግዶቹ ተበርክቷል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር