05/09/2026
የመንገድ ፈንድ በ2018 በጀት ዓመት 28 ቢሊዮን ብር ሰበሰበ፤ በ2019 በጀት ዓመት ደግሞ ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ አቀደ
ቢሾፍቱ፣ ነሐሴ 30/2018 ዓም(ኢመአ): የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከመንገድ ፈንድ የጥገና በጀት ድጋፍ ከሚደረግላቸው የሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች የመንገድ ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ሲያካሂድ የቆየውን የምክክር ውይይት አጠናቀቀ። በውይይት መድረኩ የመንገድ ፈንድ የ2018 በጀት ዓመት ገቢ አፈጻጸም 28 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተገለጿል፤ በ2019 በጀት ዓመት ደግሞ ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።
የፈንዱ ገቢ ምንጮች በነዳጅ ላይ ከሚጣል ታሪፍ፣ ከቅባትና ዘይት ታሪፎች፣ የሀገሪቱን ድንበር አቋርጠው ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች ክፍያ፣ ከአመታዊ ክብደትን መሰረት ካደረገ ዓመታዊ የፈቃድ ማደሻ እንዲሁም ከክብደት ወሰን በላይ ጭነት ቅጣቶች የሚገኘውን ገቢ ናቸው።
በመንገድ ፈንድ የሚደገፉ 72 ኤጀንሲዎች ከአመታዊ ዕቅድ ዝግጅት እስከ ክፍያ አፈጻጸም ድረስ ባሉት ሂደቶች ላይ በቴክኒክ፣ በኦዲትና በአማካሪዎች አማካኝነት የቅርብ ክትትል ይደረግባቸዋል። በተጨማሪም ኤጀንሲዎቹ በአማካሪዎቹ ስራው በትክክል መሰራቱን አረጋግጠው በሚልኳቸው የምስክር ወረቀቶች (ሰርተፍኬቶች) ላይ ተመስርቶ ክፊያ ይፈጸማል፣ ቁጥጥርም ይደረጋል።
የመንገድ ኤጀንሲዎቹ አጠቃላይ አፈጻጸም ከዕቅድ በላይ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ያሉ የበጀት ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም፣ የግብዓት ዋጋ መጨመር፣ አንዳንድ አካባቢ የሚስተዋለው የጸጥታ ሁኔታና መሰል ችግሮች በሥራዎቻቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳደረዋል። በተላይ የጥገና በጀት ማነስ፣ የነባር ግንባታ ማሽነሪዎች ዕድሳት መዘግየት እና የአዳዲስ ማሽነሪዎች ግዢ አለመፈጸም አፋጠኝ መፍትሄ የሚፈልጉ መሆናቸው ተጠቁሟል። ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ተመላክቷል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል መንግሥቴ ባስተላለፉት መልእክት፤ ከመንገድ ፈንድ የሚመደበውን በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋልና አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። አያይዘውም የፋይናንስና የሥራ አፈጻጸም ሰነዶች የሚረጋገጡበት ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋትና ተፈጻሚ ማድረግ፣ እንዲሁም ለሕብረተሰቡ የተሳለጠ የመንገድ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢንስታግራም https://www.instagram.com/ethioroads
› ኢሜል [email protected]
› ዩቲዮብ www.youtube.com/